1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዳርፉር ያገረሸው ውጊያ

ቅዳሜ፣ የካቲት 5 2008

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2003 ዓም ወዲህ በጦርነት፣ በኃይሉ ተግባር እና በረሀብ በተጎዳው የሱዳን ምዕራባዊ ግዛት ዳርፉር በመንግሥት ጦር እና ለሰፊ ራስ ገዝ አስተዳደር በሚታገሉት ዓማፅያን መካከል ከአንድ ወር ገደማ ወዲህ እንዳዲስ የፈነዳው ውጊያ አሳሳቢ የሰብዓዊ ቀውስ እንዳያስከትል ማስጋቱ ተገለጸ።

https://p.dw.com/p/1Hub4
Südsudan Flüchtlingscamp Flüchtlinge in Yida
ምስል Getty Images/AFP/A. G. Farran

[No title]

ወደ 1,5 ሚልዮን ሕዝብ በ60 መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ በሚኖርበት በዳርፉር ማዕከል በሚገኘው በጀቤል ማራ አካባቢ ሰሞኑን በተነሳው ውጊያ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ መፈናቀላቸውን በዚያ የሚገኘው የተመድ አስቸኳይ እርዳታ አስተባባሪ መስሪያ ቤት፣ በምህፃሩ «ኦቻ» ቃል አቀባይ ሳማንታ ኒውፖርት አስታውቀዋል።

« ሰዎቹ ከኃይሉ ተግባር ለመራቅ ሲሉ ወደሁሉ አቅጣጫዎች ሸሽተዋል። በርግጠኝነት የምናውቀው ከ38,000 የሚበልጡ ሰዎች ወደ ሰሜን ዳርፉር እንደሸሹ ነው። ለነዚህ ሰዎች አስፈላጊውን አገዝ እና አስቸኳዩን ርዳታ ማቅረብ ጀምረናል። »

Darfur Munition in Nyala
ምስል Getty Images/AFP/A. Shazly

ከነዚሁ ተፈናቃዮች መካከል 90% ሴቶች እና ህፃናት ሲሆኑ፣ በሶርቶኒ በሚገኘው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ ሰፈር አካባቢ ተጠለዋል። ሌሎች ቁጥራቸው በውል ያልታወቁም ወደ ማዕከላይ ዳርፉር ሳይሸሹ እንዳልቀሩ እና ይህም ተፈናቃዮቹን የመርዳቱን ሁኔታ አዳጋች እንዳደረገው ኒውፖርት አመልክተዋል።

« ሁኔታው ግልጽ አይደለም። በማዕከላይ ዳርፉር ወዳሉት አካባቢዎች መግባት አልቻልንም። በተለያዩ ቦታዎች የተፈናቀሉ ሰዎች እንዳሉ እና ቁጥራቸውም ከ500 እስከ 50,000 ሊደርስ እንደሚችል የተለያየ መረጃዎች ደርሶናል። ስለዚህ፣ አንድ ቡድን ወደዚያ ተልኮ፣ ሁኔታውን ፣ ብሎም፣ ሰዎቹ ምን እንደሚያስፈልጋቸው ማጣራት እና አስፈላጊውን ምላሽ መስጠት ፈልገን ነበር። »

ይሁንና፣ ይኸው ጥረታቸው ያካባቢው ባለስልጣናት ባለመፍቀዳቸው ሊሳካ አልቻለም ይላሉ ኒውፖርት።

Marina Peter vom Sudan Focal Point
ምስል Marina Peter

የዳርፉርን ውዝግብ ከ2003 ዓም ወዲህ በቅርብ የ «ሱዳን ፎረም» የተባለው የፖለቲካ ተቋም ሊቀመንበር ጀርመናዊት ማሪና ፔተር በወቅቱ በዳርፉር ለሚካሄደው ውጊያ መንስዔው ከ13 ዓመት በፊት ከነበረው እንደማይለይ አስረድተዋል።

« የውዝግቡ መንስዔ ከሞላ ጎደል ለማለት ይቻላል የተፈጥሮ ሀብት ክፍፍል ጉዳይ ነው። ከዚህም ጎን በጎሳዎች መካከል ባለፉት ዓመታት የተፈጠሩት ግጭቶች ይጠቀሳሉ። ውዝግቡ አሁን ለተባባሰበት በዳርፉር በብዛት የሚካሄደው፣ ብዙውም፣ በሕገ ወጥ መንገድ የሚከናወነው የወርቅ ንግድ ምክንያት ሆኖዋል።

በዚህም የተነሳ ውጊያ እና የሕዝቡ መፈናቀል አሁን እንደገና ማገርሸቱ ማሪና ፔተርን ብዙም አላስገረመም። የሰላም ድርድር ሊጀመር ሲል እንደሚታየው ሁሉ ዳርፉር ውስጥ በ2010 ዓም የሱዳን መንግሥት እና ዓማፅያኑ በዶሀ፣ ቃታር የተኩስ አቁም ደንብ በተፈራረሙበት ጊዜ ውጊያው ለጥቂት ጊዜ ጋብ ቢልም፣ ጨርሶ እንዳላቆመ ነው ፔተር ያስረዱት። ላካባቢው እስከዛሬ ዘላቂ ሰላም ማውረድ ላልተቻለበት ሁኔታ በዚያን ጊዜው ድርድር ዋነኞቹ ያማፅያን ቡድኖች ያልተሳተፉበት ድርጊት እንደ ምክንያት ይጠቀሳል።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ