1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በደቡብ ሱዳን የህፃናት መብት ጥሰት

ማክሰኞ፣ ሰኔ 23 2007

በደቡብ ሱዳን የሰዓብዊ መብት ጥሰት በእጅጉ ተባብሶ መቀጠሉን የተመድ አስታወቀ። በሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት ይዞታን የመረመረው በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮ ዛሬ ባወጣው ዘገባ የደቡብ ሱዳን ጦር ሴቶችና ልጃገረዶችን ደፍሮ በህይወት እንዲቃጠሉ ማድረጉን አጋልጧል።

https://p.dw.com/p/1Fqsr
Symbolbild Frauen Opfer Konflikt Südsudan
ምስል GetttyImages/AFP/C. Lomodon

[No title]

የተመ የህፃናት ጉዳይ መርጃ ድርጅት በምህፃሩ UNICEF ከጥቂት ሳምንታት በፊት ይፋ እንዳደረገው ደግሞ በደቡብ ሱዳን በተለይ በህፃናት ላይ የሚፈፀመውም በደል እጅግ ተባብሷል።

በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግስታት ተልዕኮ ስር በተካሄደው የደቡብ ሱዳን ሰብዓዊ መብቶች ይዞታ ምርመራ ዘገባ መሠረት ደቡብ ሱዳን ውስጥ የመንግስት ኃይሎች በአማጽያን ላይ በቅርቡ ባካሄዱት ዘመቻ የተፈፀመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት መጠነ ሰፊ ነው። ጦሩ በተለይ በዩኒቲ ግዛትዋ በማዮም ወረዳ ባለፈው ጥር በከፈተው ጥቃት ሰለማዊ ሰዎች መገደላቸውን መንደሮችም መውደማቸውንና ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች ከቀየቸው መፈናቀላቸውን ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች ተናግረዋል። 115 የጥቃት ሰለባዎችን እንዲሁም የዐይን ምስክሮችን በማነጋገር አጥኝዎቹ ባወጡት ዘገባ ጦር ኃይሉ ሴቶችና ልጃገረዶችን መድፈሩንና ቁም ስቅል ማሳየቱን ጠቁመዋል። እንደዘገባው ከተደፈሩት መካከል አንዳንዶቹ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ እንዲቃጠሉ ተደርጓል። ሌሎች ደግሞ ተተኩሶባቸው ተገድለዋል። ከአንድ ወር በፊት የተመድ የህፃናት ጉዳይ መርጃ ድርጅት UNICEF ባወጣው ዘገባ ደግሞ በደቡብ ሱዳን ህፃናት ከመጠን ያለፈ በደል ይደርስባቸዋል። ዶቼቬለ ያነጋገራቸው የUNICEF ቃል አቀባይ ክሪስቶፍ ቡሉአራክ በደቡብ ሱዳን ህፃናት የሚገኙበት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል።
«ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በህጻናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች እጅግ እየተባባሱ ሄደዋል። በህጻናት ላይ ከዚህ ቀደም ያልታዩ ጭካኔ የተሞላባቸው ጥቃቶች ይደርሳሉ። ደቡብ ሱዳን የምትገኝበት ሁኔታ ትኩረት እንዲሰጠው ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ጥሪ አስተላልፈናል። እኛም በሃገሪቱ ስንቀሳቀስ ብዙ ፈተናዎች እንደሚገጥሙን ና ህዝቡ በተለይም ለጥቃት የተጋለጡ ህጻናት የሚገኙበት ሁኔታ አስቸጋሪ መሆኑን አስረድተናል።»
UNICEF እንደሚለው በደቡብ ሱዳን በህፃናት ላይ ከሚፈፀሙ ወንጀሎች መካከል አስገድዶ መድፈር ና ማኮላሸት ይገኙበታል። ቃል አቀባዩ እንዳሉት በደቡብ ሱዳን ህፃናት የከፋ ችግር ውስጥ የሚገኙት ጦርነቱ በተባባሰባቸው በዩኒቲ፣ በብሉናይል ፣ እንዲሁም በጆንግሌ ግዛቶች ነው። በሀገሪቱ ምኑንም የማያውቁ ህፃናትን ለውትድርና በመመልመል በከፋው የርስ በርስ ጦርነት እንዲካፈሉ መደረጉም ከቀድሞው አሁን እየባሰ ሄዷል። ቃል አቀባይ ቡሉአራክ በአሁኑ ጊዜ ደቡብ ሱዳን ውስጥ 13 ሺህ ህጻናት በተለያዩ የደቡብ ሱዳን ኃይሎች ተመልምለው በውጊያ መሰማራታቸውን አስታውቀዋል። እንደ ቃል አቀባዩ ድርጅታቸው ዓለም ዓቀፍ ድንጋጌዎችን በመጣስ በደቡብ ሱዳን በልጆች ላይ የሚፈመው ወንጀል እንዲቆም ጠይቋል።
«እኛ የመንግስት ኃይሎችም ሆኑ አማፅያን ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግን የሚፃረሩት እነዚህ እጅጅግ አሰቃቂ የሆኑ ጥቃቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ጠይቀናል። ከታህሳስ 2006 ዓም በፊት ጥሩ ውጤቶችን አይተን ነበር። በዚያን ጊዜ ኮብራ የሚባለው አንጃ በውትድርና ያሰማራቸውን 1700 ህፃናት ለቆ ነበር። ሆኖም አሁን በህፃናት ላይ የሚፈፀመው ጥቃትም ሆነ ህጻናትን ለውትድርና መመልመሉ እየተባባሰ ነው የሄደው። »
ዩኒሴፍ እንደሚለው ጦርነት ተባብሶ በቀጠለባት በደቡብ ሱዳን ስር በሰደደ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ከ250 ሺህ የሚበልጡ ህፃናት ተጎድተዋል። ከ400 ሺህ በላይ ህጻናት ትምህርት ቤት መሄድ አልቻሉም። በቀጠለው ጦርነት ምክንያት ለውትድርና የሚመለመሉትም ህጻናት ቁጥርም እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው። ለነዚህ ችግርች መፍትሄው በሀገሪቱ በተቻለ ፍጥነት ሰላም የሚወርድበትን መንገድ መፈለግ መሆኑን ዩኒሴፍ አሳስቧል።

Südsudan Soldaten Rückeroberung Blue Nile Raffinerie
ምስል picture-alliance/AA
Symbolbild Frauen Opfer Konflikt Südsudan
ምስል GetttyImages/AFP/C. Lomodon

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ