1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እማኞች 2 ሞተው 10 በጽኑ ቆስለዋል ይላሉ

ረቡዕ፣ ጥር 3 2009

በጎንደር ከተማ በአንድ ሆቴል ላይ ትላንት ምሽት ጥር ሁለት በደረሰ የቦምብ ፍንዳታ አንድ ሰው ሞቶ 18 ሰዎች መቁሰላቸውን የአማራ ክልል አስታውቋል፡፡ ጥቃቱን ያደረሱት ሰዎች ማንነት አለመታወቁን የክልሉ ኮሚዩኔኬሽን ጉዳዩች ኃላፊ ተናግረዋል፡፡ የዓይን እማኞች በበኩላቸው ሟቾቹ ሁለት መሆናቸውን 10 ሰዎችም በጽኑ መቁሰላቸውን ይገልጻሉ፡፡ 

https://p.dw.com/p/2VeBQ
12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

ፍንዳታው የደረሰው በማራኪ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 18 በሚገኘው ኢንታሶል አነስተኛ ሆቴል ነበር፡፡ ሆቴሉ ትላንት ምሽቱን እንደወትሮው ደንበኞቹን እያስተናገደ በነበረበት ጊዜ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ ፍንዳታ መሰማቱን የዓይን እማኞች ይናገራሉ፡፡ በፍንዳታው ሁለት ሰዎች መሞታቸውን እና 10 በጸና መቁሰላቸውን እማኞቹ ተናግረዋል፡፡ ከፍተኛ አደጋ ከደረሳባቸው ውስጥ ሁለቱ በሆቴሉ ውስጥ በአስተናጋጅነት የሚያገለግሉ እንደነበሩ ይገልጻሉ፡፡

አደጋው እንደደረሰ አካባቢው በወታደሮች መከበቡን እና በርካታ ሰውም ይሯሯጥ እንደነበር እማኞቹ ያስረዳሉ፡፡ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የአካባቢው ነዋሪ የተመለከቱትን ለዶይቸ ቨለ እንዲህ ገልጸዋል፡፡

“አካባቢው ወደ [ጎንደር መምህራን] ኮሌጅ አካባቢ ነው፡፡ ወደመሰጊድ ታክሲ የሚያዝበት አካባቢ ነው፡፡ ማታ ነበር፡፡ ፋሲል ከነማ ጨዋታ ነበረው በዚያ ላይ በዓል ስለነበር በርካታ ሰው በሚንቀሳቀስበት አካባቢ ነው ይህ አደጋ የደረሰው፡፡ ሁለት ሰዎች ሞተዋል ነው የተባለው፡፡ አስር የሚደርሱ ሰዎች ደግሞ ተጎድተዋል፣ ከባድ አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡ ወደ ሆስፒታል ነው የተወሰዱት የተባለው፡፡ ሆስፒታል መግባት እይቻልም፡፡ እንደዚህ ዓይነት አደጋ ሲደርስ ጎንደር አንዳንዴ ከበድ ይላል፡፡ [ወደሆስፒታል] መግባት የማይቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ የህዝብ ሆስፒታል ቢሆንም ብዙ ጊዜ ለመጠየቅም፣ ለመግባትም የሚከብድበት ሁኔታ ይፈጠራል” ይላሉ የአካባቢው ነዋሪ፡፡

የአማራ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ቦምብ ፈንድቶ ጉዳት መድረሱን ለዶይቸ ቨለ አረጋግጠዋል፡፡ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በተመለከተ ግን ከዓይን እማኞች ይለያሉ፡፡ አጠቃላይ ቁስለኞችን ቁጥር ከፍ ያደርጉታል፡፡

“ምሽት ሁለት ሰዓት ላይ ሰዎች በሚዝናኑበት ሆቴል ቦምብ ተጥሎ፣ ፈንድቶ የአንድ ሰው ህይወት አጥፍቷል፡፡ አስራ ስምንት ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ ከእነዚህ ውስት የሶስቱ ከባድ ነው፡፡ የአስራ አምስቱ ቀላል የአካል ጉዳት ነው፡፡ የሚታከሙት በጎንደር ሆስፒታል በህክምና ላይ ናቸው፡፡ መለስተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ህክምና የሚደረግላቸው ተደርጎላቸው ወደየቤተቦቻቸውና መኖሪያዎቻቸው ተመልሰዋል” ይላሉ ኃላፊው፡፡

Symbolbild Bombe
ምስል Fotolia/vlorzor

አቶ ንጉሱ የማቹን ማንነት ባይገልጹም የጀርመን ዜና አገልግሎት ግን የመንግስት ሰራተኛ መሆኑን ባለስልጣናትን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ የዓይን እማኞች በአካባቢው ባለው የጸጥታ ቁጥጥር ምክንያት ስለሟቾቹም ሆነ ስለአደጋው ሌሎች ተጨማሪ መረጃዎች ለማግኘት እንደተቸገሩ ይነገራሉ፡፡ ከአደጋው በኋላ በሆቴሉ አካባቢ ያለው ሁኔታ ምን እንደሚመስል የዓይን እማኙ እንዲህ ያስረዳሉ፡፡

“እስካሁን ያየው ነገር በርካታ ወታደሮች እንዳሉ ነው፡፡ ውስጥ ነው የፈነዳው የተባለው፡፡ ውጭ ላይ ስታየው ምንም የተፈጠረ ነገር ያለ አይመስልም፡፡ እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አልነበረም፡፡ ወታደሮች ብቻ ነበር የነበሩት፡፡ ለምርመራ የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች እየወሰዱ ይመስለኛል፡፡ ህዝቡንም እየጠየቁ ነበር፡፡ እዚያ አካባቢ ያሉትን ሰዎች የምታውቋቸው እያሉ መረጃዎች እየጠየቁ ነው፡፡ እንቅስቃሴው ከሰዓት በኋላ ወደቀድሞው ተመልሷል፡፡ ቤተ-እስራኤላውን ናቸው በብዛት እዚያ አካባቢ የሚበዙትም ፣ የሚዝናኑትም፡፡ ብዙ ጊዜ ለመዝናናትም ሲመጡ እዚያ ሆቴል ነው፡፡ ነገር ግን ሆቴሉ ለሁሉም ማህበረሰብ ነው አግልግሎት የሚሰጠው” ይላል የአይን እማኙ ሆቴል በእነማን እንደሚዘወተር ጭምር ሲያብራራ፡፡  

በአማራ ክልል የቦምብ ፍንዳታ ሲደርስ የትናንቱ በሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ የክልሉ መንግስት መቀመጫ በሆነችው ባህር ዳር ረቡዕ ታህሳስ 26 ሌላ ፍንዳታ ተከስቶ ነበር፡፡ ቦምቡ የፈነዳው ግራንድ ሪዞርት እና ስፓ በተሰኘ ሆቴል አጠገብ ነበር፡፡ የክልሉ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሁለቱን አደጋዎች የሚያገናኛቸው ነገር ይኖር እንደው ጠይቀናቸዋል፡፡ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

“ባህርዳር ላይ ታህሳስ 26 አንድ ሆቴል ላይ ቦምብ ፈንድቶ በአካልም፣ በንብረትም ላይየደረሰ ጉዳት የለም፡፡ ይሄኛው ደግሞ በትናትናው ምሽት ደርሷል፡፡ እንግዲህ ሁለቱ ይገናኛሉ አይገናኙም የሚለው ዝርዝር የጸጥታ መዋቅሩ በሚደርስበት መረጃ ይወሰናል ማለት ነው” ይላሉ ኃላፊው፡፡

የጎንደሩን ጉዳቱን ያደረሰው አካል ማን እንደሆነ አለመታወቁን የሚናገሩት አቶ ንጉሱ የጸጥታ መዋቅሩ እና የክልሉ ፖሊስ ጉዳዩን እያጣራ እንደሚገኝ ይገልጻሉ፡፡ ተጠርጣሪም እስካሁን አለመያዙንም ተናግረዋል፡፡ የክልሉ መንግስት ወደፊት የደረሰበትን እና ፈጻሚዎቹ በቁጥጥር ስር ሲያውል ለህዝብ እንደሚገልጽ ጨምረው አስረድተዋል፡፡  

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ