1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዩናይትድ ስቴትስ የተጠናከረዉ ተቃዉሞ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 6 2007

ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ በተከታታይ መሣሪያ ያልያዙ ጥቁሮች በነጭ ፖሊሶች መገደላቸዉ ያስነሳዉ ተቃዉሞ እንደቀጠለ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1E4Q6
USA Protest Rassismus Polizeigewalt
ምስል Reuters/Stephen Lam

ባሳለፍነዉ ሳምንት መጨረሻ በሺዎች የሚገመቱ ዜጎች በተለያዩ የሀገሪቱ ግዛቶች ለተቃዉሞ አደባባይ ወጥተዋል። በአስር ሺዎች የተገመቱ ደግሞ ከተለያዩ ግዛቶች ወደዋሽንግተን ዲሲ በመጓዝ በኋይትሃዉስ ፊት ለፊት የተቃዉሞ ድምፃቸዉን አሰምተዋል።

ከመንትያ እህቷ ጋ ለተቃዉሞ ወደዋሽንግተን የመጣችዉ በፍትህ ሥርዓቱ መበላሸት የተሰማት ንዴት ያልበረደዉ ጃሬት ግራማዛ «ረዳት የማጣት» ስሜት እንደተሰማቸዉ ነዉ የምትናገረዉ። በአንድ ዓመት ዉስጥ እነዚህ ሁሉ ጥቁር ወጣቶች በነጭ ፖሊስ መገደላቸዉ የፍትህ መዛባት ነዉ ስትልም ትተቻለች። እንደእህቷ ጆይስ እምነት ደግሞ ለዚህ ዋና መዘዙም ዘረኝነትና ዘረኝነት ነዉ።

«ዘረኝነት ነዉ ዋናዉ ምክንያት ይህ ምንም አያጠያይቅም። ለዚህ ሁሉ ጭካኔ ማዕከሉ ዘረኝነት ለመሆኑ ምንም ጥያቄ አይኖርም። እናም ይህ መለወጥ ይኖርበታል። በወጣቱ ትዉልድ ይህ እየተለወጠ ነዉ ነገር ግን መግደል እንዲቀጥል የሚፈቅዱት ሰዎች አሁንም ስልጣኑ አላቸዉ። ያ ግን መቀጠል አይኖርበትም አሁኑ መቀየር አለበት።»

USA Protest Rassismus Polizeigewalt
ምስል Reuters/Stephen Lam

የእሷን ዓይነት አመለካከት ካላቸዉ 52 ሰዎች ጋ ከሴራኪዩስ ወደኒዮርክ የተጓዘችዉ ፍትህ ጠያቂ እኩለ ለሊት እንዳለፈ ነዉ አዉቶቡስ ተሳፍራ ጉዞዋን የጀመረችዉ። ከእነሱ ጋም ባለፈዉ ነሐሴ ወር ፈርገሰን ሚዙሪ ዉስጥ በነጭ ፖሊስ የተገደለዉ አፍሪቃ አሜሪካዊ ማይክል ብራዉን ቤተዘመዶችም ይገኛሉ። ከወራት ቆይታ በኋላ የአካባቢዉ ፍርድ ሸንጎ ያልታጠቀዉን ታዳጊ ጥቁር አሜሪካዊ የገደለዉ ነጩ ፖሊስ ዳረል ዊልሰን መከሰስ የለበትም ማለቱ በፈርገሰን አመፅ የቀላቀለ ተቃዉሞ ማስነሳቱ ይታወሳል። ተቃዉሞዉም በመላ ሀገሪቱ መዳረሱ እየታየ ነዉ። አመፁና ተቃዉሞዉ ከዜጎች እንቢተኝነት ሳይሆን ፍትህ ከማጣት የመነጨ መሆኑን ነዉ ከተሰላፊዎቹ አንዱ የሚያስረዱት፤

«የራሳችን መንግሥት አመፅ እየፈፀመ ለእኔም ሆነ ለሌላ ሰዉ እንዴት አመፅ አያስፈልግም ብሎ መናገር ይቻላል? መንግሥታችን ሰዉ አልባ አዉሮፕላን ይጠቀማል፤ ሰዎችን ያስራል፤ እናም ሰላማዊ በሆነ መንግሥት ላይ አይደለም አመፀኛ ሆነን የተገኘነዉ አመፁ የመጣዉ ሊጨቁነን በሚሞክር ኃይል ላይ ነዉ። እና ሰዎችን በአደባባይ በሚገድሉ ሰዎች ፊት ሰላማዊ እንድሆን ይጠበቃል? የተገደለዉ ወንድሜ ሊሆን ይችላል፤ እህቴ ልትሆን ትችላለች፤ ከማዉቃቸዉ ሰዎች አንዱ ሊሆን ይችላል፤ እኔም ራሴ ልሆን እችላለሁ።»

USA Proteste gegen Polizeigewalt in New York Demonstranten
ምስል Reuters/S. Lam

የሰልፉ አስተባባሪዎች አምስት ሺህ ሰዎች ገደማ ዋሽንግተን ላይ ለሰልፍ እንደሚወጡ ነበር የጠበቁት፤ አደባባይ የተገኘዉ ሕዝብ ግን እነሱ ከገመቱት በላይ ነዉ። ቆየት ብለዉ እንደገለጹትም 25ሺህ ገደማ ሕዝብ «የጥቁሮች ሕይወትም ትርጉም አለዉ» የሚል መፈክር አንግቦ ጎዳና ላይ ወጥቷል። «መተንፈስ አልቻልኩም» ሲል እየጮኸም አንገቱን በፈርጣማ ክንድ ተጨምቆ የተገደለዉን ኤርክ ጋርነርን ሲዘክር ዉሏል። ለሰለፍ አደባባይ የወጣዉ ሕዝብ እድሜ እና የማንነት የጀርባ ታሪኩ አላገደዉም፣ ተሰላፊዉም ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ሲሆን ጥያቄዉም አንድ ነዉ፤ በጥቁሮች ላይ የሚፈጸመዉ ጥቃት ይቁም፣ ለተበደሉ ፍትህ እና የፖሊስ አሰራር ይስተካከል የሚል። በሳምንቱ መጨረሻ አደባባይ ከወጡት አንዷ ይህን ሁሉ አመፅ የቀሰቀሰዉ ሙስና የተጠናወተዉ የፍርድ ሸንጎዉ ዉሳኔ መለወጥ አለበት ባይ ናቸዉ፤

«ምን እናድርግ? በአዉቶብስ ተጭነን ድምፃችን እንዲሰማና ከመላዉ ሕዝብ ጎን ለመቆም ወደዚህ መጥተናል። የፍትህ ሚኒስቴር የፍርድ ሸንጎዉን ዉሳኔ እንዲሽር ነዉ የምንፈልገዉ፤ በሙስና የተተበተቡ ነበሩ።»

USA Protest Rassismus Polizeigewalt
ምስል Reuters/Deanna Dent

የእሷን ስሜት ዋሽንግተን፣ ቦስተን፣ ቺካጎ፣ አዉስቲን፣ ሳንፍራንሲስኮም ሆነ በሌሎች የዩናይትድ ስቴትስ ከተሞች በሳምንቱ ማለቂያ አደባባይ የወጡ ዜጎች በሙሉ ይጋሩታል። ጉዳዩ ለተቃዉሞ ሰልፍ በወጡት ወገኖች ብቻ የተወሰነ ሳይሆን የመብት ተሟጋቾች እና ምሁራን በየደረጃዉ የሚከራከሩበትና የሚነጋገሩበት ርዕስ ሆኗል፤ ዩናይትድ ስቴትስ ከዚህ ሁሉ ዘመን በኋላ ከጥቁር ነጭ የቀለም አድሎ አልተላቀቀችም ወይ? በዩኒቨርስቲዎች የሚገኙ የሕግ ባለሙያዎች በእርግጥ ሕጉ የቀለም አድሎ አድርጓል ወይ እያነጋገራቸዉ ነዉ። በሌላ በኩል ፖሊስና የአሜሪካን ባለስልጣናት የዩናይትድ ስቴትስን የሕግ ስርዓት ተአማኒነት ዳግም ለማምጣት ፖሊስ የተሻለ ስልጠና ይሰጠዉ፣ እንቅስቃሴያቸዉን የሚቀርፅ ካሜራ በሰዉነታቸዉ ላይ ይዘዉ ይንቀሳቀሱ እና የፍርድ ሸንጎዎችን የፍትህ ሂደት መቀየር ያስፈልጋል በሚሉ ጉዳዮች ላይ እየተነጋገሩ ዉሳኔም እያሳለፉ ነዉ።

ጌሮ ሽሊስ /ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ