1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቡርኪና ፋሶ አዲስ መንግስት ከፍተኛ ተቃውሞ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 22 2007

በቡርኪና ፋሶ ወታደራዊው ኃይል የአስተዳደር ሥልጣኑን ከተረከበ በኋላ እሁድ፣ ጥቅምት 23 ቀን 2007 ዓ. ም. መዲና ዋጋዱጉ ዳግም በተቃዋሚ ሰልፈኞች ተጥለቅልቃ ዋለች። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች ጎዳና በመዉጣት የሽግግር መንግሥቱ መሪ ሆነዉ ቅዳሜ የተሾሙትን ኮሎኔል ይሳቅ ዚዳን ተቃዉመዋል።

https://p.dw.com/p/1DfYR
Proteste nach Militärputsch in Bukina Faso 02.11.2014
ምስል Issouf Sanogo/AFP/Getty Images

ሰልፈኞቹ የሀገሪቱ የቀድሞ የጦር ምክትል አዛዥ የሀገሪቱን የአስተዳደር ሥልጣን መያዝ የለበትም፤ የሽግግር መንግስቱ ከሲቪሉ ማኅበረሰብ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መሆን አለበት ሲሉ ተቃዉሟቸዉን ገልፀዋል።ስልጣናቸዉን ያስረከቡት የቀድሞዉ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ብሌዝ ኮምፓዎሬ በጎርጎሪዮሳዊዉ 1987 ዓ,ም በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ሥልጣን መምጣታቸዉ ይታወሳል። የአፍሪቃዉ ሕብረት በበኩሉ በአሁኑ ሰዓት በቡርኪና ፋሶ ስልጣን ይዞ የሚገኘዉ ወታደራዊ ኃይል ሥልጣኑን ለሲቪሉ እንዲያስረክብ ጠይቋል።

እንደ ምዕራብ አፍሪቃዊትዋ ሀገር ቡርኪና ፋሶ ሕገ-መንግሥት አዲስ ምርጫ በ90 ቀናት ዉስጥ መካሄድ ይኖርበታል። ዩኤስ አሜሪካም በቡርኪና ፋሶ ወታደራዊዉ ኃይል ወደ ሥልጣን መምጣቱን አዉግዛለች። በበርሊን የሚገኘዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግዴታ ካልሆነ በቀር ወደ ቡርኪና ፋሶ ጉዞ ባይደረግ መመረጡን አስታዉቋል።

የቡርኪና ፋሶ ጦር ሰራዊት ኮሎኔል ዚዳን የሽግግር መንግሥቱ መሪ ሲል ቅዳሜ ዕለት ሰየመ። ለረዥም ዓመታት ቡርኪና ፋሶን በፕሬዚዳንትነት ያስተዳደሩት ብሌዝ ኮምፓዎሬ በሕዝባዊ ዓመፅ ግፊት ሥልጣናቸዉን ከለቀቁ በኋላ ከ24 ሰዓታት በላይ ሀገሪቱን የሚያስተዳድረዉ ከፍተኛ ባለስልጣን ማን መሆኑ በግልፅ የታወቀ አልነበረም።

ኮሎኔል ያኩባ ይሳቅ ዚዳን የሽግግር መንግሥቱ መሪ ሆነዉ የተሾሙት የቡርኪና ፋሶ ከፍተኛ የጦር ሠራዊት አመራር ካካሄደው የአስቸኳይ ጉባዔ በኋላ መሆኑ ተመልክቶአል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ከሥልጣን በመወገዳቸው በተፈጠረው ክፍተት የተነሳ በኮሎኔል ያኩባ ይሳቅ ዚዳ እና በጄኔራል ትራዎሬ መካከል የሥልጣን ሽኩቻ ተፈጥሮ እንደነበር ይታወቃል። የቡርኪና ፋሶ ከፍተኛ የጦር አመራር በንባብ ባሰማው መግለጫ «ፕሬዚዳንት ብሌዝ ካምፓኦሬ ከተወገዱ በኋላ ክፍት የሆነውን የሽግግር ጊዜ እንዲመሩ ኮሎኔል ያኩባ ይሳቅ ዚዳ ያለአንዳች ተቃውሞ ተመርጠዋል »።

የቡርኪና ፋሶ የቀድሞ ፕሬዚዳንት በሕዝባዊ ዓመፅ ከሥልጣናቸው የተወገዱት ሀገሪቱን ለ27 ዓመታት ከገዙ በኋላ የሥልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ማቀዳቸውን ተከትሎ በተነሳው ሕዝባዊ ቁጣ መሆኑ ይታወቃል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሥልጣናቸውን ለቀው ወደ ጎረቤት ሀገር አይቮሪኮስት መኮብለላቸውን ራዲዮ ፍራንስ ኢንተርናሽናል ዘግቧል።
ቡርኪና ፋሶ ከፈረንሳይ ቅኝ ነጻ ከወጣችበት እ.ኤ.አ. 1984 ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የምታውቀው ሁለት መሪዎች ብቻ ነው። አፍሪካዊው ቼ ጉቬራ ይባሉ የነበሩት ቶማስ ሳንካራን እና ብሌዝ ኮምፓዎሬን ። ብሌዝ ኮምፓዎሬ ወደ ስልጣን የመጡት ቶማስ ሳንካራ በወታደሮች መገደላቸውን ተከትሎ እንደ ጎርጎረሳዊዉ አቆጣጠር በ1987 ዓ.ም. ነበር። ዛሬም ድረስ ግልጽ ባይሆንም በቶማስ ሳንካራ ግድያ እጃቸው እንዳለበት ይጠረጠራል። ወደ ስልጣን ሲመጡ ታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታት እና የቀድሞ ጓደኛቸውና መሪያቸው ቶማስ ሳንካራ የሚከተሉትን ሶሻሊዝም አሽቀንጥሮ መጣል በቀዳሚነት ያከናወኗቸው ተግባራት ነበሩ።
ኮምፓዎሬ እንደ ጎርጎረሳዊዉ አቆጣጠር በ1991 እና 1998 የተካሄዱ ሀገራዊ ምርጫዎችን አሸንፈዋል። እንደ ጎርጎረሳዊዉ አቆጣጠር በ2000 የወጣው አዲስ የቡርኪና ፋሶ ህገ-መንግስት የፕሬዝደንቱን የስልጣን ዘመን ለአስር ዓመት ብቻ ቢወስነውም ተጨማሪ ሁለት ምርጫዎችን ከማሸነፍ አላገዳቸውም። በሁሉም ምርጫዎች ከ80 በመቶ በላይ ድምፅ በማግኘት ነበር ያሸነፉት።ኮምፓዎሬ ቡርኪና ፋሶን ሲመሩ ስልጣን ሁሉ በእጃቸው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስቴር ይሾማሉ። መንግስታዊ መዋቅሩና ሀገራዊ ጦሩ በእርሳቸው ጥብቅ ቁጥጥር ስር ነበር። ራሳቸውን የሀገሪቱ መረጋጋትና ኢኮኖሚያዊ እድገት ጠበቃ አድርገውም ይቆጥሩ፤ ይሰብኩም ነበር። አሁን ግን የልጅነት ጓደኛቸውን ገድሎ ለስልጣን ያበቃቸው የሀገራቸዉ ጦር ለ27 ዓመታት የነገሱበትን መንበረ ነጥቆ ስልጣኑን መያዙን አስታዉቋል።ብሌዝ ኮምፓዎሬን የሸኘው የቡርኪና ፋሶ ተቃውሞ አዲሱ መሪን ለመቃወም ከአንድ ሌሊት በላይ መጠበቅ አልፈለገም። እሁድ ጥቅምት 23 ቀን 2007 ዓ. ም. መዲና ዋጋዱጉ ዳግም በተቃዋሚ ሰልፈኞች ተጥለቅልቃ ውላለች።

ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ

Burkina Faso Machtübernahme General Honore Traore 31.10.2014
የቡርኪና ፋሶ ከፍተኛ የጦር ሠራዊት አመራርምስል Reuters/J. Penney
Burkina Faso - Oberst Isaac Zida
ኮሎኔል ያኩባ ይሳቅ ዚዳንምስል ISSOUF SANOGO/AFP/Getty Images