1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሽብርተኝነትና በአሸባሪዎች ጥቃት፤ ወደር ያልተገኘላት ሶማልያ፣

ሰኞ፣ ኅዳር 6 2003

ለሽብርተኝነት ጥቃት በመጋለጥ ሶማልያ በዓለም ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ መያዟ ተገለጠ።እ ጎ አ ከ 1991 ዓ ም አንስቶ ከሞላ ጎደል ለ 20 ዓመታት ያህል ሥርዓት አልበኛነት ነግሦባት በቆየችው፣

https://p.dw.com/p/Q9mL
የአክራሪው የአሽ ሽባ ድርጅት አባላት ፣ በሰሜን መቅዲሹ፣ የጦር ልምምድ ሲያደርጉምስል AP

የተደላደለም ሆነ የተረጋጋ መንግሥት እንደሌላት በሚነገርላት ሶማልያ፣ በአደገኛነት ከኢራቅ መላቋ እየተነገረ ነው። በሩሲያ ፣ ግሪክና የመን የአሸባሪነት አደጋ በማንሠራራት ላይ ሲሆን ፣ በህንድና አልጀሪያ ጋብ ብሏል። ይህን መግለጫ ያወጣውን የብሪታንያ ኩባንያ Maplecroft ዋና ሥራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር አሊሰን ወርኸርስትን በማነጋገር ተክሌ የኋላ ተከታዩን ዘገባ አጠናቅሮአል።

«ዛሬ ያወጣነው መግለጫ(ያቀረብነው ዘገባ) ሶማልያን የሚመለከተው ዜና፣ ማለትም አገሪቱ የሽብር መዲና በመሆን ረገድ ከኢራቅ፣ አፍጋኒስታን ፣ ፓኪስታንና ኮሎምቢያ ልቃ መገኘቷን የሚያስረዳ ነው። ዘገባው፤ የዩናይትድ እስቴትስ ብሔራዊ ፀረ-አሸባሪነት ማእከል ፣ በዓለም ዙሪያ በዚህ ረገድ ሁኔታዎችን ተከታትሎ ያቀረበውን የአደገኛ ድርጊቶች፣ ጥቃቶች መዘርዝር ጥናትን መሠረትበማድረግ ፣ ሁኔታዎችን አጉልቶ ለማሳየት ጥረት ያደረገ ነው። ጥናቱም የሽብር ተግባራትን ተከታታይ ድርጊቶችና የክብደታቸውን መጠን የሚዳስስ ነው። ሶማልያ ፣ አምና፣ ከነበረችበት 4 ኛ ደረጃ ዘንድሮ(ወደ ከፍተኛ ደረጃ) አንደኛ ደረጃ ተሸጋግራለች። ይህም 156 የሽብር ጥቃት በመፈጸምና 437 ሰዎችን በመግደልና ከሞላ ጎደል 3,500 ሰዎችን በማቁሰል ነው። ይህ የተፈጸመው ደግሞ እ ጎ አ በሰኔ ወር 2009 እና ሰኔ 2010 መካከል ነው።»

የ Maplecroft ሥራ አስኪያጅ ፣ ኩባንያቸው ዘገባውን ያቀረበው በመላዋ ሶማልያ በቀድሞዋ የብሪታንያ ቅኝ ጋዛት ሶማሊላንድና በፑንትላንድ እንዲሁም በደቡብ ሶማልያ የተከሠተውን በመከታተል ቢሆንም፣ አደጋው ይበልጥ አስከፊ ሆኖ የተገኘው በማእከልና በደቡብ ሶማልያ መሆኑን ገልጸዋል።አሸባሪነት ከተናሣ ፣ ጥናቱ የባህር ላይ ውንብድናን ያጠቃለለ መሆን አለመሆኑንም ጠይቄአቸው----

«የባህር ላይ ውንብድና ፣ በዚህ መዘርዝር ጥናት አልተካተተም። ያተኮርነው በየብስ በተፈጸሙ ጥቃቶች ላይ ነው። ግን፤ የባህር ላይ ውንብድናን በተመለከተ የተለዬ መዘርዝር ጥናት አካሂደናል። ዓለም አቀፉ የንግድ ም/ቤት ፣ እንዲሁም ዓለም አቀፉ የመርከብ ንግድ ም/ቤት እንዳስረዱት ፤ የባህር ላይ ውንብድና ፣ ሶማልያ ውስጥ እጅግ የተንሠራፋ ነው። በ 2009 ብቻ 217 የባህር ላይ ውንብድና ተግባር ተፈጽሟል።»

Maplecroft ያቀረበው የጥናት ውጤት ፣ ለራሷ ለሶማልያ፣ ለአጎራባች አገሮች የተፈጥሮ ጋዝና ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ለሚሹ ኩባንያዎች፣ ብዙ የንግድ መርከብ በሚተላለፍበት መሥመር ለሚገለገሉ የንግድ መርከቦች ሁሉ፣ በዚያ የአፍሪቃ ክፍል ንግድ ለማካሄድ ለሚፈልጉ ሁሉ ባ,አጠቃላይ ጠቃሚ ምክር የሚለግሥ መሆኑን የዚሁ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ Prof. Alyson Warhurst አስረድተዋል።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ