1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በካሜሩን ያገረሸው ቀውስ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 8 2009

በካሜሩን በሰሜን ምዕራብ እና ደቡብ ምዕራብ በሚገኙት ሁለቱ አካባቢዎች ግጭት እንደገና ተከሰተ። በዚሁ አካባቢ የሚኖሩት እንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪዎቹ ውሁዳኑ የሀገሪቱ ዜጎች በመንግሥት አንጻር ያደረባቸውን ቁጣ አጉልቷል።

https://p.dw.com/p/2UQWr
Karte Infografik Cameroon Region Bandenda ENG

ባለፈው ሳምንት በሰሜን ምዕራብ የካሜሩን ግዛት ዋና ከተማ ባሜንዳ ባካሄዱት ተቃውሞ ወቅት የካሜሩንን ባንዲራ አቃጥለው የራሳቸውን ባንዴራ ሰቅለዋል በሰቀሉበት ወቅት ከፖሊስ ጋር በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ ሁለት ሰዎች ተገድለዋል፣ እንደ ባለስልጣናት ገለጻ።   ተቃዋሚዎች  አራት ሰው መሞቱን እና ብዙዎች መቁሰላቸውን ነው የተናገሩት። 
ከካሜሩን አስር ግዛቶች መካከል ስምንቱ ፈረንሳይኛ ቋንቋ፣ ሁለቱ ደግሞ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው። ከካሜሩን 22 ,5 ሚልዮን ሕዝብ መካካልም አንድ አምስተኛውን ብቻ  የሚሸፍኑት እንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪዎቹ በሀገሪቱ እንደ ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ እንደሚታዩ እና ከ1982 ዓም ወዲህ በስልጣን ላይ በሚገኘቱት ፕሬዚደንት ፖል ቢያ መንግሥት አድልዎ እንደሚደረግባቸው  በማስታወቅ ተቃውሞ ከጀመሩ ሰንብቷል። በ83 ዓመቱ የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ፖል ቢያ መንግሥት እና በብዙኃኑ  ፈረንሳይኛ ቋንቋ  ተናጋሪዎች አድልዎ እንደሚደረግባቸው፣ ሀገሪቱ በተፈጥሮ ሀብት ብትታደልም፣ ሀብቱ በግዛቶቹ መካከል እኩል አለመከፋፈሉን በማስታወቅ ተቃውሞ ማሰማታቸውን ቀጥለዋል።  በዚሁ ጊዜ ፕሬዚደንት ፖል ቢያ ተቃዋሚዎቹን እንዲያነጋግሩ ጠቅላይ ሚንስትራቸውን ፊልሞን ያንግን ወዳካባቢው ቢልኩም፣ ተቃዋሚዎች ጠቅላይ ሚንስትሩ  ተልዕኳቸውን እንዲያከናውኑ ለማከላከል ባደረጉት ተቃውሞ  ሁከት በመፈጠሩ፣ መንግሥት ባካባቢው ወደ 5000 ወታደሮች አሰማርቶዋል። በሰሞኑ ግጭት መደብራቸውን ያጡት የ45 ዓመቱ ነጋዴ  መንግሥት የችግሩአሳሳቢነት እንዲገነዘበው ጠይቀዋል።
« መንግሥት ግልጽ ውይይት ማካሄድ ይኖርበታል። ለእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪዎቹም ችግር በቀና መንፈስ መፍትሔ ሊያስገኝለት ይገባል። »

Soldat Kamerun Maschinengewehr West Afrika
ምስል picture-alliance/dpa/T.Graham

የሰሞኑ ግጭት እና ሁከት የተቀሰቀሰው በነዚህ ሁለት አካባቢዎች በመጀመሪያ ጠበቆች፣ ቀጥለውም አስተማሪዎች የስራ ማቆም አድማ ካደረጉ በኋላ ነው። አካባቢዎቹ የሚከተሉት የፍትሕ እና የትምህርት ስርዓት የተለያየ መሆኑ እየታወቀ፣ መንግሥት ባካባቢያቸው ፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ የህግ ባለሙያዎችን እና አስተማሪዎችን በብዛት እያሰማራ ነው በሚል ቅሬታቸውን ገልጸዋል። ምንም እንኳን ፈረንሳይኛ እና እንግሊዝኛ የሀገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋዎች ቢሆኑም፣ የመንግሥት መግለጫዎች በሚሰጡበት፣ አውደ ጥናት ወይም  ስብሰባ  በሚደረግበት ጊዜ ለእንግሊዝኛ ተናጋሪዎቹ በቂ ጽሁፍ እንደማይቀርብ በማስታወቅ ድርጊቱን አውግዘዋል። የካሜሩን ፕሬዚደንት ፖል ቢያ  ቀውሱ እየከፋ እንዳይሄድ ከፈለጉ የሕዝቡ ብሶት ምን መሆኑን ከራሱ ከቅሬታ አቅራቢው ለመስመት ቢሞክሩ መልካም እንደሚሆን ነው በጡረታ የሚገኙ መምህር አቺዲ ሄንሪ አሳስበዋል።
«  ፕሬዚደንቱ አንድ የልዑካን ቡድን ብቻ መላክ የለባቸውም። ወደ አካባቢው ፣ ወደ ባሜንዳ መሄድ ካልቻሉ የስራ ማቆም አድማ የጀመሩትን በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ሊያነጋግሩዋቸው ይገባል። ራሳቸው የተቆጣውን ሕዝብ ሊያረጋጉ ይችላሉ። ባለስልጣናቸውን መላክ ግን ችግሩን ሊፈታ የማይችል የተሳሰተ ዘዴ ነው። »

Kamerun Präsident Paul Biya
ፕሬዚደንት ፖል ቢያ ምስል imago/Xinhua Afrika

አንዳንድ አክራሪዎች በሰሜን ምዕራብ ግዛት እና በደቡብ ምዕራብ ግዛት በቀጠለው ተቃውሞ እና አድማ ወቅት ካለፉት 22 ዓመታት ወዲህ የሚሰማውን አንድ ነፃ የደቡባዊ ካሜሩን መንግሥት እንዲቋቋም ሲጠይቁ ተሰምተዋል፣ ለዘብተኛ የሚባሉት ያካባቢው ዜጎች ግን እጎአ ከ1961 እስከ 1972 ዓም  የተሰራበት ዓይነቱ ፌዴራል ስርዓት እንዲመለስ ፍላጎታቸውን አጉልተዋል። እንደሚታወሰው፣ በ1972 ዓም ነበር የሀገሪቱ የመጀመሪያ ፕሬዚደንት አሃማዱ አሂጆ እንግሊዝኛ እና ፈረንሳኛ ተናጋሪዎቹን ግዛቶች በማዋሃድ የካሜሩን ሬፓብሊክን ያቋቋሙት።
የካሜሩን ፕሬዚደንት ፖል ቢያ አሁን እንደገና ስላገረሸው ሁከት ቀውስ እስካሁን በይፋ እቋማቸውን ባይገልጹም፣ የፌዴራል ስርዓት እንዲመለስ የሚለው ጥያቄ በፍጹም ተቀባይነት እንደማያገኝ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ፊልሞን ያንግ እና ሌሎች የካሜሩን ባለስልጣናት ከወዲሁ በግልጽ አስታውቀዋል።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ