1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የዩኤስ አሜሪካ ስጋት እና ጥሪ

ሰኞ፣ ነሐሴ 30 2008

ዩኤስ አሜሪካ በኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ላይ ተወሰዷል የምትለው ከመጠን ያለፈ የኃይል ርምጃ እንዳሳሰባት በተመድ የዩኤስ አምባሳደር ሳማንታ ፓወር መግለጻቸውን አሶሽየትድ ፕሬስ አስታወቀ።

https://p.dw.com/p/1Jw8w
Oromo Proteste in Äthiopien
ምስል Oromia Media Network

የተመድ ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት የልዑካን ቡድን በደቡብ ሱዳን ያካሄደውን ጉብኝት ባጠናቀቀበት ጊዜ አምባሳደር ሳማንታ ፓወር በመዲናይቱ ጁባ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ሁከቱን «እጅግ አስጊ» በማለት ግልጽ እና ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አሰምተዋል። ሰዎች በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞ ማካሄድ እንዲፈቅድላቸው ዩኤስ አሜሪካ የኢትዮጵያን መንግሥት መጠየቋን አምባሳደር ሳማንታ አክለው ገልጸዋል። ዜና ምንጩ ያወጣው ዜና እንዳመለከተው፣ በኢትዮጵያ ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ ሰፊ ነፃነት በመጠየቅ አደባባይ የወጡ ሰዎች ሕይወት የጠፋባቸው ተቃውሞዎች የተካሄዱ ሲሆን፣ በተቃዋሚዎች ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት የግድያ እና የድብደባ ተግባር ፈጽሞዋል፣ እንዲሁም፣ የኢንተርኔት አቅርቦትን አግዷል በሚል ወቀሳ ቀርቦበታል። በመዲናይቱ አዲስ አበባ የሚገኘው የአፍሪቃ ህብረት በኢትዮጵያ የተፈጠረው ያለመረጋጋት ሁኔታ እንዳሳሰበው ባለፈው ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ መግለጹን ያስታወሰው የአሶሽየትድ ፕሬስ ዘገባ፣ የደቡብ ሱዳን ጉብኝቱን ያበቃው የተመድ ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት የልዑካን ቡድን ከአፍሪቃ ህብረት ባለስልጣናት ጋር ለመወያየት ዛሬ ጉዞውን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

Samantha Power
ምስል Burton/Getty Images

ይህ በዚህ እንዳለ፣ በአዲስ አበባ የፖለቲካ እስረኞች በሚገኙበት ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግበት የቂሊንጦ ወህኒ ቤት ባለፈው ቅዳሜ በተነሳ ቃጠሎ ቢያንስ አንድ ሰው መሞቱን የኢትዮጵያ መንግሥት ዛሬ አስታውቋል። በቃጠሎው ሌሎች ስድስት ሰዎችም መቁሰላቸውን መንግሥት በሚቆጣጠረው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ድረ ገፅ የወጣው የመንግሥቱ መግለጫ አመልክቶዋል። የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ግን በእስር ቤቱ በደረሰው ቃጠሎ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ቢያንስ 20 መሆኑን ነው ያመለከቱት። የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እና ማህበራዊ ድረ ገፆች እንዳስታወቁት፣ ቃጠሎውን ተከትሎ በእስር ቤቱ ውስጥ ተኩስ ተሰምቶዋል። በቂሊንጦ ወህኒ ቤት ውስጥ በማዕከላይ ኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች በቀጠለው ተቃውሞ ሰበብዘ የተያዙ በርካታ እስረኞች ይገኛሉ። በመብት ተሟጋቹ ድርጅት፣ «ሂውመን ራይትስ ዎች» ግምት መሰረት፣ ካለፈው ህዳር ወር ወዲህ በኢትዮጵያ በቀጠለው ፀረ መንግሥት ተቃውሞ ከ400 የሚበልጡ ተቃዋሚዎች በፀጥታ ኃይላት ተገድለዋል።

አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ