1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በየመን ጦርነት የታገቱት ኢትዮጵያውያን

ማክሰኞ፣ መጋቢት 26 2009

በጦርነት በሚታመሰው የየመን እና ሳዑዲ-አረቢያ ድንበር አቅራቢያ በርካታ ኢትዮጵያውያን መውጫ አጥተው መታገታቸውን ገለጡ። በአካባቢው በተከፈተ የተኩስ ልውውጥ በርካታ ኢትዮጵያውያን መሞታቸውንም ተናግረዋል። 

https://p.dw.com/p/2agJk
Infografik Karte Yemen Front Lines 2015 englisch

M M T/ Ethiopians stranded in war torn Yemen - MP3-Stereo

ሰናይት መብራኽቱ ከውቅሮ ተነስታ በጦርነት ወደምትናወጠው የመን ለመድረስ የፈጀባት ሁለት ሳምንት ብቻ ነው።  ከትውልድ ቀዬዋ ተነስታ እስከ ሶማሌላንድ እስክትደርስ መንገድ የመሯት ባሕርም የያሻገሯት ኢትዮጵያውያን ደላሎች ናቸው።  በምላሹ ሰናይት እየተቀባበሉ ቀይ ባሕርን ላሻገሯት ሶስት የሰዎች ደላሎች ወደ 22,000 ብር ከፍላለች። የመንን አቋርጣ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ልትሻገር ያቀደችው ሰናይት የጠበቃት ግን የከፋ ጦርነት ነበር። በሳዑዲ አረቢያ እና የመን መካከል በሚገኘው ራጎ የተሰኘ አነስተኛ መንደር ከ4,000-5,000 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንደሚገኙ ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የዓይን እማኞች ይናገራሉ። የየመን ሑቲ አማፅያን እና የሳዑዲ አረቢያ ጦር በሚያደርጉት የተኩስ ልውውጥ ከ15-20 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን መገደላቸውን አብዱመሐመድ ተናግሯል።
እንደ ሰናይት መብራኽቱ ሁሉ ከውቅሮ ተነስቶ የመን የገባው ዳንኤል አብርሃ ራጎ በተሰኘችው መንደር ከሁለት ሳምንት እስከ ስድስት ወር የቆዩ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ታዝቧል። በአካባቢው በሥራ ላይ የተሰማሩ እንዲሁም ድንበር አቋርጠው ለተሻለ ሥራ ፍለጋ ወደ ሳዑዲ ለመዝለቅ የሚያልሙም በራጎ ይገኛሉ። በራጎ ላለፉት ስድስት ወራት የቆየው አቡሽ ግደይ የውቅሮ ልጅ ነው። የሑቲ አማፅያን እና በሳዑዲ አረቢያ መራሹ የአገራት ጥምረት መካከል የሚደረገው ፍልሚያ ሲበረታ ኢትዮጵያውያኑ በየጥሻው ለመሸሸግ መገደዳቸውን የሚናገረው አቡሽ ከአካባቢው ለመውጣት መቸገራቸውን ይገልጣል።
በዚህ ዘገባ ላይ በሳዑዲ አረቢያ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስተያየት ለማካተት ያደረግንው ጥረት አልተሳካም። 


እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ