1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአፍጋኒስታን የዓለም ዓቀፉ ተልኮ ማብቂያ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 20 2007

የጎርጎሪዮሳዊዉ አዲስ አመት ሲጀምር አፍጋኒስታን ዉስጥ የ 13 ዓመት የዘለቀዉ ዓለም አቀፋዊ ወታደራዊ ተልኮ ያበቃል። ረዥሙ እና ብዙ ዋጋ የተከፈለበት የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት በምህፃሩ ኔቶ ተልኮን የሚገመግሙ፤ አንዳንዶች ስለ ስኬት ሌሎች ደግሞ ስለ ባከነ ተልኮ ይናገራሉ።

https://p.dw.com/p/1EAQs
Übergabe der Sicherheitsverantwortung in Südwest-Afghanistan
ምስል picture-alliance/dpa/MOD/Sergeant Obi Igbo

ዓለም አቀፋዊው ወታደራዊ ተልኮ በአፍጋኒስታን የጀመረው፤ የአልቃይዳ ቡድን በዩናይትድ ስቴትስ ላይ እጎአ መስከረም 11 ቀን2001 ዓም ጥቃት ከጣለ ጥቂት ወራት በኋላ ነው። ከአልቃይዳ መሪ ኦሳማ ቢን ላዲን ጋር በቅርበት ይሰራ የነበረው የታሊባን መንግሥት እንደወደቀ፤ በታህሳስ ወር ዓለም ዓቀፉ የአፍጋኒስታን የፀጥታ ኃይል ወታደሮቹን ወደ ካቡል ላከ። ኋላም የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት በምህፃሩ ኔቶ ተልኮውን ይመራ ጀመር። በወቅቱም ከ 50 ሀገራት የተውጣጡ 130 000 የሚደርሱ ወታደሮች ሂንዱኩሽ ውስጥ ሰፍረዉ ነበር። ረዥሙ እና ብዙ ዋጋ ከተከፈለበት ተልኮ ሲያበቃም፤ ተልኮው ስኬታማ ነበር ብሎ መጠየቁ የግድ ነው። የኔቶ ዋና ፀሀፊ ዬንስ ሽቶልንበርግ ዓላማችን ተሳክቷል ይላሉ።« ለመፈፀም ያቀድናቸዉን በጋራ ግልፅ በሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ኃላፊነት ፈፅመናል። ለዓለም አቀፍ አሸባሪዎች ተደላድለው የሚቀመጡበት ቦታ እንዳያገኙ አድርገናል፣ አፍጋኒስታንን ጠንካራ አድርገናል፣ በተጨማሪም የራሳችንን ሀገራት ከስጋት አድነናል።»

ባለፉት ዓመታት እውን ከሆኑት ነገሮች ጥቂቶቹ አፍጋኒስታን ውስጥ የአልቃይዳ የጦር ማሰልጠኛ ወድሟል። የቀድሞው የአልቃይዳ መሪ ኦሳማ ቢን ላድን እኢአ በግንቦት ወር 2011 ፓኪስታን ውስጥ ተገድለዋል፣ እንዲሁም አፍጋኒስታን ውስጥ በጤና እና በትምህርቱ ዘርፍ መሠረተ ልማቶች ተዘርግተዋል። ከዚህም ሌላ 350 000 ፓሊሶችን ያቀፈ የአፍጋኒስታን የጥበቃ ኃይል መቋቋሙ ይፋ ሆኗል። ይህ በእንዲህ እንዳለም የተለያዩ ሀገራት ወታደሮቻቸውን ከአፍጋኒስታን በማስወጣት ላይ ይገኛሉ። ይሁንና የአፍጋኒስታን የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሀሚድ ካርዛይ ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት እንደተናገሩት ፤ ሀገሪቷ አሁንም አታስተማምንም። የዓለም ዓቀፉ የአፍጋኒስታን የፀጥታ ኃይል ወታደሮችም ሀገሪቷን ሊለቁ ጥቂት ጊዜ ቀርቶዋቸውም አፍጋኒስታን ውስጥ በተደጋጋሚ ጥቃቶች መጣላቸው በየዕለቱ ማለት ይቻላል ተሰምቷል። የአፍጋኒስታን ጦርነት ገና አልተጠናቀቀም ይላሉ፤ የአፍጋኒስታን ምሁራን መድረክ ተባባሪ ዳሬክተር ቶማስ ሩቲግ፤ ከበርሊን ።«እቅዱ ታሊባን ከነበረ ወይም ፓሊባንን ማጥፋት ከነበረ፤ እቅዱ ተደናቅፏል። ጥቃቶች አሁንም በሀገሪቱ ጠቅላላው መድረሳቸዉ አልቆመም። አፍጋኒስታን ላይ ከ 2010 በኋላ የተጣሉት ጥቃቶች መጠን ከበፊቱ ጋር ሲነፃፀር ከፍ ብሏል። ያ ማለት ጦርነቱ ስር ሰዷል እንዲሁም በሁለቱ አካላት በኩል ተጧጡፏል። በዚህም የተነሳ የ2001 ወታደራዊ ያልሆኑ እቅዶች አልተሳኩም ማለት ነው።»

Ursula von der Leyen in Afghanistan
ምስል MACDOUGALL/AFP/Getty Images

በዓለም አቀፋዊው የአፍጋኒስታን ተልኮ ከ 3400 በላይ ወታደሮች ህይወታቸው ጠፍቷል። ከነዚህ መካከል 55ቱ ጀርመናውያን ነበሩ። የሰላም ማስከበሩን ኃላፊነት የአፍጋኒስታን ኃይል ከተረከበ አንስቶም የሚሞተው ወታደር ቁጥር ጨምሯል። ባለፉት 11 ወራት ብቻ 6000 የሚጠጉ የአፍጋኒስታን ፖሊሶች እና ወታደሮች መገደላቸው ተገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ በአፍጋኒስታን ሲቪል ማህበረሰብ ላይ በርካታ ጥቃት ደርሷል። ቁጥራቸው በ10 ሺ ይገመታል። እንደ ተባበሩት መንግሥታት ዘገባ እስካለፈው ወር የጎርጎረሲያዊው 2014 ዓም ብቻ 3188 ሲቪሎች ሲሞቱ 6429 ደግሞ ቆስለዋል። ለዚህ ሁሉ ሰለባ ምክንያት የሆነው ምዕራባዊያን የተጠቀሙት ስልት ነው ይላሉ ሩቲግ፤« እንደኔ አመለካከት የሲቪል እና ወታደራዊ ተልዕኮው መቀላቀሉ ለተልዕኮዉ መክሸፍ አንዱ ምክንያት ነው። በሁለቱ ተልዕኮዎች መካከል ያለው ልዩነት ግልፅ ስላልነበርም ታሊባን ሲቪሉን ተልዕኮ የሚያጠቃበት ሰበብ አግኝቷል። »

Bundeswehr Soldaten der Clausewitz-Kaserne in Burg Archiv 2011
ምስል picture-alliance/dpa/J. Wolf

ዓለም ዓቀፉ የአፍጋኒስታን የፀጥታ ኃይል ተልኮ በኋላ ታሊባን አካባቢዎችን መልሶ የመቆጣጠሩ ነገር ከጊዜ ጋር የሚታይ ይሆናል። የብዙዎች ስጋት ቀደም ሲል የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች ከኢራቅ በይፋ ሲወጡ ሀገሪቱ የገጠማት ትርምስ መልሶ በአፍጋኒስታንም እንዳይታይ ነው። ከዚህም ሌላ ኢራቅ ውስጥ አሁን የሚንቀሳቀሰው ራሱን «እስላማዊ መንግሥት» ሲል የሚጠራው አይነት አክራሪ ቡድን አፍጋኒስታን ውስጥም እንዳይመሰረት ያሰጋል።

ፍሪድል ታውበ

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ