1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሳውዲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና አዲስ ዓመት

ሰኞ፣ መስከረም 1 2010

የኢትዮጵያ  አዲስ ዓመት የ2010 አቀባበል በሳዑዲ ዓረቢያ ርዕሰ መዲና ሪያድ ቀዝቀዝ ያለ ድባብ ሰፍኖበታል፡፡ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት በግዛቱ በሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች ላይ የጣለው ወርሃዊ ክፍያ ያስፈራቸው ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያዊያን ቤተሰቦቻቸውን ወደ ሀገር ልከው ብቻቸውን ናቸው፡፡

https://p.dw.com/p/2jkBC
Ethiopian International School Riyadh
ምስል DW/Sileshi Shibru

በሳውዲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና አዲሱ ዓመት

ቤተሰቦቻቸውን ወደ ሀገር ያልላኩትም ቢሆኑ ነገ ሊመጣ ያለውን አደጋ  እያሰቡ ስጋት ውስጥ እንዳሉ ነው የሚናገሩት።
ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻቸው ላይ በሚደርሱ የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ አደጋዎች ድጋፍ ለማድረግ ቀዳሚ እንደነበሩ የሚናገሩት የሪያድ ነዋሪዎች ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ወደ ሀገር ለመግባት በሚያደርጉት ጥረት መንግስት ድጋፍ ያደርግላቸው ዘንድ ጠይቀዋል፡፡
አቶ ጸጉ ገብረ ህይወት ላለፉት 20 ዓመታት ሪያድ ሳዑዲ ዓረቢያ ከቤተሰቦቹ ጋር ኖሯል፡፡ እንኳንስ በዓውድ ዓመት በአዘቦቱም ቀን እንኳን ከ 4 ልጆቹም ሆነ ከባለቤቱ ተለይቶ አያውቅም፡፡ ዛሬ ግን ዘመን መለወጫን ያህል አውድ ዓመት አንድ ልቡን አክሱም አንዱን ደግሞ ሪያድ አድርጎበታል፡፡
የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት መምህር የሆነው ታዬ ጨፎ ልጆቹን ወደ ሀገር ከላከ 3 ቀኑ ነው ጥቂት የማይባሉ የስራ ባልደረቦቹም ቤተሰቦቻቸውን ተሰናብተው የብቸኝነት ኑሮ ጀምረዋል፡፡አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ልጆቹን እየላከ መሆኑን መታዘቡንም መምህር ታዬ ይገልጻል፡፡
የአብዛኞቹ ኢትዮጵዊያን መኖሪያ እና መገበያያ የሆነው መንፉሀ አካባቢ የኢትዮጵያዊያን ሱቆችና ሬስቶራንቶች ጭር ብለው ማርፈዳቸውን የአካባቢው ነዋሪ አቶ አያልቅበት ኃይለማሪያም  ይናገራሉ፡፡የዚያው የመንፉሀ ነዋሪ የሆነው አቶ ቶፊክም የድሮው የአውድ አመት ድባብ ዛሬ እንደሌለ ታዝቧል፡፡
በተደጋጋሚ ጓደኞቹን የሸኘው መምህር ታገል በሂያጅ ልጆች እና በቀሪ አባቶች መካከል የሚፈጠረውን ውጥረት ያነሳል ፡፡ ትላንትናም የአንድ የስራ ባልደረባውን ቤተሰቦች ሸኝቷል፡፡
በያዝነው የጎርጎሮሳዊያን 2017 ዓመተ ምህረት ሳዑዲ ዓረቢያ የሚኖር የውጭ ዜጋ በስሩ ላሉ ቤተሰቦቹ በየ ወሩ 100 የሳዑዲ ሪያል  መክፈል ጀምሯል፡፡ በ2018 ይህ ክፍያው ወደ 200 ሳዑዲ ሪያል ያድጋል፡፡ በሳዑዲ ዓረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ በተበረዘ መንፈስ ነው ዘመን መለወጫን እያከበሩ ያሉት፡፡  ምናልባትም ለአብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን ይህ ዘመን መለወጫ በሳዑዲ ዓረቢያ የመጨረሻቸው ዓውድ አመት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ስለሺ ሽብሩ

ተስፋለም ወልደየስ

ሂሩት መለሰ