1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጀርመን ቀኝ ፅንፈኞች እየተጠናከሩ ይሆን?

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 8 2007

በደቡብ ጀርመን ኑርንበርግ ከተማ አቅራቢያ ለስደተኞች በተሰናዱ መጠለያዎች ላይ ቃጠሎ ከደረሰ በኋላ ፤ ቃጠሎውም ሆን ተብሎ እንደደረሰ የሚጠቁሙ የፅንፈኞች ምልክቶች በመገኘታቸው ፖሊስ ምርመራውን አጠናቅሯል።

https://p.dw.com/p/1E4am
Brandanschlag in Vorra bei Nürnberg 12.12.2014
ምስል Reuters/M. Dalder

ይህ በእንዲህ እንዳለ በተለያዩ ከተሞች ዘረኝነትን የሚቃወሙ እና የሚደግፉ ሰልፎች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ። ከጦርነት፣ ከኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ሸሽተው በርካታ ስደተኞች ባለፉት ወራት ወደ አውሮፓ ተሰደዋል። ጀርመን ብቻ ከ 25 000 በላይ የሶርያ ስደተኞችን መዝግባለች። በአጠቃላይ የውጭ ሀገር ዜጎች እንብዛም በማይስተዋሉባቸው የጀርመን ከተሞች ፤ ተገን የሚጠይቁ ስደተኞች ተትረፍርፈዋል። ሰሞኑን ጀርመን ውስጥ ቮራበተባለች፤ ኑርንበርግ ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው መንደር በበርካታ የመኖሪያ ህንፃዎች ላይ የደረሰው ቃጠሎ አንዳንድ ጀርመናውያንን የውጭ ሀገር ዜጎች ወደ ሀገራቸው መምጣታቸው እንዳስቆጣቸው ያንፀባርቃል። ቃጠሎ የደረሰባቸው ለስደተኞች የተሰናዱመጠለያዎች አቅራቢያ በሚገኝ ግድግዳ ላይ በትልቁ « ምንም አይነት ስደተኞች አንፈልግም » የሚሉ እና ናዚዎች የሚጠቀሙት የመስቀል ምስል እንዲሁም ሌሎች በውጭ ዜጎች ላይ ጥላቻን የሚያንፀባርቁ ፁሁፎች ተነበዋል። ስለሆነም ፖሊስ በመጀመሪያ ደረጃ እያጣራ ያለው ቃጠሎው በቀኝ ፅንፈኞች ስለመፈፀሙ ነው።

ቃጠሎው የደረሰው በሶስት ለስደተኞች በተሰናዱ ህንፃዎች ላይ ሲሆን ባዶ ቆመው የነበሩት ህንፃዎች ታድሰው የከተማው አስተዳድር ስደተኞችን እስኪያስገባባቸው ነበር የሚጠብቁት። ለዓርብ ዕለት አጥቢያ ግን 150 የእሳት አደጋ ሰራተኞች ያጠፉት እሳት፤ እንደ ፖሊስ ዘገባ 700 000 ዩሮ የሚደርስ ንብረት አውድሟል። ይህ ብቻ አይደለም፤ ጀርመን ለውጭ ዜጎች ያላትን አቀባበል ጥያቄ ውስጥ ከቷል።

Brandanschlag in Vorra bei Nürnberg 12.12.2014
በውጭ ዜጎች ላይ ጥላቻን የሚያንፀባርቁ ፁሁፎችምስል picture-alliance/dpa/ToMa

የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የደረሰውን ቃጠሎ በማውገዝ እያንዳንዱ፣ ወደ ጀርመን የሚመጣ እና ተገን የሚጠይቅ ሰው፤ በህጉ መሠረት በአግባቡ አቀባበል ሊደረግለት እንደሚገባ ከቃጠሎው በኋላ ሲያሳስቡ በተለያዩ ከተሞች ዘረኝነትን የሚቃወሙ ሰልፎች ደግሞ አደባባይ በመውጣት ተቃውሞዋቸውን ገልፀዋል። እሁድ ዕለት ቮራ ውስጥ ቁጥራቸው ወደ ሦስት መቶ የሚጠጉ ሠልፈኞች እጅ ለእጅ ተያይዘው በእሳት የወደመውን ህንጻ በመክበብ ዘረኝነት እና የቀኝ አክራሪነትን ለመቃወም ድምፃቸውን ሲያሰሙ 15 000 የሚጠጉ ደግሞ በቦን አቅራቢያ በምትገኘው የኮሎኝ ከተማ እንዲሁ ተቃውሞዋቸውን አሰምተዋል። በበርሊን እና በቦን ከተማ እንዲሁ የተቃውሞ ሰልፎች ሰኞ ዕለት ተካሂደዋል።ስለ ቀኝ አክራሪዎች እንቅስቃሴ የሚያጠኑት ሀንስ-ግርድ ያሽከ ከዚህ ቃጠሎ በኋላ አውሮፓ ውስጥ እስልምና እንዳይስፋፋ የሚታገሉ አርበኞች ያበረታቷቸው ተቃውሞዎች እንዳይኪያሄዱ ያስጠነቅቃሉ፤« ኑርንበርጉ የተከናወነውን ፤ቅርብ ጊዜ በጀርመን ታሪክ ከተከሰተው ጋር አነፃፅረን ልንመለከተው እንችላለን። ከ 1990 እስከ 1993 ድረስ ከሮስቶክ ፣ ዞሊንግን እና ሌሎች ከተሞች ጥቃቶች ተፈፅመዋል። የነዚህን ጥቃቶች ለየት የሚያደርገው፤ ጥቃት አድራሾቹ ማህበረሰቡ እንደሚያበረታታቸው ይሰማቸው ነበር። ይህ አሁን እየተከናወነ ወዳለው ብናስተላልፈው ፤ ፔጊዳ የሚባሉት እስልምና እንዳይስፋፋ የሚታገሉት የአውሮፓ አርበኞች እንዳደረጉት አይነት አመፅ እንዳይካሄድ ያሰጋል። እና የቀኝ አክራሪ ወጣት እና ጎልማሶች ሁኔታውን ተቆጣጥረው ጥቃት ሊፈፅሙ ይችላሉ።»

በአሁኑ ወቅት በጀርመን ከተሞች የተለያዩ የተቃውሞ ሰልፎች ይካሄዳሉ። የቀኝ ፅንፈኞችን የሚያወግዙ፣ በዓለም ላይ በተለየያዩ አክራሪ ሙስሊም ቡድናት የሚፈፀሙትን ጥቃቶች ተመርኩዘው እስልምና በአውሮፓ እንዳይስፋፋ የሚያስጠነቅቁ እንዲሁም ቀኝ ፅንፈኞች አደባባይ ይወጣሉ። ኑርንበርግ የክርስቲያን ሶሻል ሕብረት ፓርቲ በምሕፃሩ CSU በሚመራው የባየርን የጀርመን ግዛት የምትገኝ ከተማ ናት። ፓርቲው በወግ አጥባቂነቱ ይታወቃል።የፓርቲው ወግ አጥባቂ መሆኑ የቀኝ ፅንፈኞችን ለጥቃት ያበረታታ ይሆን። በትክክል ይላሉ ስለ ቀኝ አክራሪዎች እንቅስቃሴ የሚያጠኑት ያሽከ ፤ « ይህ ትክክል ነው። በCSU በኩል፣ የውጭ ሀገር ተሽከርካሪዎች ግብር እንዲከፍሉ፣ ጀርመን የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች እቤታቸውም ጀርመንኛ መናገር አለባቸው የሚሉ የፖለቲካ አቋማቸው ስደተኞችን ወይም መጤዎችን በቀና የሚቀበል አይደለም። ሌላው እስልምና እንዳይስፋፋ የሚታገሉት የአውሮፓ አርበኞች ያደረጉት ሰልፍ እንደሚያፋፍም አመላካች ነው። አደባባይ የወጡትን የተቆጡ ማህበረሰቦች እንበላቸው፤ በመካከለኛው ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች ናቸው፤ ከነዚህ ውስጥ ጥቃት አድራሾች ሊወጣባቸው ይችላል።

Demonstration gegen Rechtsradikale in Köln
ቀኝ ፅንፈኞችን የሚቃወሙ ሰልፈኞችምስል picture-alliance/dpa/M. Simaitis

እንደ ያሽከ እስልምና በአውሮፓ እንዳይስፋፋ የሚያስጠነቅቁት፤ የግድ የቀኝ ፅንፈኞች ወይም ናዚዎች ብቻ አይደሉም። የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ከሚመሩት የክርስቲያን ዴሞክራቲክ ሕብረት ፓርቲ እና ከሌላው የዚህ እህት ፓርቲ CSU የተውጣጡ ሰዎች ሊሆኑም ይችላሉ። እንደዛም ሆኖ ከጀርመን የናዢ ታሪክ በኋላ የቀኝ ፅንፈኞች እንዴት አሁን ድረስ እንደዚህ ጠንካራ ሊሆኑ ቻሉ? « በ90ዎቹ ሮስቶል፣ ሆየርስቬርደ፤ዞሊንገን ከተሞች በርካታ መፈታት የነበረባቸው የቀኝ ፅንፈኛነት ድርጊቶች ነበሩ። ነገር ግን እነዚህ ጉዳዮች መስከረም 1 ቀን በተፈፀመው የአልቃይዳ ምክንያት ችላ ተብለዋል። ከዛን ጊዜ አንስቶ ሁሉን ነገር የተቆጣጠረው የሙስሊም አማፂያን ጉዳይ ነው። የቀኝ ፅንፈኞች ጉዳይ ያለአግባብ ተዘንግተዋል። እግዚያብሔር ይመስገን ምርጫን በተመለከተ ግን የቀኝ ፅንፈኞች እስካሁን አልቀናቸውም። »

Mekonnen Shiferaw Geschäftsführer Babel e.V.
የባብል ኤ ፋው ድርጅት መሥራች እና ስራ አስኪያጅ ዶክተር መኮንን ሽፈራው፤ምስል DW/Y. Hinz

በጀርመን ዘረኝነትን በመታገል የሚንቀሳቀሰው ባብል ኤ ፋው የተባለው ድርጅት መሥራች እና ስራ አስኪያጅ ዶክተር መኮንን ሽፈራው፤ የመኖሪያ ህንፃዎቹን ቃጠሎ እና በአጠቃላይ በጀርመን የቀኝ ፅንፈኝነትን በአሁኑ ሰዓት እንዴት እንደሚገመግሙት ከዚህ በታች በድምፅ ያገኙታል።

ልደት አበበ

ነጋሽ መሐመድ