1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በግሪክ ምርጫ ግራ ዘመሙ ፓርቲ እየመራ ነው

እሑድ፣ መስከረም 9 2008

በግሪክ ዛሬ ምክር ቤታዊ ምርጫ ተኪያሄደ። አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በግሪክ ምክር ቤታዊ ምርጫ ሲኪያሄድ ይህ ሁለተኛ ጊዜው ነው። ከሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው የተነሱት የቀድሞው የግሪክ ጠቅላይ ሚንስትር አሌክሲስ ሲፕራስ ግራ ዘመም ፓርቲ ሲሪዛ በድምፅ እየመራ ነው።

https://p.dw.com/p/1GZTz
Griechenland Athen Wahlen Wahllokal Alexis Tsipras
ምስል Getty Images/AFP/L. Gouliamaki

በግሪክ የምክር ቤት የመጀመሪያ ዙር የምርጫ ውጤት መሠረት ሲሪዛ ፓርቲ አብላቻ ድምጽ አግኝቷል። ሆኖም ለብቻው መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችለውን ድምፅ አላገኘም ተብሏል። በግሪክ አንድ ፓርቲ በተናጠል መንግሥት ለመመሥረት 38 ከመቶ ድምፅ ማግኘት ያስፈልጋል። ግራ ዘመሙ የሲሪዛ ፓርቲ እስካሁን ያገኘው ድምፅ ከ30 እስከ 34 በመቶ እንደሆነ ተገልጧል።

በቁጠባ መርሐግብር ከዩሮ አባል ሃገራት ጋር ክርክር ውስጥ በነበረችው ግሪክ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ለምርጫ ጥሪ ደርሶታል። ይሁንና የህዝቡ የምርጫ ተሳትፎ ከፍተኛ እንዳልነበር ተስተውሏል። ጊዜያዊ የምርጫ ውጤት ዛሬ ማምሻውን ይጠበቃል። እንደ አንድ የመጨረሻው የሕዝብ መጠይቅ ከሆነ ግን ምርጫው ከፍተኛ ፉክክር የሚታይበት ነው። ከሥልጣናቸው በገዛ ፈቃዳቸው የተነሱት የቀድሞው የግሪክ ጠቅላይ ሚንስትር አሌክሲስ ሲፕራስ የሚመሩት ግራ ዘመሙ ሲሪዛ ፓርቲ እና ወግ አጥባቂው የኒያ ዲሞክራቲያ ዕጩው ኤቫንጄሎስ ማይማራኪስ መካከል ፉክክሩ መጠናከሩ ተገልጧል።

Griechenland Wahlen Wahlplakat mit Alexis Tsipras in Athen
ምስል Reuters/A. Konstantinidis

አንድ ፓርቲ አብላጫ ድምፅ ማግኘቱ አጠያያቂ በመሆኑ ምናልባትም ከዛሬው ምርጫ ውጤት በኋላ በግሪክ ጥምር መንግሥት መመሥረቱ የግድ አስፈላጊ መሆኑ አይቀርም ተብሏል። ወግ አጥባቂውና መፍቀሬ አውሮጳ ኅብረት የሆነው አዲስ ዲሞክራሲ (Neo Dimokratia) ከ28,5 እስከ 32,5 በመቶ እንዳገኘ ተጠቅሷል። በሦስተኛ ደረጃ ድምፅ ያገኘው የቀኝ አክራሪዎቹ ወርቃማው የንጋት ጎሕ የተሰኘው ፓርቲ ነው። እስካሁን በተቆጠረው ድምፅ መሠረት ከ6,5 እስከ 8,0 በመቶ ድምጽ አግኝቷል። ኮሙኒስቶች ከ5,5 እስከ 7 በመቶ በማግኘት ተከትለውታል። መሀል ሰፋሪውና በግሪክ ቋንቋ ወንዙ የሚል ትርጓሜ ያለው ቱ ፖ ታሚ ፓርቲ (To Potami) ፓርቲ ከ4,5 እስከ 7 በመቶ የሚደርስ ድምፅ እንዳገኘ ተዘግቧል። ለምርጫው ጥምረት የፈጠሩት የሶሻሊስት ንቅናቄው ፓሶክ (Pasok) ፓርቲ እና አነስተኛው ዲሞክራሲያዊ ግራ ዘመም ፓርቲ ዲማር (Dimar) በጋራ ከ5,5 እስከ 7 እንዳገኙ ተገልጧል።

በግሪክ የምርጫ ደንብ መሠረት ከ300 የግሪክ ምክር ቤት መቀመጫዎች 250ዎቹ በምርጫው ላሸነፉ ፓርቲዎች ይታደላል። የተቀሩት 50 መቀመጫዎችበምርጫው ጠንካራ ሆኖ ለወጣው ፓርቲ በቀጥታ ይሰጣሉ። በዛሬው ምርጫ ጠንካራ ሆኖ የወጣው የግራ ዘመሞቹ ሲሪዛ ፓርቲ እንደሆነ ተጠቅሷል።

ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ