1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በነዳጅ ለውጥ ምግብ፧

ሰኞ፣ ጥቅምት 21 1998

ሐምሌ 26 ቀን 1982 ዓ ም፧ ኢራቅ ክዌትን ከወረረች በኋላ፧ ዓለም አቀፍ እገዳ ተጥሎባት እንደነበረ አይዘነጋም። ያኔ፧ በተጠቀሰው እርምጃ ሳቢያ፧ ህዝቡ ለህልውና መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን በማጣት፧ ደርሶበት የነበረውን ብርቱ ችግር፧ በመጠኑም ቢሆን ለማቃለል፧ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዘረጋው ሰብአዊ መርኀ-ግብር፧ አገሪቱ ከምታመርተው ነዳጅ ዘይት በከፊል እየተሸጠ ምግብና መድኀኒት ይቀርብ እንደነበረ የሚታወስ ነው። ድርጊቱ፧ የሆነው ሆኖ፧ ከሙስና የ

https://p.dw.com/p/E0eD
ምስል AP

�ዳ እንዳልነበረ፧ በተለይ ባለፉት ወራት፧ ከየአቅጣጫው የተሰማው ወቀሳ ይጠቁማል።

ድርጅቱ፧ ያሠማራው መርማሪ ኮሚሽን፧ ባለፈው ሐሙስ ይፋ ባደረገው የምርመራ ውጤት ላይ የዶቸ ቨለ ባልደረባ፧ ፔተር ፊሊፕ የሚከተለውን ሐተታ አቅርቧል።
በኢራቅ ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ፧ የተፈጥሮ ሀብት ባለው አንድ ሀገር ላይ ያን የመሰለው እርምጃ የቱን ያህል ተፈጻሚ ሊሆን እንደሚችል ወደፊት፧ የሚሰጠው ትምህርት ይኖራል። ኢራን፧ በአቶም ጥያቄ ላይ፧ አሻፈረኝ እንዳለች ከቀጠለች፧ አንድ ወቅት በኢራቅ ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ በእርሷም ላይ ሊደገም ይችል ይሆናል። በሀብታም አገሮች ላይ የንግድ እገዳ ማስተዋወቁ ከባድ ነው፧ የእገዳውን ደንብ ማክበሩ ደግሞ ይበልጥ ያስቸግራል። የሚያስገርመው፧ እገዳ እንዲጣል ግንባር ቀደም ሆነው የተገኙ መንግሥታት፧ ድርጅቶችም ሆኑ ኩባንያዎች ህጉን እስከመጣስ የደረሱበት ሁኔታ ነው። በሳዳም ሁሴን ሥር በነበረችው ኢራቅ፧ በእገዳ ሳቢያ የተጎዳውን ህዝብ ሥቃይ ለማስታገስ፧ በነዳጅ ለውጥ ምግብና መድኀኒት፧ እንዲሁም የተለያዩ ተፈላጊ ቁሳቁሶች በቀረቡበት የንግድ ውል የተሳተፉት ከ 2,000 በላይ የሚሆኑ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ነበሩ። በዚህ ሙስና በተጠናወተው የንግድ ልውውጥ፧ የኩባንያዎቹና የአምባገነኑ ሳዳም ካዝና በተትረፈረፍ ገንዘብ ነበረ የተሞላው።
600 ገጾች ያሉት፧ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፧ የመርማሪ ኮሚሽኑ ዘገባ እንደሚያስረዳው፧ «በነዳጅ ምትክ ምግብ« የተሰኘው መርኀ-ግብር፧ ስንጥቅ ትርፍ የሚዛቅበት ልዩ የንግድ ልውውጥ ሆኖ ነበር። ሳዳም ሁሴን በዚሁ ከውጭ እኽልና መድኀኒት ማስገባት በተቻለበት የንግድ ልውውጥ፧ «የሰላም ተቆርቋሪዎች« በሚሰኙ ወገኖች በኩል ብቻ አልነበረም፧ በቢልዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ እንዲንቀሳቀስ ያበቁት። በዓለም ዙሪያ፧ የታወቁ ዝና ያላቸው ኢንዱስትሪዎችና ኩባንያዎች እንዲሁም የሥርዓታቸው ተወካዮች ጭምር ትርፍ ዝቀዋል። በዚህ አማላይ የንግድ ልውውጥ የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞችም «ከደሙ ንፁህ« ሆነው አልተገኙም። ከእነዚህም አንዱ፧ በባግዳድ «ምግብ በነዳጅ ዘይት ምትክ« የተሰኘው መርኀ-ግብር ሥራ አስኪያጅ ጀርመናዊው von Sponek ናቸው። እገዳ የተደረገበትን መንግሥት ይቃወሙ የነበሩትና ያኔ በሙያ ብቃትም ማለፊያ ስም የነበራቸው ሰው በመርማሪ ኮሚሽኑ፧ የተባበሩትን መንግሥታት ውሳኔ የሚፃረር ተግባር እንዳላከናወኑ ተመሥክሮላቸዋል። ይሁንና፧ von Sponek የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመደበላቸውን ተግባር ከፈጸሙ በኋላ፧ ኢራቅ ውስጥ በኀላፊነት ይሠሩ በነበረበት ወቅት፧ በንግድ ውስጥ ተሠማርተው በነበሩ ቢያንስ ሁለት ኩባንያዎች ውስጥ ተቀጥረው መሥራታቸው ተደርሶበታል። በኢራቁ «ምግብ በነዳጅ ዘይት ምትክ« መርኀ-ግብር፧ ከተከሰተው ሙስናም ሆነ ጉቦኛነት ጋር ተያይዞ አንዳንድ የታወቁ የጀርመን ኩባንያዎች ስም ተጠቅሷል። አንዳንዶቹ፧ ፀጥ ሲሉ፧ አንዳንዶቹም፧ የረባ ድርሻ እንዳልነበረቸው በመጥቀስ ተሳትፎቸውን ትርጉም የለሽ ለማስመሰል በመጣር ላይ መሆናቸው ይሰማል። በእነርሱ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ዐቃቤ-ህግም አልተገኘም።
ያን ያህል የዴሞክራሲ አስተዳደር ባልሠፈነባቸው አገሮች፧ የኢንዱስትሪ ምርቶች አቅርቦት ወይም ንግድ፧ በጉቦ ሲታጀብ፧ ዐሠርተ ዓመታት አልፈዋል። ጉቦው የሚቀርበው ሌሎች ተወዳዳሪ ኩባንያዎችን አሸንፎ ውል ለማድረግ ነው። የሚያሳዝነው፧ ፔተር ፊሊፕ እንደሚለው፧ ይህን የሚያደርጉት ኩባንያዎች፧ ከመንግሥት በኩል የቀረጥ ቅናሽ ሲደረግላቸው መቆየቱ ነው። ሞራል፧ የሥነ-ምግባር ስሜት፧ ድንገት ከየት ሊመነጭ ይችላል? ንግድ፧ ንግድ ነው። የሞራል ጥያቄ ደግሞ ሌላ ጉዳይ ነው። ፖለቲካውም አብዛኛውን ጊዜ ከሞራል ጋር የተቆራኘ አይደለም። ታዲያ፧ ገንዘብ በገፍ በሚንቀሳቀሥበት ቦታ፧ በግንባር ቀደምትነት ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ የሚመደቡ ሰዎች ሁሉ፧ በሞራላዊ ሥነ ምግባር ታንጸው ሥራቸውን የሚያካሂዱ ይሆናሉ ብሎ፧ እንዴት መጠበቅ ይቻላል?