1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በስዊዘርላንድ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በድርቅ ለተጎዱ ርዳታ

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 8 2008

ኤል ኒኖ ተብሎ በሚጠራው የአየር ንብረት ክስተት ምክንያት ኢትዮጵያ ከ8.2 ሚሊዮን በላይ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ፈላጊ ዜጎችን ለመመገብ በመታገል ላይ ትገኛለች። በኤል ኒኖ ምክንያት በኢትዮጵያ የተከሰተውን ድርቅ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ30 ዓመታት ውስጥ አስከፊው ሲል ገልጾታል።

https://p.dw.com/p/1HQ4e
Äthiopische Diasporagemeinde in der Schweiz
ምስል Äthiopische Diasporagemeinde

[No title]

ዓለም አቀፉ ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ ርዳታ ፈላጊ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በሚቀጥሉት ስምንት ወራት በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል ሲል አስጠንቅቋል። በአገሪቱ የተከሰተው ድርቅ «አሳስቦናል» ያሉ በስዊዘርላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለአስቸኳይ እርዳታ ፈላጊዎች የሚሆን ገንዘብ አሰባስበዋል።
በዓለም የጤና ድርጅት መረጃ መሰረት በጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም. 400 ሺህ ህጻናት የከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጦት ይገጥማቸዋል። ሌሎች አንድ ሚሊዮን ህጻናት እና 700 ሺህ ነፍሰ ጡር ወይም ጡት የሚያጠቡ እናቶች መለስተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጦትን ይጋፈጣሉ። በ30 ዓመታት ውስጥ አስከፊ በተባለው ድርቅ ምክንያት 80% ዓመታዊ ሰብል ምርት አያስገኝም ሲል የዓለም ጤና ድርጅት ጨምሮ አስታውቋል።
ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶችም ይሁኑ የኢትዮጵያ መንግስት ድርቁንና ያስከተለውን አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ጥያቄ ለመመለስ እገዛ እንደሚያስፈልጋቸው አስታውቀዋል። በስዊዘርላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። በኢትዮ-ዙሪክ የእግር ኳስ ቡድን አስተባባሪ የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ተክለጊዮርጊስ በስዊዘርላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን 30 ሺህ ፍራንክ በማሰባሰብ በጄኔቫ ከተማ ለሚገኘው የዓለም የምግብ ድርጅት ማስረከባቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
በስዊዘርላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከስፖርታዊ እንቅስቃሴው በተጨማሪ የረድዔት ተግባራትን እንደሚያከናውን የተናገሩት አቶ ቴዎድሮስ በሊቢያ ህይወታቸውን ላጡ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ወጣቶች ቤተሰቦች ከ15 ሺህ በላይ የስዊዝ ፍራንክ በማሰባሰብ መለገሳቸውን አስታውሰዋል። አሁን አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን የሚያደርጉትን እገዛም እንደሚቀጥሉም አስረድተዋል።

እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ