1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ የተባባሰው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት

ሐሙስ፣ ነሐሴ 28 2007

ኢትዮጵያ ዉስጥ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት መመዝገቡ ተገለፀ። « ዘ ስታር» የተሰኘዉ ድረ ገፅ ይፋ እንዳደረገዉ በሐምሌ ወር ብቻ የዋጋ ግሽበቱ 14,7 በመቶ ተመዝግቧል። በደቡባዊና በምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራት የጋራ ገበያ «ኮሜሳ» ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ከተመዘገበባቸዉ ሃገራት ኢትዮጵያን በሶስተኛ ደረጃ ነዉ የተቀመጠችዉ።

https://p.dw.com/p/1GQmc
Blick aus meinem Fenster Addis Abeba Äthiopien
ምስል Solomon Mengist

[No title]

በኢትዮጵያ ዉስጥ የተከሰተዉ የዋጋ ንረት በአንድ ጊዜ የመጣ ጉዳይ አይደለም የሚሉት የኤኮኖሚ ጉዳይ አዋቂዉ አቶ ሙሼ ሰሙ፤ አንዱ ምክንያት ኢትዮጵያ ዉስጥ ከፍተኛ የሆነ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዉ አለመጣጠን ነዉ ይላሉ።
« የዋጋ ዉድንነት ኢትዮጵያ ዉስጥ የመከሰቱ ጉዳይ የአንድ ጊዜ ችግር ዉጤት አይደለም፤ ለበርካታ ዘመናት ሲከታተል የመጣ ጉዳይ ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ በአጭር ጊዜ ዉስጥ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ተካሂደዋል። በእነዚህ መሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ምክንያት የሀገሪቱ ኃብት ወይም የገንዘብ ዝዉዉር ጨምሮአል። ከዚህ በፊት በኤኮኖሚ ዉስጥ ያልነበረ ማኅበረሰብ በመግዛት አቅም መጥቆአል። እነዚህ ነገሮች በአንድ በኩል በገንቢነት ሊታዩ ይችላሉ፤ ነገር ግን ተመጣጣኝ በሆነ ደረጃ አቅርቦቱ እያደገ ባለመጣጠኑ ሀገሪቱ ዉስጥ እየተሰራጨ ያለዉ ገንዘብ አቅም፤ በሀገሪቱ ዉስጥ እየገባ ያለዉ የገንዘብ መጠን አቅርቦቱን መሸከም የማይችልበት ደረጃ መድረሱ ነዉ፤ ችግር የፈጠረዉ።»

"Mercato-Markt" in Addis Abeba, Äthiopien
ምስል picture alliance/kpa


እንደ አቶ ሙሼ ሰሙ፤ አገላለጽ ከሆነ ኢትዮጵያ ዉስጥ በትንሽ አቅርቦት ከፍተኛ የሆነ የመግዛት አቅም ተፈጥሮአል። ይህ ኃይል ግን ስርዓትና ሕግን የተከተለ ባለመሆኑ ለከፍተኛ ግሽበቱ መከሰት ምክንያት መሆኑንና፤ ቋሚ የሚባል ገቢ ያለዉ ማኅበረሰብ የኑሮ ዉድነቱን መቋቋም እንዳቃተዉ ተናግረዋል «ኢትዮጵያዉስጥ እጅግ በማይታመን ደረጃ፤ ለዛዉም መንግሥት የሚሰጠዉ ስታትስቲክስ ዓመታዊ ስለሆነ የሚታየዉ ከዓመት በኋላ የነበረዉ ግሽበት ላይ የተጨመረዉን ልዩነት ነዉ። ኢትዮጵያ የሠራተኛ ደምወዝ ማደግ ከጀመረ ቋሚ ገቢ ያለዉ ማኅበረሰብ ደሞዝ ማደግ ከጀመረ፤ ከስድስት ዓመት በላይ አልፎታል።ወደ ኋላ ተመልሰን ያለዉን ግአት ብናይ ከሁለት መቶ ፐርሰንት በላይ ነዉ»
ይህ የዋጋ ግሽበት እንዴት ሊስተካከል ይቻላል? ሙሼ ሰሙ፤
« አንደኛ ኤኮነሚዉ ከሚገባዉ በላይ ግሎአል። መንግሥት የሚያየዉ ሀገሪቱ ዉስጥ እየሰራ ያለዉ መሰረተ ልማት ለፖለቲካ የሚያመጣለትን ግብዓት ብቻ ነዉ። አንዳንዱ መሰረተ ልማትን ስንመለከተዉ በአጭር ጊዜ ዉስጥ የወጣበትን ወጭ መመለስ ወይም እሴት መፍቸት የማይችል ስለሆነ ሊዘገይ ሊራዘም ወይm ደግሞ ለሚቀጥለዉ ጊዜ ሊታይ የሚችሉ ነገሮች ናቸዉ። እነዚህ ላይ ትኩረት መሰጠት አለበት። ለዉድድር የሚደረጉ ነገሮች በሙሉ ኤኮኖሚዉ ላይ የሚያሳድሩትን ተፅኖ ከግምት ዉስጥ አስገብቶ ማረም ያስፈልጋል። ሁለተኛዉ በፕሮጀክት የሚያዙ ነገሮች በአግባቡ በጊዜዉ እና በወቅቱ ስለማይጠናቀቁ ከፍተኛ የሆነ ወጭ የማኅበረሰቡ ጫና ሆነዋል። »

"Mercato-Markt" in Addis Abeba, Äthiopien
ምስል picture alliance/kpa

እንደ « ዘ ስታር» እንደተሰኘዉ ድረ ገፅ ኢትዮጵያ 26.6 ግሽበት ካስመዘገበችው ማላዊና 17.4 በመቶ ግሽበት ካስመዘገበችው ሱዳን ቀጥላ በሶስተኝነት 14.7 በመቶ የዋጋ ግሽበት ያስመዘገበች አገርናት። በደቡባዊና በምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራት የጋራ ገበያ «ኮሜሳ» አነስተኛ ግሽበት ከተመዘገበባቸዉ የአፍሪቃ ሀገሮች መካከል ደግሞ ዲሞክራቲክ ኮንጎ አንዷ ናት።


አዜብ ታደሰ


ሸዋዬ ለገሰ