1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሶሪያ ተኩስ አቁም ስምምነቱ ተጣሰ

ዓርብ፣ ጥቅምት 16 2005

በሶሪያ ከአርብ ኢድ አል አድሃ በዓል አንስቶ ለአራት ቀናት እንዲፀና መግባባት ላይ የተደረሰበት የተኩስ አቁም ስምምነት መጣሱ ተገለፀ። የተለያዩ የዜና ምንጮች እንደዘገቡት ከሆነ በሶሪያ አሌፖን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞችና ግዛቶች ውጊያው አገርሽቷል።

https://p.dw.com/p/16XjO
የሶሪያ ወታደር በተኩስ አቁሙ ወቅት
የሶሪያ ወታደር በተኩስ አቁሙ ወቅትምስል picture-alliance/dpa

በሶሪያ ከአርብ ጥቅምት 16 ፣ 2005 ዓም ኢድ አል አድሃ በዓል አንስቶ ለአራት ቀናት እንዲፀና መግባባት ላይ የተደረሰበት የተኩስ አቁም ስምምነት መጣሱ ተገለፀ። የተለያዩ የዜና ምንጮች እንደዘገቡት ከሆነ በሶሪያ አሌፖን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞችና ግዛቶች ውጊያው አገርሽቷል።በመንግስት እና አማፂያን መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ለፖለቲካዊ ንግግር መንደርደሪያ ሊሆን እንደሚችል የተመድ የሶሪያ ልዩ መልዕክተኛ ላክህዳር ብራሂሚ ከትናንት በስትያ ከግብፅ ካይሮ ሆነው ገልፀው ነበር።

«አሁን ከደማስቆሱ ጉብኝቴ በኋላ የሶሪያ መንግስት አርብ በበዓሉ ቀን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ መወሰኑን መናገር እችላለሁ። በሶሪያ ግጭት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን በሙሉ ለማናገር ሞክረናል። ይህ ንግግር ስኬታማ ከሆነ ረዘም ወዳለ የተኩስ አቁም ስምምነት እና ወደ ፖለቲካዊ ንግግር የሚያሻግረን እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን። ለትኩረታችሁ አመሰግናለሁ፤ ለሁላችሁም ኢድ ሙባረክ። የተቀደሰ በዓል ይሁንላችሁ።»

ሆኖም የሠላም መልዕክተኛው እንደተመኙት ሳይሆን ቀርቶ የተኩስ አቁም ስምምነቱ መጣሱ ተገልጿል። ሶርያ ውስጥ ውጊያ በየአቅጣጫው አገርሽቷል። ዛሬ ከመዲናዋ ደማስቆስ ሰሜን ምስራቅ መውጫ ላይ በምትገኘው የሐራሳታ ከተማ ሶስት ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል። አንደኛው በመድፍ ጥይት ሁለቱ ደግሞ በዓልሞ ተኳሽ ወታደሮች ተተኩሶባቸው ነበር የተገደሉት። ሌላ አንድ ሰውም ኢርቢን በተባለች ከተማ በአልሞ ተኳሽ ተመቶ መሞቱ ታውቋል። ሆምስ በተባለችው ከተማ ማዕከላዊ ስፍራም እንዲሁ በአማፂያን በተያዘችው ካልዲዬህ አውራጃ ላይ ወታደሮች ባዘነቡት የመድፍ ውርጅብኝ አንድ ሠላማዊ ሰው እንደተገደለ ተዘግቧል።

ሶሪያዊ ህፃን በተኩስ አቁሙ ወቅት
ሶሪያዊ ህፃን በተኩስ አቁሙ ወቅትምስል AP

ከቱርክ ጋ በምትዋሰነው ሰሜናዊቷ የድንበር ከተማ ደግሞ አንድ አማፂ በአልሞ ተኳሽ እንደተገደለ አማፂያን ገልፀዋል። የሮይተርስ ጋዜጠኛ በበኩሉ በከተማው ውስጥ አራት ጊዜ የሚሆን የታንክ የተኩስ ድምጽ መስማቱን ተናግሯል። ተግባራዊ በሆነ በሠዓታት ውስጥ የተጣሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ገና ከመነሻው ጥርጣሬ እንደነበራቸው የሶሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል ሳሌህ ሙባረክ ቀደም ሲል በዚህ መልኩ ገልፀው ነበር።

«እኛ በጣም ነው ጥርጣሬ የገባን። መንግስት እስካሁን መልካም ፍላጎቱን አላሳየንም። በተኩስ አቁም ስምምነት የሚያምን ሰው ከስምምነቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በርካታ ሴቶችና ህፃናትን አይገድልም።»

የዓለም አቀፍ አደራዳሪው የተመድ መልዕክተኛ ላክህዳር ብራሂሚ ያቀረቡትን የተኩስ አቁም ስምምነት የፕሬዚዳንት ባሽር አል አሳድ ጦር እንደሚቀበል ሲገልፅ ቅድመሁኔታዎችን በማስቀመጥ ነበር። ጦሩ አማፂያንን ለማስታጠቅና ለማደራጀት በሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ አለያም በአማፂያን በኩል ለሚሰነዘር ጥቃት ፈጣን ምላሽ እንደሚሰጥ አስጠንቅቆ ነበር። የነፃ ሶሪያ ጦር አማፂ ቡድን አዛዥ በበኩላቸው አማፂያንም የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንደሚቀበሉ ሆኖም የአሳድ ጦር ስምምነቱን ማክበር እንዳለበት አስጠንቅቀው ነበር። የተኩስ አቁም ስምምነቱ በመጀመሪያ በየትኛው ወገን እንደተጣሰ አልታወቀም። ዓለምአቀፉ የሠላም አደራዳሪ የተኩስ አቁም ስምምነቱን በተመለከተ ያሳደሩት ተስፋ የበዛ ነበር ባይ ናቸው ሳሌህ ሙባረክ።

ጦርነት ያዳቀቃት የአሌፖ ከተማ
ጦርነት ያዳቀቃት የአሌፖ ከተማምስል PHILIPPE DESMAZES/AFP/Getty Images

«ሚስተር ብራሂሚ ዲፕሎማት ናቸው። እውነታውን አይደለም የተናገሩት ለማለት አልፈልግም። ይሁንና ለራሳቸው ሲበዛ ተስፈኛ ነው የሆኑት። ከተኩስ አቁሙ ስምምነት አስቀድሞ በአንዳንድ ጉዳዮች ዙሪያ መነጋገር እንፈልጋለን። እናም መንግስት ቃሉን ከጠበቀ ሁሉም ተቃዋሚዎችም ያን ነው የሚያደርጉት። በዚያ ሲበዛ ርግጠኛ ነኝ።»

ለሠዓታት መዝለቅ ያልቻለው የተኩስ አቁም ስምምነት በሶሪያ መጣሱ ተፋላሚዎችን ወደ ፖለቲካዊ ንግግር ለማሻገር ተስፋ ጥለው ለነበሩት የሠላም አደራዳሪ ታላቅ የራስ ምታት መሆኑ አልቀረም። አጀማመሩ ሠላማዊ ሆኖ ለ19 ወራት የዘለቀውን የሶሪያ ተቃውሞ የአሳድ ጦር በወታደራዊ ሀይል ለማንበርከክ ከቃጣበት ጊዜ አንስቶ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ35,000 በላይ እንደሆነ ይጠቀሳል።

ማንrt,ጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ