1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቡሩንዲና የአፍሪቃ ኅብረት የፀጥታ አስከባሪ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 12 2008

የአፍሪቃ ኅብረት ወደቡሩንዲ የሰላም አስከባሪ ኃይል ለመላክ ያቀረበዉ እቅድ በሀገሪቱ ምክር ቤት አባላት ተቃዉሞ ገጠመዉ። ትናንት በጉዳዩ ላይ የመከረዉ የቡሩንዲ ምክር ቤት የኅብረቱን የሰላም አስከባሪ ኃይል «ወራሪ» በማለት ኮንኖ፤ መንግሥት ተልዕኮዉን እንዳይቀበል አሳስቧል።

https://p.dw.com/p/1HRsJ
Burundi Armee findet Waffen in der Hauptstadt Bujumbura
ምስል Reuters/J. P. Aime Harerimana

[No title]

54 አባል ሃገራት ያሉት የአፍሪቃ ኅብረት ባለፈዉ ሳምንት ዓርብ ነዉ ቡሩንዲ ዉስጥ የቀጠለዉ አመፅ ተባብሶ ወደ እርስበርስ ጦርነት እንዳይሸጋገር ይረዳል ያለዉን የሰላም አስከባሪ ኃይል ለመላክ መወሰኑን ያሳወቀዉ። ለዚህ ዉሳኔዉም የቡሩንዲ መንግሥትን ይሁንታ ለማግኘት የአራት ቀናት ጊዜን ሰጥቷል። በዚህ ጊዜ ምላሽ ባያገኝም ግን የተነሳዉን አመፅ ማብረድ የሚችል 5,000 የሰላም አስከባሪ ኃይል እንደሚልክ ነዉ የተነገረዉ። የቡሩንዲ ፕሬዝደንት ቃል አቀባይ ቀደም ብለዉ መንግሥታቸዉ የኅብረቱን ሰላም አስከባሪ ኃይል ለመቀበል ዝግጁ እንዳልሆነ ተናግረዋል። የመንግሥታቸዉን ይሁንታ ሳያገኝ ኅብረቱ ጦር የሚልክ ከሆነም ወራሪ ኃይል ስለሚሆን የቡሩንዲ መንግሥት መብቱን የማስጠበቅ ርምጃ የመዉሰድ መብት እንዳለዉም አመልክተዋል። የቡሩንዲ ምክር ቤት ትናንት በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ ባወጣዉ መግለጫ መንግሥት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በፀጥታ ማረጋጋት ስም በባዕዳን እንዳያስይዝ ተማፅኗል። «ወራሪ ኃይል» ያለዉን ሰላም አስከባሪ ጦር ለመቀበልም ከኅብረቱ ጋር መስማማት እንደማይኖርበት አሳስቧል። የምክር ቤት አባል የሆኑት ሪቨሪየን ናዲኩሪዮ የኅብረቱን ዉሳኔ ደግፈዉ የሰላም አስከባሪ ወታደር ለመላክ ካቀዱ ሃገራት ጋር መነጋገር እንደሚያስፈልግ ነዉ የጠቆሙት፤

Burundi Gewalt ARCHIVBILD
የቀጠለዉ አመፅምስል picture-alliance/dpa/D. Kurokawa

«የዚህ ህዝብ ወኪሎች እንደመሆናችን ወደቡሩንዲ ወታደሮች ለመላክ የሚስማሙ ሃገራትን እንጎበኛለን። ምክር ቤቶቻቸዉ ቡሩንዲን ለማጥቃት ይፈልጉ እንደሆን እንጠይቃቸዋለን። እዚያም ቢሆን ሰዎች አለመሞታቸዉን እንጠይቃለን ምክንያቱም መሞት እና የዘር ማጥፋት ልዩነት አለዉና። አራት ሰዉ ከሞተ ዘር ማጥፋት አይደለም። ምክር ቤት ስላለዉ ወደአፍሪቃ ኅብረትም ሄደን የፓን አፍሪቃ ፓርላማ እንዴት ከአፍሪቃ ኅብረት ጋር ሊተባበር እንደቻለ እንጠይቃለን።»

ቡሩንዲ ዉስጥ በተካሄደዉ ምርጫ አሸንፈዉ ምርጫዉ ተዓማኒና ሚዛናዊ አይደለም በሚል ምክር ቤት አልገባም ያሉት የብሔራዊ ምክር ቤት አንድነት ፓርቲ ተመራጭ በበኩላቸዉ ገዢዉ ፓርቲ ከተቆጣጠረዉ ምክር ቤት የሚፈፀመዉ ግድያ የዘር ማጥፋት መሆኑን ሊያምን እንደማይችል ነዉ የሚናገሩት፤

«90 በመቶዉ የምክር ቤት ተመራጭ የCNDD-FDD አባል በሆነበት ምክር ቤት እንዲህ ያለዉን ወንጀል ማጣጣል በጣም የተለመደ ነዉ። ገዢዉ ፓርቲ በወንጀሉ ኃላፊነት አለበት። ሕዝቡን ከጥቃት ለመከላከል የሚመጣዉን የዉጭ ጣልቃ ገብነት ያለዉን ኃይል በሙሉ ተጠቅሞ ይታገላል።»

የቡሩንዲ ፕሬዝደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ የሐገሪቱ ሕገ-መንግሥትን ጥሰዉ ለሶስተኛ ዘመነ-ሥልጣን ለመመረጥ ከወሰኑ እና በሐምሌ ወርም ተመርጠዉ መልሰዉ ስልጣናቸዉን ካደላደሉ ወዲህ የሐገሪቱ ሠላም ተናግቷል። ለወራት የዘለቀዉ የጎዳና ላይ ተቃዉሞ አመፅን ከማስፋፋቱ በላይ በየምሽቱ የታጠቁ ኃይሎች ተኩስ እንደናጣት ነዉ። ዘገባዎች እንደሚሉትም በየጎዳናዎቿ የሰዎች አስከሬን በየቀኑ ይታያል። ባለፈዉ ዓመት ግንቦት ወር ላይ ወታደሮች ያልተሳካ መፈንቅለ መንግሥት ሞክረዋል፤ የቡሩንዲ መንግሥት እንዲህ ላየዉ ጎረቤት ሩዋንዳን አማፅያንን በማሰልጠንና በመደገፍ ይከሳል፤ ኪጋሊ ዉድቅ ብታደርገዉም። በፀጥታ ኃይሎች እና በመንግሥት ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ ከቀላል መሣሪያ አንስቶ እስከአዳፍኔ ጥቃቶች ይደርሳሉ። የቡሩንዲ ምክር ቤት አባላት ግን ሀገራቸዉ ከአጎራባች ሃገራት ያልተናነሰ ሰላም የሰፈነባት መሆኗን ነዉ የሚናገሩት። የምክር ቤቱ እና የገዢዉ CNDD FDD ፓርቲ ሊቀመንበር ፓስካል ኒይቤንዳ ችግር ካለም በዋና ከተማ ቡጁምቡራ ጥቂት አካባቢዎች ነዉ ማለታቸዉን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ጠቅሷል።

African Union Hauptquartier in Addis Abeba
የአፍሪቃ ኅብረትምስል AFP/Getty Images/J. Vaughan

የበርካታ ዜጎች ህይወት ማለፉ እንደሚያሳዝናቸዉ የገለፁት የቡሩንዲ ብሔራዊ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አጋቶን ራዋሳም ቢሆኑ የሰላም አስከባሪ ወደዚያች ሀገር ይላካል መባሉን የተቀበሉት አይመስሉም፤

«ዛሬ ምንነቱ ባልታወቀ አጋጣሚ የሚገደሉ ቡሩንዲያዉያን መኖራቸዉ በጣም አሳዛኝ ነዉ። ምናልባትም ግን የከፋ ችግር ያለባቸዉ ጎረቤት ሃገራት ይኖራሉ። በአንዲት መንደር እንኳን ቢሆን ያም ችግር ነዉ። ቡሩንዲ አንድ ናት። ይህም ብሔራዊ ችግር መሆኑን መረዳት አለብን።»

ባለፈዉ ሳምንት የተመድ ዋና ፀሐፊ ባን ጊ ሙን ወደእርስበር ጦርነት ለመግባት አፋፍ ላይ ደርሷ ያሉት የቡሩንዲ ቀዉስ አካባቢዉን በመላ ሊያዳርስ እንደሚችል ስጋታቸዉን ተናግረዋል። አመፁን ለማረጋጋት የተመድን የሰላም አስከባሪ ኃይል የመላክ አማራጭንም አቅርበዋል። ሆኖም ዋና ፀሐፊዉ አስቀድሞ የቡሩንዲን ቀዉስ በዉይይት ለመፍታት አንድ የልዑካን ቡድን ወደዚያ እንደሚልኩም አስታዉቀዋል።

Burundi Gewalt und Tote
አስከሬኖች በጎዳና ላይምስል picture-alliance/AP Photo

በተመድ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሳማንታ ፓወር የቡሩንዲ መንግሥት የአፍሪቃ ኅብረትን የሰላም አስከባሪ ኃይል አልቀበልም ያለበትን አቋም አስተካክሎ የመጨረሻ ያሉትን ምላሽ እንደሚሰጥ ተስፋቸዉን ገልጸዋል። እሳቸዉ እንደሚሉትም የሰላም አስከባሪ ኃይል ስምሪቱ ለሲቪሉ ኅብረተሰብ መተማመን እና ጥበቃ ይደረግልኛል የሚል ስሜትን ይፈጥራል። ቡሩንዲ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1993 እስከ 2006,ም ድረስ በእርስ በርስ ጦርነት ታምሳለች። በወቅቱም ሁቱዎች የሚበዙባቸዉ አማፅያን እና ቱትሲዎች የሚያመዝኑበት የጦር ኃይል ባካሄዱት ዉጊያ የ300,000 ሰዎችን ህይወት ፈጅቷል። ሀገሪቱ አሁንም ወደተመሳሳይ የእርስ በርስ ጦርነት እንዳትገባ የሚል ስጋት አለ።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ