1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ኢጣሊያ ገቡ

እሑድ፣ ግንቦት 24 2006

የኢጣሊያ ባህር ኃይል ዳግም በሺ የሚቆጠሩ የጀልባ ላይ ስደተኞችን ማዳኑን አስታወቀ። እንደ ባህር ኃይሉ ከሆነ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ከ3000 በላይ ስደተኞችን ከኢጣሊያ የባህር ጠረፍ ተቀብሏል። ከሰሜን አፍሪቃ በኩል እንደመጡ የተነገረዉ አብዛኞቹ ስደተኞች ወደ ሲሲሊያ መወሰዳቸውም ተነግሯል።

https://p.dw.com/p/1CADd
Libyen-Flüchtlinge Ankunft Italien
ምስል Mauro Seminara/AFP/Getty Images

እንደ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ አብዛኞቹ ስደተኞች ከሶሪያ እና ግብፅ ናቸው። ካለፈው ግማሽ ዓመት አንስቶ የኢጣሊያ የባህር ኃይል በርካታ ስደተኞችን መታደግ ግድ ሆኖበታል። የኢጣሊያ መንግሥት ገና በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ስደተኞች በሰሜን አፍሪቃ በኩል አድርገው ወደ አውሮጳ ለመግባት ዝግጁ እንደሆኑ ይገምታል። የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አንጄሊኖ አልፋኖ ኢጣሊያ ብቻዋን የስደተኞቹን ጎርፍ መቋቋም ስለማትችል ሌሎች የአውሮጳ ሀገራት እንዲተባበሩ ጠይቀዋል።

ባለፉት ግዝያት አፍሪቃውያን ስደተኞች በሰሜን አፍሪቃ ወደምትገኘው የስጳኝ ወሽመጣዊ ግዛት ሜሊላ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግባትን አጥር ጥሰው በብዛት መግባታቸው ይታወቃል። የሜሊላ ፕሬዚደንት ኽዋን ኾዜ ኢምብሮዳ ለአንድ የስጳኛውያኑ ራድዮ፤ ወደ ሜሊላ ለመግባት ከሞከሩት 1000 ስደተኞች መካከል ወደ 400 የሚጠጉ እንደ ቀናቸዉም ተናግረዉ ነበር። ካለፉት አምሥት ወራት ወዲህ ወደ ስጳኛውያኑ ወሽመጣዊ ግዛቶች ሜሊላ እና ሴውታ የገባው ስደተኛ ቁጥር በጉልህ ከፍ ብሎዋል። ጥቅምት የኤርትራ ስደተኞች ያሳፈረች አንዲት ጀልባ ላምፔዱዛ አጠገብ ሰጥማ ከሰወስት መቶ በላይ ስደተኞች ካለቁ ወዲሕ ኢጣሊያ ባሕር ሐይል የባሕር ጠረፎቹን በጥብቅ እየተቆጣጠረ መሆኑ ይታወቃል። ስደተኞቹን ለማዳን ሲል ባለፈው ጥቅምት ወር የተቋቋመው « ማሬ ኖስትሩም » ወይም ሲተረጎም ባህራችን የተሰኘው ቡድን በየወሩ ዘጠኝ ሚልዮን ዩሮ ወይም በየቀኑ 300,000 ዩሮ እንደሚያወጣ የኢጣልያ መገናኛ ብዙኃን አስታውቀዋል። በዚሁ የማዳን ተግባር በየሳምንቱ በአማካይ አምስት የጦር መርከቦች እና 900 ሰዎች ተሳታፊ ይሆናሉ። የመሀል ቀኝ ዘመም « ፎርሳ ኢጣልያ » እና ፀረ ፍልሰቱ «ሰሜናዊ ሊግ » ፓርቲዎች የውዱን የሰው አድን ተግባር ወጪ የሚሸፍኑት የኢጣልያ ቀረጥ ከፋይ ዜጎች ናቸው በሚል ምክንያት ስደተኞችን ከመስመጥ አደጋ የማዳኑ ተግባር አሁኑኑ እንዲቆም ጠይቀዉ እንደነበር ተዘግቦአል። ኢጣልያ እና ሌሎች ስድስት በሜድትሬንያን ባህር አካባቢ የሚገኙ ሀገራት የአውሮጳ ህብረት በተለይ ስደተኞቹ ለሚገቡባቸው ሀገራት የሚሰጠውን ርዳታ ከፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። የአውሮጳውያኑ 2014 ዓም ከገባ ወዲህ ኢጣልያ የገቡት ስደተኞች ቁጥር ወደ 22,000 የሚጠጋ ሲሆን፣ አምና በዚሁ ጊዜ ከገቡት ስደተኞች በ10 እጥፍ ጨምሮዋል።

Italien Flüchtlinge 17.03.2014
ምስል picture alliance / ROPI

አዜብ ታደሰ

ልደት አበበ