1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጃፓን ያልታረቀዉ ያለፈ የጦርነት ታሪክ ተቃርኖ

ሰኞ፣ ነሐሴ 11 2007

የሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ካከተመ ከበርካታ አስርት ዓመታት በኋላ ጃፓን ዛሬም በጎረቤቶቿ መከሰሷ አልቆመም። ቻይና እና ደቡብ ኮሪያ ጃፓን የያኔ የጦርነት ሚናዋን ከልብ አልተቀበለችም፤ አልተፀፀተችምም በማለት ይከሳሉ።

https://p.dw.com/p/1GGsq
Japan Shinzo Abe Ansprache im Kabinett
ምስል Reuters/T. Hanai

[No title]

ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ከጦርነቱ በኋላ የተዘጋጀዉን ጦርነትና አመፅን የሚያወግዘዉን የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት ብሔራዊነትን እንዲያንፀባርቅ አድርገዉ ለመተርጎም ያደረጉት ሙከራም አልረዳም። በተመሳሳይ ያሳለፈችዉን ከልምዷ ለማካፈል የሞከረችዉ ጀርመን በበኩሏ ጃፓን ብቻ ሳትሆን ጎረቤቶቿም ያለፈዉን ትተዉ ተማምኖ ለመኖር የየበኩላቸዉን ማድረግ እንዳለባቸዉ መክራለች።

ቻይና ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ያከተመበትን 70ኛ ዓመት ብዙም አጀብ ሳታበዛ አስባዉ ነዉ ያለፈችዉ። በተቃራኒዉ ግን በመጪዉ መስከረም ወር የቻይና ሕዝብ የጃፓንን ወራሪ ጦር የተከላከለበትን የድል ቀን በታላቅ ወታደራዊ ሰልፍ ለማክበር ሽርጉድ እያለች ነዉ። ፕሬዝደንት ሺ ዢንፒንግ የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤን በሥርዓቱ ላይ እንዲገኙ መጋበዛቸዉ ተሰምቷል። ሆኖም ግን ወታደራዊ ሰልፎች በሚስተናገዱበት የድል በዓል ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አቤ መገኘት መቻል አለመቻላቸዉ ግልፅ አይደለም። ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ በዩናይትድ ስቴትስ የሰብዓዊ መብቶችና የጋዜጠኝነት ፕሮፌሰር የሆኑት የበርካታ መጽሃፍት ደራሲ ኢያን ቡሩማ የሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በሚመለከት ጃፓን የተከፋፈለ አመለካከት ሲኖራቸዉ ጀርመኖች ግን ከኒዮ ናዚዎች በቀር አንድ አቋም መያዛቸዉን ይናገራሉ። እርግጥም ጃፓንና ጀርመን ሲወዳደሩ፤ በወቅቱ ጃፓን ዉስጥ ሂትለርን አከል መሪ፤ ወይም የናዚ ፓርቲ አልነበረም። እንደዉም የጃፓን ዘዉዳዊ አገዛዝ እስያ ዉስጥ ከነበረዉ ከምዕራባዉያን ጋር ተዋግቷል። ቻይናና ደቡብ ምሥራቅ እስያ ዉስጥ ጃፓን የፈፀመችዉ የጭካኔ ድርጊት አሰቃቂ ቢሆንም ጀርመን ዉስጥ እንደተካሄደዉ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ግን አልነበረም። የጃፓን ወታደሮች በርካታ ንፁሃንን የገደሉት ምናባዊ በሆነ ምክንያት አንድን ዘር አጥፍቶ ቁጥሩን ለመቀነስ አይደለም። የጀርመን ናዚ አገዛዝ በአዉሮጳ ለተካሄደዉ ጦርነት ተጠያቂ ሲሆን ጃፓን ደግሞ ወታደራዊ ጡንቻዋን በማጠናከር ነዉ። ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ማግስት በጎርጎሪዮሳዊዉ 1946ዓ,ም አሜሪካኖች ወታደራዊ ኃይል መጠቀምን የሚያወግዘዉን የጃፓንን ሕገ መንግሥት ፃፉላቸዉ። ጃፓናዉያን የግራ ፖለቲከኞች ይህ ሀገሪቱ በጦር ወንጀል ለተጫወተችዉ ሚና ተገቢ ክፍያ ነዉ ብለዉ ያምናሉ። ይህ ሕገ መንግሥት እንዲሻሻል የሚሹት ብሔርተኞቹ ጃፓኖች በበኩላቸዉ የተፈፀመ የተለየ መጥፎ ነገር አልነበረም ወይም በጦርነቱ የጃፓን የተለየ የሚባል ድርሻም የለም በማለት ይሟገታሉ። ለጃፓን በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወቅት የነበራትን ሚና ተቀብሎ ከጎረቤቶቿ ጋር ተስማምቶና ተማምኖ መኖሩ የከበዳት ይመስላል። ይህ ምን ያህል ለዉጥ እንደሚያስገኝላት አሁን መገመት ባይቻልም ጠቅላይ ሚኒስትር አቤ ጦርነቱ ያከተመበትን 70ኛ ዓመት ምክንያት አድርገዉ በወቅቱ ጃፓን ለፈፀመችዉ ጥፋት እንደተፀፀተች የሚገልፅ መግለጫ ለማዉጣት ማሰባቸዉ እየተነገረ ነዉ። ባለፈዉ መጋቢት ወር ጃፓንን የጎበኙት መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልም የጀርመንን ያለፈ ታሪክ በማስታወስ ከልምዳቸዉ ለማካፈል ሳይሞክሩ አልቀሩም። ጎረቤቶቿ ቻይናና ደቡብ ኮርያም ቢሆኑ ወደልባዊ እርቅና መተማመን ለመምጣት ያለፈዉን ቂም ለመርሳት የበኩላቸዉን ማድረግ እንደሚገባቸዉም አሳስበዋል። በጦርነቱ ማግስት የተከፋፈለችዉ ጀርመን ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ተዋህዳ የደረሰችበትን ስኬት በራሳቸዉ ሃገርም ለማስመዝገብ ያቀዱት ጠቅላይ ሚኒስትር አቤ ሕገመንግሥቱ እንዲከለስም ሃሳብ አቅርበዋል። ይህ እቅዳቸዉንም ቀደም ብለዉ ባለፈዉ ሚያዚያ ወር ነዉ በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ተገኝተዉ ባደረጉት ንግግር እንዲህ ጠቁመዉ ነበር።

Japan Militär Soldaten Armee Shinzo Abe
ምስል Getty Images/AFP/T. Yamanaka
Japan Gedenkzeremonie 70. Jahrestag Atombombenabwurf Hiroshima
ምስል Getty Images/AFP/K. Nogi

«ጃፓን ዉስጥ ለደህንነታችን መሠረት የሚሆን ሕጋዊ አግባቦችን ለማስተካከል ጠንክረን እየሠራን ነዉ። ለማንኛዉም ደረጃ ለሚገኙ ቀዉሶጥ ጃፓን ይበልጥ ተመጣጣኝ ምላሾችን ለመስጠት ትችላለች። እነዚህ የተጠናከሩ ሕጋዊ መሠረቶች በዩናይትድ ስቴትስ ጦር እና በጃፓን መከላከያ ኃይል መካከል ያለዉን ትብብር የበለጠ አጠንክረዉ፤ አንድነታቸዉንም ተጨባጭ በማድረግ ለአካባቢዉ ሰላም አስተማማኝ ርምጃዎች ይሆናሉ። ይህ ማሻሻያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረግ እና ከጦርነቱ በፊት የነበረዉን ታሪክ የሚያፀዳ ነዉ። በመጪዉ የበጋ ወራት ይህን ከግብ እናደርሳለን።»

Japan Proteste Abstimmung Sicherheitsgesetz
ምስል Reuters/I. Kato

እሳቸዉ ይህን ይበሉ እንጂ የምክር ቤታቸዉን ሙሉ በሙሉ ይሁንታ አላገኙም። ከምንም በላይ የጃፓን ጦር ከሀገሩ ዉጭም ለግዳጅ እንዲሰለፍ የሚፈቅደዉ ሕግ ከፍተኛ ተቃዉሞ ነዉ የገጠመዉ። ተቃዋሚዎቻቸዉ በዚህ ጉዳይ ላይ ድምጽ ሲሰጥ «ሕግ ተጣሰ» የሚሉ መፈክሮቻቸዉን ምክር ቤት ዉስጥ ከፍ አድርገው ነዉ ያሳዩት። በአንፃሩ የቻይናን ወታደራዊ ድንፋታ ለማስከን ይረዳል የሚሉ ወገኖች አቤ ተገቢዉን ርምጃ በተገቢዉ ሰዓት መዉሰዳቸዉን ያደንቃሉ። የሕገ መንግሥት ባለሙያ ያሱኦ ሃሰበ ግን የጃፓን ደህንነት እርግጠኛ ስጋት ካለበት እና ከተደፈረ፤ መንግሥት ሊወስድ የሚገባቸዉ ርምጃዎች ቢኖሩም የጃፓን መንግሥት አሜሪካን ጦሯን ባሰማራችበት ወታደሮቼን አሰልፌ ድጋፍ አገኛለሁ ብሎ አስቦ ከሆነ ግን ከምኞት አይዘልም ነዉ የሚሉት።

ማርቲን ፍሪትስ/ ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ