1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፍተሻውን የሚያደርጉት የመከላከያ እና ልዩ ኃይል አባላት ናቸው

ዓርብ፣ ኅዳር 16 2009

በጋምቤላ ከተማ የጦር መሳሪያን ለመያዝ በሚል የቤት ለቤት ፍተሻ ረቡዕ  ህዳር 14 መደረጉን እና በሌሎችም የጋምቤላ ወረዳዎች አሰሳው እንደሚቀጥል ነዋሪዎች ለዶይቸ ቬለ ገለጹ፡፡ ፍተሻውን እያደረጉ የሚገኙት የመከላከያ ሰራዊት አባላት እና የክልሉ ልዩ ኃይላት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

https://p.dw.com/p/2TH3g
Russland Waffe Kalaschnikow-Modell AK-47
ምስል picture-alliance/dpa

Military, Special Force search for firearms in Gambella FINAL - MP3-Stereo

ፍተሻው በኢታንግ ወረዳ ከቀናት በፊት እንደተጀመረ እና አሁንም በወረዳው የተለያዩ አካባቢዎች ቀጥሏል ብለዋል ነዋሪዎች፡፡ ረቡዕ በጋምቤላ ከተማ የተካሄደው የቤት ለቤት ፍተሻ ነዋሪው ሳያውቅ ድንገት የተደረገ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ በተለያዩ ቦታዎች መንገድ ተዘግቶ ከለሊቱ 11 ሰዓት ጀምሮ ፍተሻ ይካሄድ እንደነበር እና ቁጥራቸው ያልታወቁ ህገ ወጥ የተባሉ መሳሪያዎች መያዛቸውንም ይገልጻሉ፡፡

ሐሙስ ምሽት ያነጋገርናቸው እና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ ረቡዕ ዕለት ስለነበረው የመሳሪያ አሰሳ ይህን ይላሉ፡፡ በሌሎች ወረዳዎች ስለነበረውም ፍተሻም ያብራራሉ፡፡ 

“ይህ በቅርብ ቀን ወደ ገጠር ወረዳ አካባቢ እንደዚሁ ተደርጎ ነበር፡፡ ግን ትናንት [ረቡዕ] ከተማ አካባቢ ነበር፡፡ በየቤቶቹ ፍተሻ ተደርጎ ሕገ ወጥ መሳሪያ መኖር አለመኖሩ ተፈትሾ የተገኙ ተወሰዱ ያልተገኙ ደግሞ ገና በመፈተሽ ላይ ነው ያሉት፡፡ ወደ ኢታንግ ወረዳ አካባቢ፣ ወደ አኮቦ አካባቢም እንደዚያው ፍተሻ ተደርጎ እዚያም ብዙ መሳሪያዎች ተገኝቶ ነበር፡፡ መሳሪያ መስጠት ፍቃደኛ ያልሆኑት በግድ የተያዙ አሉ፤ እስከ እስር ቤት የደረሱ አሉ፡፡ ብዛታቸው አልተነገረንም” ይላሉ፡፡

የእኚህን ነዋሪ ገለጻ ሌላኛው የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ አቶ ድላንግ ጆንም ይጋራሉ፡፡ የኑዌር ተወላጆች መኖሪያ ሰፈር በሆኑው “ኒውላንድ” የሚገኘው የእርሳቸው ቤትም መፈተሹን ይናገራሉ፡፡ በጋምቤላ ባለፈው ዓመት የተቀሰቀሰው ዓይነት የእርስ በእርስ ግጭት ዳግም እንዳይነሳ በሚል ፍተሻው መደረጉን ያስረዳሉ፡፡

“ጠዋት ለሊት አንኳኩ፡፡ ከዚያ ሰውየው ውጡ፣ ይፈተሽ ብሎ መሳሪያ ካለ ይወስዳል፡፡ አንተ ከእነ መሳሪያው ትሄዳለህ፡፡ ከሁለቱም ጋር ማለት ነው፡፡ መሳሪያ ከተገኘብህ ትሄዳለህ፡፡ ከየት ነው ያገኘኸው [ብለው ይጠይቁሃል] አንተ ትናገራለህ፡፡ እርሱ ነው የሆነው፡፡ ከባሮ ማዶ፣ ከጎንደር ሰፈር፣ ከዶን ቦስኮ እንዳለ ጋምቤላ ጠቅላላ ነው የተፈተሸው፡፡ መሳሪያ አግኝተዋል ግን ስንት እንዳገኙ እኔ አላውቅም” ሲሉ ያዩትን ይናገራሉ፡፡

በጋምቤላ ከተማ የነበረው ፍተሻ እስኪጠናቀቅ የክልሉ ፖሊሶች መሳሪያቸውን እንዲያስረክቡ እንደተደረገ እና በትናንትናው ዕለት እንደተመለሰላቸው ነዋሪው አስረድተዋል፡፡ ሰሞኑን በጋምቤላ ክልል ሲካሄድ የሰነበተው ፍተሻ አሰሳው ባልደረሰባቸው ወረዳዎችም እንደሚቀጥል ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡ በኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ድንበር ላይ የምትገኘው የማታር ከተማ ቀጣይ የፍተሻው ኢላማ እንደምትሆን ሰምተዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለማግኘት ወደ ጋምቤላ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ጋትሉክ ቱት ተንቃሳቃሽ ስልክ ላይ በተደጋጋሚ ብንደውልም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ

አዜብ ታደሰ