1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቡሩንዲ ከምሥራቅ አፍሪቃ ማኅበረሰብ ልትወጣ ነው

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 30 2007

ቡሩንዲ ከምሥራቅ አፍሪቃ ማኅበረሰብ አባልነቷ ልትወጣ እንደምትችል አንዳንድ የምሥራቅ አፍሪቃ መገናኛ አውታሮች በመዘገብ ላይ ናቸው። በእንግሊዘኛ (The East African)የምስራቅ አፍሪቃው የተሰኘው አንድ በኬንያ የሚታተም መጽሔት የማኅበረሰቡን ዋና ጸሐፊ በምንጭነት ጠቅሶ ስለጉዳዩ ዘግቧል። ሌሎች መገናኛ አውታሮች ምንጫቸውን አልጠቀሱም።

https://p.dw.com/p/1GRhj
Tansania EAC Gipfel in Dar es Salaam
ምስል picture-alliance/dpa/S. Duda

[No title]

ቡሩንዲ ከማኅበረሰቡ አባልነት ልትወጣ ያስችላታል የተባለው የጀርመን የልማት ትብብር በምሥራቅ አፍሪቃ ማኅበረሰብ ላይ ግፊት በማድረጉ እንደኾነ ገልጠዋል። ግፊቱም ቡሩንዲ በምሥራቅ አፍሪቃ ማኅበረሰብ አባልነቷ የምትቀጥል ከኾነ የጀርመን ልማት ትብብር ከምሥራቅ አፍሪቃ ማኅበረሰብ ጋር አብሮ መሥራቱን ሊያቋርጥ እንደሚችል መዛቱ ነው ብለዋል። የምሥራቅ አፍሪቃ ማኅበረሰብ አባላት ቡሩንዲ፣ ርዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ እና ኬንያ ናቸው።

በምሥራቅ አፍሪቃ ማኅበረሰብ የቡሩንዲ ተወካይ ሊዮንቲኔ ንዮንዜማ ሃገራቸው ከማኅበረሰቡ አባልነት ልትወጣ ነው መባሉን ሲሰሙ እጅግ ነው የተደነቁት። «ቡሩንዲ ውስጥ ይኪያሄዱ የነበሩ ስብሰባዎች በአጠቃላይ ለእኛ ሳይነገረን ወደ ሌሎች ሃገራት ተዛውረዋል።» ያሉት ተወካዪዋ ሀገራቸው ከማኅበረሰቡ አባልነት ወጥታለች መባሉን መስማታቸውን ተናግረዋል። ሀገራቸው ከማኅበረሰቡ እንድትወጣ ያደረጉት የምሥራቅ አፍሪቃ ማኅበረሰብ ዋና ጸሓፊ ሩዋንዳዊው ሪቻርድ ሴዚቤራንም ወቅሰዋል። «የጀርመን የልማት ትብብር ውሳኔን በተመለከተ ሊያሳውቁን ይገባ ነበር» ብለዋል። ኬንያ ናይሮቢ ውስጥ የአፍሪቃ ፀጥታ ጥናት ተቋም ተንታኝ የኾኑት ዮላንዴ ቦካ የጀርመን የልማት ትብብር ከቡሩንዲ ጋር መተባበሩን ማቋረጡ የጭምጭምታው ምንጭ መኾኑን ጠቁመዋል።

የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ እና የቡሩንዲ ፕሬዚዳንት ፒዬር ንኩሩንዚዛ ለምሥራቅ አፍሪቃ ማኅበረሰብ ጉባኤ ኬንያ መዲና ናይሮቢ ውስጥ
የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ እና የቡሩንዲ ፕሬዚዳንት ፒዬር ንኩሩንዚዛ ለምሥራቅ አፍሪቃ ማኅበረሰብ ጉባኤ ኬንያ መዲና ናይሮቢ ውስጥምስል Getty Images/AFP/T. Karuma

«በታላላቅ ሀይቆች አካባቢ ያሉ ነገሮችን በምትመለከትበት ጊዜ ሁሉ በርካታ ጭምጭምታዎች፣ መረጃዎች እና አሳሳች መረጃዎች አይጠፉም። እናም የእነዚህን ነገሮች እውነተኛነት ለማጣራት እና በቦታው ያለውን ነገር ለመተንተን እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ ሲበዛ አደገኛ ነገር ነው።»

ለቡሩንዲ ከአባልነት መውጣት የምሥራቅ አፍሪቃ ማኅበረሰብ አባላት በኾኑት በሩዋንዳ እና ቡሩንዲ መካከል እያየለ የመጣው ዲፕሎማሲያዊ ውጥረትን እንደሰበብ የሚጠቅሱም አሉ። ቡሩንዲ የሁቱ ዓማፂያንን መጠለያ ሰጥታለች ስትል ጎረቤት ሩዋንዳ ትከሳለች። ቡሩንዲ በበኩሏ ከወራት በፊት በሀገሯ ለተቃጣው መፈንቅለ-መንግሥት ሩዋንዳን ትወነጅላለች። ቡሩንዲን ከማኅበረሰቡ አባልነት እንዳስወጡ የተነገረላቸው የምሥራቅ አፍሪቃ ማኅበረሰብ ዋና ጸሓፊ ሩዋንዳዊ ናቸው።

«ይኽን ዜና ለእውነተኛነቱ ማረጋገጫ ባይኖርም በርካታ ሰዎች አምነው ተቀብለውታል። በኹለቱ ሃገራት መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ውጥረቱን የሚያንረው በመኾኑ እጅግ ሲበዛ አሳሳቢ ነው።»

የምሥራቅ አፍሪቃ ማኅበረሰብ የወቅቱ ሊቀመንበር የታንዛኒያው ፕሬዚዳንት ጃካያ ኪክዌቴ የቡሩንዲን ከማኅበሩ መውጣት በተመለከተ በይፋ የተናገሩት ነገር የለም ተብሏል። ማኅበረሰቡ የጋራ ቀረጥ ኅብረት ሲኖረው፤ አባል ሃገራቱ የሰው ኃይል፣ የቁሳቁሶች፣ የመንቀሳቀሻ ገንዘብ እና የአገልግሎቶች ልውውጥ ያደርጋሉ። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር እስከ 2025ዓ.ም.ድረስም አባል ሃገራቱ የጋራ ገንዘብ ተግባራዊ የማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው ይነገራል። የምሥራቅ አፍሪቃ ማኅበረሰብ በፖለቲካው ረገድ የተልመሸመሸ እንደኾነ ይነገርለታል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ