1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእሳት አደጋ በርካታ ንብረት አወደመ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 3 2009

ዛሬ ጠዋት በአዲስ አበባ ለገሃር በቀድሞው ጉምሩክ ግቢ ውስጥ በሚገኝ የፌደራል ፖሊስ አባላት መኖሪያ ስፍራ ላይ በደረሰ ከፍተኛ የእሳት አደጋ እሰካሁን ግምቱ ያልታወቀ በርካታ ንብረት መውደሙን የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መቆጣጠርና መከላከል ባለስልጣን አስታወቀ፡፡ በአደጋው ፍንዳታዎች ይሰሙ እንደነበር የአይን እማኞች ገልጸዋል፡፡

https://p.dw.com/p/2eSdl
Brennende Streichhölzer
ምስል Bilderbox

የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መቆጣጠርና መከላከል ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለዶይቸ ቬለ እንደተናገሩት የእሳት አደጋ እንደተከሰተ ጥሪ የደረሳቸው ከጠዋቱ 2 ሰዓት ከ17 ደቂቃ ላይ ነው፡፡ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ እሳቱን ለማጥፋት 10 የእሳት አደጋ ማጥፊያ ተሸከርካሪዎችን፣ ሶስት ከፍተኛ ውሃ የመጫን አቅም ያላቸው ቦቴዎች እና 100 ገደማ የሚሆኑ የእሳት አደጋ ሰራተኞችን በፍጥነት ወደ ቦታው ማሰማራቱን ይገልጻሉ፡፡ “እንግዲህ ቦታው ላይ ስንደርስ የነበረው ሁኔታ ሶስት መጋዘኖች በውስጣቸው የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ ቁሳቁሶች ያሉበት ሙሉ በሙሉ በእሳት ተያይዘው ነበር፡፡ ስንደርስ ማድረግ የነበረብን በተለይ በሰው ላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ መቀነስ ነው፡፡ በዚህም የተሳካ ስራ ተሰርቶ በሰው ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰም፡፡ በግቢው ውስጥ ሌላ አገልግሎት የሚሰጡ ብሎኮች አሉና ወደዚያ ተዛምቶ አደጋ እንዳይደረስ ከፍተኛ የመከላከል ስራ ሰርተናል፡፡ በዚህም ከአምስት ሰዓት ተኩል ገደማ  እስከ ስድስት ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ እሳቱን ሙሉ ለሙሉ  ለመቆጣጠር ተችሏል፡፡”
አቶ ንጋቱ በሰው ላይ ጉዳት አልደረሰም ይበሉ እንጂ በቦታው የነበሩ ስማቸው እንዳይገለጽ የሚፈልጉ የአይን እማኝ አምቡላንሶች በተደጋጋሚ አደጋው ከደረሰበት ግቢ ሲወጡ መመልከታቸውን እና ቀላል ፍንዳታዎች መስማታቸውን ያስረዳሉ፡፡ እስከ ጠዋቱ ሶስት ሰዓት ድረስ በቦታው ላይ እንደነበሩ የሚናገሩት እኚህ የዓይን እማኝ በቦታው ላይ ሲደርሱ የተመለከቱትን እንዲህ ይገልጹታል፡፡  “በዚያ መንገድ ፖሊስ መንገዱን ዘጋግቶት ነበር፡፡ የእሳት አደጋ መኪና ግን ያልፋል፡፡ በጣም ብዙ ሰው ያይ ነበር፡፡ በተለይ የባቡሩ ማለፊያ ከፍ ያለ ስለነበር እዚያ ላይ ሆኖ በደንብ ይታይ ነበር፡፡ ከውስጥ አንድ ሶስት አይነት መጋዘን ቤቶች ነበሩ፡፡ ከእነዚያ ውስጥ አንዱ ሙሉ ለሙሉ በእሳት ተያይዞ ነበር፡፡ ከእርሱ አጠገብ የነበሩትን ብሎኮች ለማዳን ነበር ርብርብ ሲደረግ የነበረው፡፡ ምን እንደሆኑ እኔ መለየት የሚከብደኝ ትንንሽ ፍንዳታዎች ነበሩ፡፡ ይጮኹ ነበር፡፡ በጣም ጭሱ ያስፈራ ነበር፡፡ አምቡላንሶች ከዚያ ውስጥ የተጎዳ ሰው ይሁን ምን ይሁን ባላውቅም ይዘው ሲወጡ አይቻለሁ፡፡”
በማህበራዊ ድረ ገጽ የተለቀቁ ምስሎች እና ቪዲዮዎች የእሳት አደጋው ከፍተኛ እንደነበር እና ከቦታው የሚትጎለጎለው ጭስ ከርቀት አካባቢዎች ጭምር ይታይ እንደነበር አመላክተዋል፡፡ እሳት አደጋ ሲከሰት ፍንዳታ መሰማት የተለመደ መሆኑን የገለጹት አቶ ንጋቱ በዚህኛው ፍንዳታ የተለየ ሁኔታ መከሰቱን እንደማያውቁ ገልጸዋል፡፡ ፖሊስ የአደጋውን መንስኤ እና አጠቃላይ በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት እያጣራ ነው ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ተስፋለም ወልደየስ

ልደት አበበ