1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኑረንበርግ የኢትዮጵያዉያን ማኅበር 25ኛ ዓመት

ዓርብ፣ ግንቦት 5 2008

« እኔ መጨረሻ መናገር የምፈልገዉ ኢትዮጵያዉያኖች በማኅበር መገናኘት እንዳለባቸዉ አዉቃለሁ። ስለዚህ የኔ ጥሪ በልዩነታችን ተቻችለን አብረን ሆነን ሃገራችንን እንድናሳድግና በዓለም ጥሩ ስምና ዝና እንዲኖራት ለማድረግ እንድንሞክር ጥሪዬን አቀርባለሁ አመሰግናለሁ» ሲሉ የማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ መንግሥቱ አበበ ገልፀዋል።

https://p.dw.com/p/1Im94
Nürnberg Äthiopischer Kulturverein Feier 25. Jahrestag der Gründung
ምስል DW/A. T. Hahn

በኑረንበርግ የኢትዮጵያዉያን ማኅበር 25ኛ ዓመት


« እዚህ ሃገር ተወላጅ እንዲሁም ተጋብተንም የተዋለድን አለን ልጆቻችን ባህላችንን እንዳይረሱ እርስ በራሳችን ተከባብረን ልጆቻችንም እኛን እንዲያከብሩ፤ ከዚህ በተጨማሪ ልጆቻችን የእዚህን ባህል ይዘዉ፤ እኛ ማኅበር መስርተን ልጆቻችን እንዲገናኙ ካላደረግን ልጆቻችን የኛን ባህል እየረሱ ወደ ሌላዉ ባህል ይሄዳሉ፤ እኔ ለምሳሌ ከጀርመን ነዉ የተጋባሁት ልጄ ባህሌን እንትረሳ አልፈልግም፤ ከሁለት ብሔርም ብትወለድ ባህሌን ይዛ የባለቤቴንም ባህል ይዛ እንድታድግ ነዉ የምፈልገዉ፤ እና እያንዳዳችን እርስ በራሳችን ተከባብረን ልጆቻችንም ለኛ ክብር እንዲኖራቸዉ ሲያድጉም ፈሪሃ እግዚአብሔር እንዲኖራቸዉ፤ በኢትዮጵያዉያን ባህላዊ ዝግጅት ላይ ልጆቻችንን ይዘን እንድንገኝ » ይላሉ ፤ ባለፈዉ ሳምንት መጠናቀቅያ ላይ በባየር ግዛት ኑረንበርግ ከተማ «በኑረንበርግና አካባቢዉ የኢትዮጵያዉያን ባህል ማኅበር» በሚል የተቋቋመዉ የኢትዮጵያዉያን ማኅበር የተመሠረተበትን 25ኛ ዓመት በደማቅ ባከበረበት ወቅት አንዲት የማኅበሩ አባል ለክብረ በዓሉ እድምተኛና የማኅበሩ አባላት የተናገሩት።

ከ 200 በላይ ኢትዮጵያዉያንና ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን የተሰባሰቡበት ማኅበር በምስረታዉ 25 ኛ ዓመት ድግስ ላይ ከኢትዮጵያ ባህላዊ አልባሳት ትርዒት ምግብና መጠጥ ባሻገር ባለፉት 25 ዓመታት ከምሥረታዉ ጀምሮ የሠራዉን ተግባራት ለተጋባዥ እንግዶች አሳይቷል፤ ታሪክንም አስደምጦአል። ከማኅበርተኛዉ አብራክ የወጡት ሕጻናትም ባህላቸዉን አዉቀዉ ቋንቋን ተምረዉ በኩራት ስለአገራቸዉ ታሪክና ባህል በመድረክ ላይ ለሌላዉ ሲያሳዩ ማየቱ የሚፈጥረዉን ደስታ በቃላት መግለጽ መቻሉ በርግጥ የሚቻል አይመስልም። በዕለቱ ዝግጅታችን በጀርመን ኑረንበርግ ከተማ «በኑረንበርግና አካባቢዉ ኢትዮጵያዉያን ባህል ማኅበር» ክብረ በዓልን እያየን ሥለ ማኅበሩ አመሰራረትና ሥራዉ እንቃኛለን!
በርግጥ ከ 200 በላይ ኢትዮጵያዉያንና ትዉልደ ኢትዮጵያዉያንን በአንድ ጃንጥላ ያሰባሰበዉ የ«ኑረንበርግና አካባቢዉ የኢትዮጵያዉያን ባህል ማኅበር» የዛሬ 25 ዓመት ሲቋቋም ማኅበሩ ዛሬ 25ኛ ዓመቱን ሲያከብር በደገሠበት አይነት በተንጣለለ አዳራሽ ዉስጥ ሳይሆን በአንዲት አነስተና ክፍል ዉስጥ ነበር። ስሙም ቢሆን በኑረንበርግና በአካባቢዉ የኢትዮጵያዉያን መገናኛ ማኅበር በሚል ነበር የሚታወቀዉ። የዛሬ 25 ዓመት በሚኖሩባት ክፍላቸዉ ኢትዮጵያዉያንን በማሰባሰብ ማኅበር ከመሠረቱት መካከል አቶ ብርኃነ ማርቆስ ታደሰ ይገኙበታል። አቶ ብርኃነ ማርቆስ ይህንን ማኅበር መሥርተዉ በግሩ አቁመዉ አሁን መኖርያቸዉን ሰሜን አሜሪካ አድርገዋል። ማኅበሩ 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ሲዓከብር በክብር እንግድነት ተገኝተዉ ነበር።

« አዎ ድሮ ኑረንበርግ ስብሰባ ስንጀምር እዚህ ወጣቶች ነን፤ በብዛት በምንኖርበት በነበረዉ የስደተኞች መጠለያ መሰብሰብያ አዳራሽ የለዉም ነበር፤ እኔ ቤት ስብሰባ ጀመርን፤ የማኅበሩ የመጀመርያ ሊቀመንበር አቶ አበበ ነዉ፤ እና እኔም ከመስራቾቹ ጋር አንድ ላይ ሆኜ እናግዝ ነበር ፤ እና በዝያን ጊዜ ቁጥራችን ከ 19 አንበልጥም ነበር ፤ ምናልባት በጎርጎረሳዉያኑ 1993 ዓ,ም ወደ አሜሪካ ጠቅልዬ ልሄድ ስል ወደ 30 ምናም ደርሰናል። አላማችንም ብዙዉን ጊዜ ለመረዳዳት ነበር። የመጀመርያ ስብሰባችን አንዲት ሙሉ የምትባል ልጅ ታማ እስዋን ለማስጠጋት ለማልበስ ለማብላት ለማጠታት ነበር። ከዝያ በኋላ ማኅበሩ እየሰፋ እየሰፋ ሄደ፤»

እንደ ጎርጎረሳዉያኑ 1999 ዓ,ም በጀርመን ሕግና ደንብ መሠረት ሕጋዊነቱን ያገኘዉ ይህ ማኅበር የወቅቱ ሊቀመንበር ማኅበር በመተዳደርያ ደንቡ መሠረት በአምስት የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባላት በመጀመርያ ለተወሰኑ ዓመታት ያህል ደንቡን በማሻሻል በየሁለት ዓመቱ ምርጫ እየተካሄደ ዛሬ 25ኛ ዓመቱን ለማክበር መቅቶአል ። የወቅቱ የማኅበሩ ሊቀመንብር አቶ መንግሥቱ አበበ በማኅበሩ ክብረ በዓል መጀመርያ የመክፈጫ ንግግር አድርገዋል። በንግግራቸዉ በዓሉን ለማክበር የመጣዉ የበዓሉ ታዳሚ ኢትዮጵያ ዉስጥ በፖለቲካ ልዩነትታቸዉ ለታሰሩ በሠዉ ሰራሽና በተፈጥሮ የረሃብ አደጋ ለደረሰባቸዉ እንዲሁም በስደት በተለያዩ የዓለም ሃገራት ተበታትነዉ በሞት ለተቀጠፉ ኢትዮጵያዉያን በሕሊና ፀሎት እንዲታሰቡ ጠይቀዉም ነበር። አቶ መንግሥቱ ስለ ማኅበሩ በሰጡን ቃለ-ምልልስ

« አዲስ ነገር ማለት የምፈልገዉ እስካሁን ድረስ በየወሩ እንገናኛለን ፤ በራችን ክፍት ነዉ፤ ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ መጥቶ ከኛ ጋር ቁጭ ብሎ ቡናና እና ሻይ ጠጥቶ ተወያይቶ የሚሄድበት መድረክ ነዉ። ቀደም ሲል ይህን የምናደርገዉ በየሳምንቱ ነበር ግን አብዛናችን ቤተሰብ ሲመርት ልጆች ሲመጡ ሥራ ሲበዛ ጊዜ ሲያጥር በወር አንድ ጊዜ መገናኘታችን ይበቃል ብለን ወስነን አሁን የምንገናኘዉ በወር አንድ ጊዜ ነዉ። ስንገናኛ በሃገራችን ጉዳይ ላይ እዚህ ጀርመን ሃገርም ባለዉ ሁኔታ በየኢትዮጵያዉያን ስደተኞችን በተመለከተ በሚደረገዉ አንዳንድ ጉዳይ ላይ እየተነጋገርን ያለዉን ነገር ለመግለጽ እና የዚህ ሃገር ኅብረተሰብም እንዲያቀዉ ለማድረግ ነዉ»

የዛሬ 25 ዓመት በጀርመን ኑረንበርግ ከተማ የኢትዮጵያዉያኑ ማኅበር ሲቋቋም ሌላዉ ከመስራቾቹ አንዱ የነበሩት አቶ አህመድ ሲራጅ ማኅበሩ ዛሬ 25ኛ ዓመቱን የሚያከብረዉ ማኅበሩ ከምን ተነስቶ ዛሬ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ለማሳየት ማኅበሩ ራሱ በጀርመን ሃገር አኗኗር ምን ያህል እንደተዋሃደ ለማሳየት፤ ለማያዉቁን ኢትዮጵያዉያንም ለማስተዋወቅ ነዉ ሲሉ ነዉ የገለፁልን።

ለኢትዮጵያዉያን እስከዛሬ ምን ሰርታችኋል ምን ምን አድርጋችኋል?

« ለኢትዮጵያዉያን እንደተገለፀዉ ማኅበሩ የተመሰረተዉ በአጋጣሚ እዚህ ከተማ ዉስጥ በደረሰ የኢትዮጵያዊ የሞት አደጋ ነዉ፤ ኃዘን ነዉ። ያ ክስተት ለሁላችንም ከባድ ድንጋዜ ነበር። ከዛ ጊዜ ጀምሮ በተለያየ ጊዜ በተለይ ያንን በማስታወስ ሰዉ ብቻዉን መሆን የለበትም በዚህ በባዕድ ሃገር። እንደሚታወቀዉ ኑረንበርግ ትልቁ ስደተኞች የሚገኙበት ብዙ ስደተኞች ጥገኝነት የሚያመለክቱበት ከተማ ነዉ። በዝያን ጊዜ በጣም ብዙ ኢትዮጵያዉያን የሚመጡበት ወቅት ነበር እና ይህ ማኅበር እነዚህ አዲስ የሚመጡ ኢትዮጵያኖችን በሚገናኙበት ቦታ እንዲመጡ እያደረገ ብቸኝነት እንዳይሰማቸዉ ቢያንስ በቋንቋ ተወያይቶ ያንን ብቸኝነት ትንሽ የሚጋራቸዉ ሰዉ መኖሩንና ሃገሩን የሚያዉቅ ሰዉ መኖሩን እንዲያዉቁ ያደርግ ነበር። ከዛ በተጨማሪ ስደተኞች የሚደርስባቸዉን ችግር ከጎናቸዉ በመቆም ለሚመለከተዉ መስርያ ቤት በማመልከት፤ በሌላ በኩል ሆስፒታል የገቡ ወገኖቻችንን ሆስፒታል ድረስ እየሄዱ መጠየቅ ትልቁ ስራችን ነበር። ከዝያም አልፎ ሃገራችን ዉስጥ በሚደርሱ የተለያዩ ችግሮች ፤ በተለይም በአሁኑ ጊዜ የሚሰማዉ ከባድ የረሃብ አደጋ ሃገራችንን በተለያዩ ወቅት አጋጥሞአታል፤ ለዝያም ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረግንበት ጊዜ ነዉ። የዚህ ማኅበር እዚህ መመስረት ከዝያ በኃላ ብዙ ማኅበሮች እንዲቋቋሙ መሰረት የሆነም ነዉ። ለምሳሌ ከዝያ በመቀጠል የስፖርት ማኅበር ኑረንበርግ ዉስጥ ተቋቁሞአል። ከዝያም ቀጥሎ የኅብረት ክንድ በኤድስ ላይ የሚል ማኅበር መስራቾችም ነን። ይህ ማኅበር እጅግ ትልቅ ስራ እየሰራ ያለ ማኅበር ነዉ። ታድያ እነዚህ ሁሉ ማኅበሮች የ«ኑረንበርግና አካባቢዉ የኢትዮጵያዉያን ባህል ማኅበር» ጥንካሪና ዉጤቶች ናቸዉ። »

አቶ አህመድ ሲራጅ በባየር ግዛት በኑረንበር ከተማና አካባቢዉ በቁጥር እስከ 1000 ኢትዮጵያዉያን ይኖራሉ ተብሎ እንደሚገመት ተናግረዋል።

የኅብረት ክንድ በኤድስ ላይ በሚባል ማኅበር ዉስጥ የየሚያገለግሉት ወ/ሮ ገነት የማነ በዚህ ማኅበር በተለይ በገንዘብ ያዥነት አገልግለዋል። ማኅበሩ በተለይ እዚህ ለሚያድጉ ሕጻናት ባህልን በማስተዋወቅ ትልቅ ሚናንን እንደሚጫወትም ተናግረዋል። ወ/ሮ ገነት ማኅበሩ በተለይ አዲስ ለሚወለዱ ኢትዮጵያዉያን ቋንቋን እና ባህልን በማስተማሩ ረገድ ከፍተኛ ስታ እየሰራም መሆኑን አክለዉ ገልፀዋል።

የክብረ በዓሉን መድረክ በአማርኛና በጀርመንኛ ቋንቋ በመምራት ታሪክ ባህል እያስተዋወቁ ፈገግ እያሰኙ የመሩት የማኅበሩ አባል አቶ ትርፊ ፈቃዱ ስለወቅታዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁኔታና የሰብዓዊ መብት አያያዝ በተለይ ደግሞ በወቅቱ ኢትዮጵያ ዉስጥ ስላለዉ ተፈጥሩዋዊ ችግር በሚመለከት ማኅበሩ መረጃዎችን ማዘጋጀቱን ሲገልፁ ነበር ። ማኅበሩ በተለይ በኢትዮጵያ በድርቅ ለተጎዱ ኢትዮጵያዉያን የርዳታ ማሰባሰብያ ዝግጅትም መጀመሩም ተመልክቶአል። ይህ ማኅበሩ እንደተቋቋመ ይህን የኢትዮጵያዉያን ቡድን የተቀላቀሉትና በማኅበሩ በርካታ ሥራዎችን የሚሰሩት አቶ ካሱ ለገሰ ማኅበሩ ይላሉ።

« እኔ ማኅበሩ በተመሰረተ በዓመቱ ነዉ ወደዚህ ሃገር የመጣሁት፤ የመጀመርያዉ የስራ አስኪያጅ ኮሚቴ ሲመሰረት ወይም ማኅበሩ ሕጋዊ በሚደረግበት ሰዓት ማኅበሩን ተቀላቅያለሁ። መጀመርያ በአባልነት ከዝያም የመጀመርያዎቹን ሁለት ዓመታት በጸሐፊነት ከዝያ ማኅበሩን ለስድስት ዓመታት በሊቀመንበርነት ሁሉ መርቻለሁ። ማኅበሩ ጋር የቀረበ ድርሻ ነዉ ያለኝ፤»

ማኅበራችን አመሰራረቱ ሰዎችን ለማገናኘት ነዉ ከዝያ በቀጣይነት ግን ከኢትዮጵያ ጋር ያለዉን ግንኙነት ለማጠንከር መሥራት ነዉ፤ ሲሉ አቶ ካሱ ለገሰ ተናግረዋል።

« በማኅበሩ ሕገ ደንብ ላይ እንደተጻፈዉ ከኢትዮጵያ ጋር ያለዉን ግንኙነት ለማጠንከር ፤ በሃገር ቤት በተፈጥሮና በሰዉ ሰራሽ ችግሮች በሚደርስ አደጋ በሚደርስ ጊዜ ማኅበሩ የራሱን የሆነ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ሕጉ ራሱ ይጠይቃል፤ በዝያም መሰረት በተለያየ ጊዜ የድርቅ አደጋ ወይም የረሃብ ችግር በተከሰተ ጊዜ ማኅበሩ በፍጥነት በመንቀሳቀስ አስተዋጽኦ ያደርጋል ከዚህ በተጨማሪ ፤ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲታዩ ማኅበሩ ድምፁን ከማሰማት በላይ ማድረግ የሚገባዉን ሁሉ ያደርጋል። በስደተኞች ጉዳይ ደግሞ መብት ለማስጠበቅ ከከተማዉ አስተዳደር እስከ መራሂተ መንግስትዋ ጽፈት ቤት ድረስ ደብዳቤዎችን በመላላክ አስተዋጽኦ ያደረገበት ጊዜ ሁሉ አለ። »

አርቲስት ታምሩ ዘገየ በኑረንበርግ ከተማ ሲኖር ሁለት ዓመት ግድም ሊሆነዉ ነዉ። ታምሩ ምንም እንኳ ሲወለድ ጀምሮ እግሩ በሽተኛ ቢሆንም በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ተመስግቦል። በጀርመን ሃገር በተለያዩ ግዙፍ የቴቬቭዥብ ጣብያዎች የአክሮባት ችሎታዉን ሲያሳይ ቀርቦ በብዙዎች ዘንድ ታዋቂነትን አግኝቶአል። በኑረንበርጉ የኢትዮጵያዉያን ማኅበር ላይ ተገኝቶ ይህንኑ ችሎታዉን አሳይቶ አዝናንቶአል።

በኢትዮጵያ ባህል የከሸነዉ ዶሮ በከሰል የተፈላዉ ቡና ፤ ምስር ሽሮዉ ሳይቀር ከወጣት የዘመናዊ ሙዚቃ ባንድና የወጣት ኢትዮጵያን ልጆች ባህላዊ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ዉዝዋዜ፤ ጀርመናዉያኑን አፍዝዞ እኛ ኢትዮጵያዉያኑን ደግሞ ኩራት አላብሶ ከስክስታዉም ወገብ አስፈትሾ፤ በፍቅር በደስታ ለዓመት አይለየን፤ ለዓመት እንዲሁ በድግሱ አሰባስቦ ያገናኘን አሰኝቶአል። በደስታ ቃለ-ምልልስ መስጠት እኪያቅታቸዉ እንባ የተናነቃቸዉ የወቅቱ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ መንግሥቱ አበበ በመጨረሻ ያላቸዉ መልክት ደግሞö

« እኔ መጨረሻ መናገር የምፈልገዉ ኢትዮጵያዉያኖች በማኅበር መገናኘት እንዳለባቸዉ አዉቃለሁ። ስለዚህ እዝያ ነገር ላይ በግሌ አጠናክሪ መስራትን ነዉ የምፈልገዉ። ኢትዮጵያዉያኖች ተገናኝተዉ ያለባቸዉን ልዩነት ትተዉ አብረዉ መሆን እዳለባቸዉ የሚል ኃሳብ ስላለኝ ነዉ ። ስለዚህ የኔ ጥሪ በልዩነታችን ተቻችለን አብረን ሆነን ይሄን ሃገር እንድናሳድግ እና ሃገራችን በዓለም ጥሩ ስምና ዝና እንዲኖራት ለማድረግ እንድንሞክር ጥሪዬን አቀርባለሁ አመሰግናለሁ»

የዝግጅት ክፍላችን ኑረንበርጎች እንግዳ ተቀባዮች መሆናቸዉን ማስመስከራቸዉን ሳይገልፅ ማለፍ አይፈልግም። ከሁሉ ከሁሉ ግን ዝግጅቱ በተባለበት ሰዓት ተጀምሮ በተባለበት ሰዓት ማብቃቱ ፤ እዉነትም የጀርመናዉያኑን የሰዓት ማክበር በባህልን ወርሶአል ያሳኛል፤ የኑረንበርግ የኢትዮጵያዉያን ባህል ማኅበርን ልምድ መቅሰም ይገባል ሳንል ማለፍ አንሻም። ለዝግጅቱ መሳካት የተባበሩንን የማኅበሩን አባላት፤ የክብረ በዓሉን እድምተኞች በዶቼ ቬለ ስም በማመስገን ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

Nürnberg Äthiopischer Kulturverein Feier 25. Jahrestag der Gründung
ምስል DW/A. T. Hahn
Nürnberg Äthiopischer Kulturverein Feier 25. Jahrestag der Gründung
ምስል DW/A. T. Hahn
Nürnberg Äthiopischer Kulturverein Feier 25. Jahrestag der Gründung
ምስል DW/A. T. Hahn
Nürnberg Äthiopischer Kulturverein Feier 25. Jahrestag der Gründung
ምስል DW/A. T. Hahn
Nürnberg Äthiopischer Kulturverein Feier 25. Jahrestag der Gründung
ምስል DW/A. T. Hahn


ነጋሽ መሐመድ