1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዓለም የሚታዩ ስጋቶች

ረቡዕ፣ ኅዳር 8 2008

የጎርጎሪዮሳዊዉ 2015ዓ,ም በዓለም የሚታዩ ስጋቶች መዘርዝር የርሃብና የአደጋዎችን ግንኙነት ያመለክታል። በርካታ የእርዳታ ድርጅቶችም በየትኛዉ የዓለም ክፍል ይህ ስጋት በአደገኛ ሁኔታ ብሶ እንደሚታይ እያመለከቱ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1H8Yg
Kenia Afrika Arid Turkana Dürre
ምስል Andrew Wasike

[No title]

ዘገባዉ የሚቀርበዉ ከሰባት የሚልቁ የጀርመን የእርዳታ ድርጅቶች የታቀፉበት የጀርመን የልማት ድርጅቶች ጥምረት በጀርመንኛዉ ቡንዲኒስ ኢንትቪክሉንግስ ሂልፈ ነዉ። የልማት ድርጅቶች ጥምረቱ ላለፉት አምስት ዓመታት በዓለም የሚታዩ ስጋቶችን ዘገባ ሲያቀርብ ቆይቷል። ዘንድሮም በተለይ ርሃብ እና እልቂት እየተፈራረቁ ያደረሱትን ችግር ለማሳየት ሞክሯል።

በጎርጎሪዮሳዊዉ 2015,ም ነሐሴ ወር ማለትም ባለፈዉ ነሐሴ በመላዉ ዓለም በሚገኘዉ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ዉስጥ ለሚገኙ ተሰዳጆች በመጠኑ እንኳ የሚበቃ ምግብ አልነበረም። ለዚህም ነዉ የእርዳታ ድርጅቶች በርሊን ላይ በተጠቀሰዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት በመላዉ ዓለም የሚታዩ ስጋቶች ዘገባ ትኩረት እንዲያገኝ ጥረት ያደረጉት። የጀርመን የርዳታ ድርጅቶች ጥምረት ዋና ዳይሬክተር ፔተር ሙክ የእርዳታዉ ርብርብ አደጋ በደረሰባቸዉ ስፍራዎች ብቻ ሳይሆን ቀዉስ ባለባቸዉ አካባቢዎች እና በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎችም አፋጣኝ የምግብ አቅርቦት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

Bangladesch Überschwemmung
ምስል Getty Images/AFP

«ባለፈዉ የጎርጎርዮሳዊ 2015 ነሐሴ ወር በአብዛኞቹ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ከአስፈላጊዉ የምግብ አቅርቦት ግማሽ ያህሉ እንኳን አልነበረም። ቀዉስ በተባባሰባቸዉ አካባቢዎች እና በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች የተሻለ የምግብ አቅርቦት እንዲኖር ማድረግ፤ አደጋ በደሰባቸዉ አካባቢዎች እርዳታ ማድረስና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነዉ።»

በነባቤ ቃል ደረጃ በአሁኑ ወቅት በዓለም ለአንድ ሰዉ የሚያስፈልገዉን ያህል ኪሎ ካሎሪ የሚያሟላ የምግብ ምርት ይመረታል። ችግሩ ግን ክፍፍሉ ፍትሀዊ አለመሆኑ እና፤ በምርት ስብሰባዉ እና ማጓጓዝ ሂደት የሚባክንና የሚጠፋዉ መበርከቱ ነዉ። አብዛኛዉ በርሃብ የሚጠቃዉ ኅብረተሰብ የሚኖረዉ በገጠር አካባቢ ነዉ። በገጠር አካባቢ የግንኙነት ሰንሰለት ባለባቸዉ ሃገራት አንድ ችግር ሲከሰት በመጀመሪያዉ ቀን አስፈላጊ የምግብ አቅርቦትን የማግኘት ዕድል አላቸዉ። ይህን ለማሻሻልም የልማት መርሆ ሊሆን ከሚገባዉ አንዱ፤ የገጠሩን አካባቢ ማዕከል በማድረግ እንዲህ ያለዉን ቀዉስ መከላከል እንደሚቻል መረዳት መሆን እንደሚኖርበት ሚዜሪዮር የተሰኘዉ ግብረሰናይ ድርጅት የቦርድ አባል ዶክተር ማርቲን ብሩይክልማን ዚሞን ያሳስባሉ።

Kenia Afrika Arid Turkana
ምስል Andrew Wasike

«የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት FAO የምርመራ ዉጤት ረሀብና ድህነትን ለመቀነስ በግብርና ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ በሌሎች ዘርፎች ላይ ከሚደረገዉ አምስት እጅ እጥፍ ዉጤታማ መሆኑን አመልክቷል። በተለይም ደግሞ ከሰሀራ በስተደቡብ የሚገኙ የአፍሪቃ አካባቢዎች ላይ ይህ ከተደረገ በ11 እጅ እጥፍ ዉጤት ሊያሳይ ይችላል።»

በዘንድሮዉ በዓለም የሚታዩ ስጋቶች ዘገባ ተመራማሪዎች በምግብ ዋስትና እና በአደጋ ስጋቶች መካከል ያለዉን ግንኙነት ለማሳየት ሞክረዋል። እንደተመራማሪዎቹ በአንድ ሀገር የመሬት መንቀጥቀጥ፤ የእሳተ ጎሞራ ፍንዳታ፣ ወይም ድርቅ እና ጎርፍ ቢከሰት ሀገሪቱ ያላት የምግብ አቅርቦት እንዲዛባ በማድረግ የረሀብ አደጋ ስጋቱ ከፍ እንዲል ያደርጋል። የምግብ ዋስትና ማጣት ሰዎች እንዲሰደዱ ከማድረጉም በላይ፤ ሰለባዎቹ ለእልቂት የመዳረጋቸዉን ስጋትም እንደሚጨምር አመልክተዋል። ተሰዳጆቹ በእንግድነት በሚሄዱባቸዉ የሚሰፍሩባቸዉ ቦታዎች ለተለያየ የተፈጥሮ አደጋ የተጋለጠ መሆኑንም ዘገባዉ ጠቁሟል። የምግብ ዋስትናን ለማረጋግጥ አፋጣኝ ርምጃ መዉሰድ አለባቸዉ ካላቸዉ ሃገራት መካከል ባንግላዴሽ፣ ሃይቲ፣ ሴኔጋል፣ ዚምባዌ እንዲሁም ቻድ ይገኙበታል።

Brasilien Giftige Schlammlawine nach Dammbruch in Bergwerk
ምስል Imago/Xinhua

ከዚህም ሌላ ተመራማሪዎቹ የተፈጥሮ ማስጠንቂያዎች እና ማኅበራዊ አካባቢዎችን ያካተቱ 28 መመዘኛዎችን መሠረት በማድረግ በ171 ሃገራት ዉስጥ ያለዉን የአደጋ ስጋቶች ቃኝተዋል። በዚህ መሠረትም ለአምስተኛ ጊዜ የደሴት ሀገሯ ቫኑቱ፣ ቶንጋ፣ ፊሊፒንስ፣ ጓቲማላ፣ ባንግላዴሽ፣ ኮስታ ሪካ እና ካምቦዲያን አስከትላ ለአደጋ ከተጋለጡ ሃገራት ግንባር ቀደም ሆናለች። እነዚህ 15 የሚሆኑ እጅግ ለአደጋ ስጋት የተጋለጡ መሆናቸዉ የተገለጸ ሃገራት አብዛኞቹ ደሴት ወይም በባህር ዳርቻ የሚገኙ ናቸዉ። አንዳንዶቹን ሃገራትም ተመራማሪዎቹ የባህሩ ከፍታ ምን ያህል እንደሚያሰጋቸዉ ለማሳየት በቀላል አቀገላለፅ ዉኃ እስከአንገታቸዉ ያጠለቃቸዉ መሆናቸዉን አስተድተዋል።

በርንት ግሮይስለር/ ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ