1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአፍሪቃ የሚጠበቀው የኤኮኖሚ ሂደት

ረቡዕ፣ ግንቦት 25 2002

በተጠናከረ ኤኮኖሚ ወደተሻለ ዘመን! ይህ በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ውስጥ የግማሽ አሠርተ-ዓመት ዕድገት የጠነሰሰው ተሥፋ ነበር።

https://p.dw.com/p/Nfrc
በአፍሪቃ የሚጠበቀው የኤኮኖሚ ሂደት
ምስል DW

ግን ዓለምን ያዳረሰው የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ሳይታሰብ ብቅ ማለቱ ነበር ችግሩ። በዚሁም የኤኮኖሚው ዕድገት በግማሽ ሲያቆለቁል ወደ ክፍለ-ዓለሚቱ የሚሻገረው ቀጥተኛ መዋዕለ-ነዋይም ሶሦውን ያህል ይቀንሳል። በኢንዱስትሪ ልማት የተራመዱት መንግሥታት ድርጅት ኦ.ኢ.ሲ.ዲ ባለፈው ሣምንት የያዝነውን 2010 ዓ.ም. የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ዕድገት ትንበያውን አቢጃን ላይ አቅርቦ ነበር። ጥናቱ ቀውሱ በአፍሪቃ ላይ የጣለው ተጽዕኖ ካልተወገደ ከባድ ፖለቲካዊና ማሕበራዊ ችግሮች ሊከተሉ እንደሚችሉ የሚያስጠነቅቅ ቢሆንም በሌላ በኩል ጥቂት የተሥፋ ጭላንጭል ማሳየቱም አልቀረም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስለ አፍሪቃ ኤኮኖሚ የወደፊት ዕርምጃ በተነሣ ቁጥር በተደጋጋሚ አበረታች ምሳሌ በመሆን የምትጠቀሰው ሩዋንዳ ናት። ባለፈው ሣምንት ይፋ በሆነው የ 2010 የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ዕድገት ትንበያም የሆነው ይሄው ነው። የአፍሪቃይቱን አገር የኤኮኖሚ ዕድገት እንደ ተዓምር እያነሱ በአድናቆት ከሚያወድሱት የምጣኔ-ሐብት ባለሙያዎች መካከል የአፍሪቃ ልማት ባንክ ባልደረባ ቪሊ ላይብፍሪትስም ይገኙበታል።

“ሩዋንዳ በዘጠናኛዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ አስከፊ በሆነ የእርስበርስ ጦርነትና የጅምላ ፍጅት ብትታመስም ዛሬ በዓለም ባንክ ዘንድ አንደኛ ደረጃ የሚሰጣት የለውጥ አገር ሆና ነው የምትቆጠረው። ይህ ደግሞ በአፍሪቃ ብቻ አይደለም። በዓለምአቀፍ ደረጃ ጭምር እንጂ!”

ሩዋንዳ ዛሬ የነዳጅ ዶላር የምታገኝበት ዘይት ባይኖራትም ሁልገብ ኤኮኖሚ እየገነባች በመምጣቷ ለብዙዎች የወደፊቱ ሞዴል ወይም አርአያ እየተባለች ነው። በአፍሪቃ ገንዘብ ያለው ነዳጅ ዘይት፣ አልማዝና መሰል ሃብት ወደ ውጭ መሸጥ የሚችል ብቻ ሆኖ ነው ለረጅም ጊዜያት ሲታይ የቆየው። እርግጥ የተፈጥሮ ሃብት መኖሩ ምናልባት የቀውሱን ተጽዕኖ ለማለዘብ ሳይረዳ አልቀረም። አለበለዚያ አንዳንድ ጠበብት እንደሚሉት የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ይብስ በደቀቀ ነበር። በሌላ በኩል ግን 31 በኢንዱስትሪ ልማት የተራመዱ ሃገራትን የሚጠቀልለው የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት የኦ.ኢ.ሲ.ዲ. የምርምር ዘርፍ ሃላፊ ሄልሙት ራይዘን እንደሚሉት የአንድ አገር አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት ከፍተኛ መሆን ሁሌም የድህነት ማቆልቆል ማለት አይደለም።

“አንጎላን ብንወስድ አጠቃላይ ብሄራዊ ምርቷ የሚለካው በተሳሳተ መንገድ ነው። ተሟጦ የሚያልቅ ጥሬ ሃብትን እያወጡ በከፍተኛ ዋጋ ለመሸጥ የሚወስኑ አገሮች ጥቅሙ ዘላቂ እንዳልሆነ ሊያውቁት ይገባል። እንግዲህ ይሄው ሃብት ከጠቅላላው ብሄራዊ ምርት ጋር ከታሰበ በኋላ እኛ ደግሞ ሃያና ሰላሣ በመቶ ጨምረን በማሰብ ነው የምናሳክረው”

አንጎላ ካለፈው 2009 ዓ.ም. የነዳጅ ዘይት ገበያ ውድቀት በፊት በዓለም ላይ በፈጣን መጠን የምታድገው አገር ነበረች። አጠር ካለ የኤኮኖሚ ችግር በኋላ በዚህ ዓመት መልሳ ከሰባት በመቶ በላይ እንደምታድግ ይጠበቃል። ሆኖም በሚሊያርድ የሚገኘው ገቢ አብዛኛውን በጥቂት የአገሪቱ መሪዎች ተሟጦ ነው የሚቀረው። ሃብት አገሪቱን ባለውና በሌለው ወገን ከፍሏል። ዋና ከተማይቱ ሉዋንዳ ዛሬ በዓለም ላይ ውድ ከሚባሉት አገሮች አንዷ ስትሆን በተመሳሳይ ጊዜ ሲሦው አንጎላዊ ረሃብተኛ ወይም በቂ ምግብ የማያገኝ ነው።

አፍሪቃ በጥሬ ሃብት ላይ ብቻ መተማመኗ ገና ከዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ በፊትም አስቸጋሪ የነበረ ጉዳይ ነው። ሆኖም ነገሩ በደህናው ወይም በምቹው ጊዜ ብዙም ትኩረት አልተሰጠውም። አሁን ግን የአፍሪቃው ልማት ባንክ ባልደረባ ቪሊ ላይብፍሪትስ እንደሚሉት አፍሪቃ በኤኮኖሚ ረገድ በአዲስ መንገድ መጓዛ ግድ ነው።

“ሁልገብ መሆን ያስፈልጋል። በአንድ ወገን በጥሬ ሃብት ብቻ መተማመን አይጠቅምም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ከጥሬ ሃብት የሚገኝ ገቢን በጥሩ ሁኔታ መልሶ በሥራ ላይ ማዋል ተገቢ ነው። ማለት፤ የግል ዘርፍን ለማነቃቃት፣ በትምሕርት ዘርፍ መዋዕለ-ነዋይን ለማሳደግና የተሻለ የመንግሥት አገልግሎት ለመስጠት፤ እንዲሁም ሙስናን ለመቀነስና ድህነትን በተሻለ መጠን ለመታገል የሚረዳ የኤኮኖሚ ለውጥ ያስፈልጋል”

ዛሬ ከዚሁ ሌላ ብዙ የአፍሪቃ አገሮች በልማት ዕርዳታ ላይ በጣሙን ጥገኞች ናቸው። እንደ ምሳሌ የምትጠቀሰው ሩዋንዳም ቢሆን 45 በመቶ በጀቷን የምታገኘው በቀጥታ ከዕርዳታ ነው። ስለዚህም ግብር መሰብሰብ ሁኔታውን ሊያሻሽል እንደሚችል ሃሣብ መንቀሳቀሱ አልቀረም። በጀርመን የልማት ተራድኦ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ባለሥልጣን በሃንስ ቮልኒይ አባባል የግብር ገንዘብ በአግባብ አለመሰብሰብ በአፍሪቃ ምናልባትም ትልቁ የኤኮኖሚ መሰናክል ሣይሆን አልቀረም።

ለምሳሌ ባለፈው ዓመት ዓለምአቀፉ የልማት ዕርዳታ 120 ሚሊያርድ ዶላር ገደማ ይጠጋ ነበር። ታዳያ በታዳጊ አገሮች ግብርን ሆን ብሎ ባለመክፈልና በማጭበርበር የሚባክነው ገንዘብ እጥፉን፤ ማለትም 250 ሚሊያርድ ዶላር እንደሚደርስ ይታመናል። ይህ እንግዲህ የግድ መለወጥ የሚኖርበት ጉዳይ ነው።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ