1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ የሃሳብ ነፃነት ዉይይት በበርሊን

ረቡዕ፣ የካቲት 8 2009

የጀርመኑ የሰብዓዊ መብቶች ተቋም «በኢትዮጵያ ሃሳብን የመግለጽ መብት» በሚል ርዕስ በዛሬዉ ዕለት በጀርመን ሰዓት አቆጣጠር ከ11:30 ጀምሮ እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት ድረስ የሚዘልቅ የዉይይት መድረክ አዘጋጅቷል። በዚህ የዉይይት መድረክ ላይ ሁለት  የዞን ዘጠኝ የድረገጽ ጸሐፍት ስለሀገሪቱ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ይዞታ እንዲያስረዱ ተጋብዘዋል።

https://p.dw.com/p/2XbAg
Äthiopien Zone9 Blogger Gruppe
ምስል Zone9

Meinungsfreiheit in Äthiopien -Zone 9 - MP3-Stereo

ከተጋባዦቹ አንዱ ጆማኒክስ ካሳዬ እንደሚለው፣ እንዲህ ያሉት የዉይይት መድረኮችም በሀገር ዉስጥ ያሉት ድምፆች በታፈኑበት በዚህ ወቅት ያለዉን ነባራዊ እዉነታ ለዓለም ማሳየት ያስችላሉ።

«ዊ ብሎግ ቢኮዝ ዊ ኬር» «የምንጽፈዉ ስለሚያገባን ነዉ» የሚል መርህ ነዉ ያላቸዉ የዞን 9 የድረገጽ ጸሐፍት። የጀርመኑ የሰብዓዊ መብቶች ተቋም የድረገጽ ጸሐፍቱን ባስተዋወቀበት አጭር ጽሑፍ፤ «ዞን ዘጠኝ የሚለዉ ስያሜ ሃሳብን የመግለፅና የፖለቲካ ነፃነት የተገደበበትን ስፍራ በዘይቤ እንደሚያመላክት ነዉ የገለጸዉ።  ዞን ዘጠኞች ከ4 ዓመት በፊት ስድስቱ አባላት በመንግሥት ተይዘዉ ሲታሠሩ ሦስቱ ባልደረቦቻቸዉ በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገር በመዉጣታቸዉ ከወህኒ አምልጠዋል። ከእነዚህ አንዱ ጆማኒክስ ካሳዬ ነዉ። ሕገ መንግሥቱ የሰጣቸዉን ሃሳብን የመግለፅ መብት በመጠቀም በፌስ ቡክ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ በዞን ዘጠኝ ስም የሚጽፏቸዉ ጽሑፎች ሕገ መንግሥቱን አርቅቆ ባጸደቀዉ መንግሥት አለመወደዳቸዉ ብዙሃኑን ለእስር ቀሪዎቹን ለስደት መዳረጉን ይናገራል ጆማኒክስ። ኢትዮጵያ ዉስጥ ሃሳብን መግለፅ አስፈሪ ተደርጓል ባይ ነዉ።

አያይዞም በአሁኑ ሰዓት በሀገሪቱ ጋዜጠኞችም ሆኑ የድረገጽ ጸሐፍት ሃሳባቸዉን በተደነገገዉ ሕግ መሠረት የመግለጽ ድፍረቱ እንዳይኖራቸዉ ተጋርጦባቸዋል ያለዉን እንዲህ ይገልጻል።

ጆማኒክስ ካሳዬ ምን እንኳን እርሱ ከመታሰር ቢያመልጥም በዉጭ ሆኖ በሌሎች ባልደረቦቹ ላይ የደረሰና የሚደርሰዉን መከታተሉ ሲረብሸዉ እንደከረመ ሳይገልፅ አላለፈም። በዛሬዉ የበርሊኑ የኢትዮጵያን ሃሳብን የመግለፅ መብት ይዞታ በሚመለከት በሚካሄደዉ ዉይይትም አሁንም እስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች እና የፖለቲካ እስረኞችን ጉዳይ በሰፊዉ ለማንሳትና ለማሳየት መዘጋጀቱን አመልክቷል።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ