1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቡሩንዲ -የተፈራው ሊደርስ ይሆን?

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 16 2008

የቡሩንዲው ፕሬዝዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ተቃዋሚዎች ግንባር ፈጥረው በመንግሥት ላይ ጦርነት ማወጃቸውን አስታውቀዋል። አዲሱ ንቅናቄ 'የብሩንዲ ሪፐብሊካን ኃይሎች' የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን በኮሎኔል ኤድዋርዶ ንሺሚሪማና እንደሚመራ የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

https://p.dw.com/p/1HU5F
Burundi Gewalt ARCHIVBILD
ምስል picture-alliance/dpa/D. Kurokawa

[No title]

የጦር አዛዡ የንቅናቄው ዋንኛ ዓላማ በየቀኑ ንኩሩዚዛን በመቃወማቸው ብቻ በየጎዳናው ይገደላሉ ያሏቸውን ዜጎች ደህንነት ማስጠበቅ እንደሆነ ተናግረዋል። «ከዚያ ንኩሩንዚዛ ከስልጣን እስኪወገዱ ድረስ እንዋጋለን።» ይላሉ ኮሎኔል ኤድዋርዶ ንሺሚሪማና። ከአገሪቱ ጦር ሰራዊት በመስከረም ወር ያፈነገጡት ኮሎኔል ኤድዋርዶ ንሺሚሪማና የህግ የበላይነትን በብሩንዲ ማስፈን የአዲሱ ንቅናቄ ዓላማ መሆኑን ጨምረው አስታውቀዋል።

የብሩንዲ መንግስት ባንፃሩ ጥምረቱ ተመሰረተ በተባለ ማግስት ተቃዋሚዎችን በሂደት ድራሻቸውን አጠፋለሁ ሲል አስታውቋል። የፕሬዝዳንቱ ቃል አቀባይ ዊሊ ኒያሚትዌ ጥምረቱ «አይዘልቅም» ሲሉ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል። «ይህ በብሩንዲ የተፈጠረ የመጀመሪያው አማጺ አይደለም።» ያሉት ዊሊ ኒያሚትዌ እንደ ቀደምቱ ሁሉ ምንም ተስፋ እንደሌለው ተናግረዋል።

Burundi Präsident Pierre Nkurunziza
ምስል picture-alliance/dpa/C. Karaba

በቡሩንዲ አዲስ የተቋቋመው የተቃዋሚዎች ጥምረት በአገሪቱ የህግ የበላይነትን ለማስከበር ከጎሮጎሮሳዊው 1993 እስከ 2005 ዓ.ም. የዘለቀውን የርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም የተፈረመውን የአሩሺያ ስምምነት መሰረት እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ትናንት-በቡሩንዲ

ከአፍሪቃ ደሐ አገራት መካከል የምትመደበው ቡሩንዲ ነጻነቷን በጎርጎሮሳዊው 1962 ዓ.ም. ከተቀዳጀችበት ጊዜ ጀምሮ ሁከትና ቀውስ ያልተለያት አገራት ነች። ቡሩንዲ ከጎርጎሮሳዊው 1973-1993 ዓ.ም ባሉት አመታት ያለፈችበትን ታሪክ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተቋቋመው ዓለም አቀፍ መርማሪ ኮሚሽን ከዘር ማጥፋት ያመሳስለዋል። በጎርጎሮሳዊው 1993 ዓ.ም. ዴሞክራሲያዊ በተባለ ምርጫ ሜልቾይር ናዳዳዬን በፕሬዝዳንትነት ብትመርጥም በቱትሲ ወታደሮች በመገደላቸው አዲስ ቀውስ ተቀጣጠለ። ሁከት ይመስል የነበረው አለመረጋጋት ወደ ለየለት የዘር ማጥፋት ተሸጋገረ። አዲስ የተመረጡት የቡሩንዲ ፕሬዝዳንት ሲፕሬይን ንታርያሚራ ከርዋንዳው አቻቸው ጋር ሲጓዙ አውሮፕላናቸው ከኪጋሊ ሰማይ ላይ ተመቶ ወደቀ። በዋናነት በሑቱ እና ቱትሲ ጎሳዎች መካከል በተቀሰቀሰው የርስ በርስ ጦርነት ከ300,000 በላይ ዜጎች መገደላቸውን ይነገራል።

በታንዛኒያ ዋና ከተማ አሩሺያ የተፈረመው ስምምነት ቁልፍ በሆኑ የፖለቲካ ተቋማትና የጸጥታ ኃይሎች ፍትሐዊ የስልጣን ክፍፍል ማድረግና አናሳውን የቱትሲ ጎሳ ከጥቃት ለመከላከል የታለመ ነበር። ስምምነቱ ፕሬዝዳንቱን በሁለት የስልጣን ዘመናት የገደበ ሲሆን የጦር ሰራዊቱ ምንም አይነት ፖለቲካዊ ሚና እንዳይኖረው እንዲያውም ሑቱና ቱትሲዎችን ወደ አንድነት እንዲያመጣ ሃላፊነት ተጥሎበታል።

የአሁኑ ፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛ ሑቱ ሲሆኑ የአማጺ መሪ በነበሩበት ዘመን የቱትሲ ጎሳ ከሚበዛበት የቀድሞው ጦር ሰራዊት ወታደሮች ጋር ተዋግተዋል።አሁን አዲስ ሐይል መመሥረታቸዉን ያወጁት ኮሎኔል ኤድዋርዶ ንሺሚሪማና ወታደሮቻቸው በመንግስት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

Burundi Gewalt und Tote - Polizist
ምስል Reuters/J.P. Aime Harerimana

የቡሩንዲ መንግስት ባለስለስልጣናት በአገሪቱ ተቃውሞ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ የሚያደርጓቸው ንግግሮች የዘር ግጭት እንዳይፈጥር አስግቷል። ፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛ ተቃዋሚዎቻቸውን «የአገር ጠላቶች» እና «ሽብርተኞች» እያሉ ሲጠሯቸው ተደምጠዋል። ከእነዚህ መካከል የቡሩንዲ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሬቬርየን ንዲኩርዮ አንዱ ናቸው። ሬቬርየን ንዲኩርዮ «ዛሬ ፖሊስ በጥይት እግር ይመታል።» አሉ። መንግስታቸው የጦር መሳሪያ አሰሳ ማድረግ በጀመረበት ወቅት- ቀጠሉ ሰውየው «ነገር ግን ቀኑ ሲደርስ ፖሊሶች እያለቀሱ መምጣታቸውን እንዲያቆሙ፤ ስራችሁን ስሩ ስንል እንነግራቸዋለን።» ሲሉ ተደመጡ። «ስራ ስሩ» የሚለው ቃል በጎርጎሮሳዊው የ1994 ዓ.ም. የሩዋንዳ ፍጅት ሑቱዎች በቱትሲዎች ላይ ግድያ እንዲፈጽሙ ትዕዛዝ የሚያስተላልፉበት አገላለጽ ነበር። የሹማምንቱ ንግግሮች እንደ አለም አቀፉ የቀውስ ተመልካች ቡድን ያሉ ተቋማትን አስግቷል። በዓለም አቀፉ ቀውስ ተመልካች ቡድን የአፍሪቃ ክፍል ሐላፊ ኮንፈርት ኤሮ የፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛ አቋም ለአገሪቱ ስጋት ነው ባይ ናቸው።

«በ1990ዎቹ ይባል ከነበረው ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነገር እያየን በመሆኑ አደገኛ ነው ብዬ አስባለሁ። ወደ ንግግር ለመምጣት ፈቃደኛ አይደሉም። የሌላ ወገን ሃሳብ ለመስማት ፈቃደኛም አይደሉም። ከሚያዝያ ወር ጀምሮ በአገራቸውም ይሁን ከአገራቸው ውጪ የሚሰሙ የለውጥ ድምጾችን ለማድመጥ ዝግጁ አይደሉም።»

በታህሳስ ወር መጀመሪያ በቡሩንዲ የጦር ሰፈሮች ላይ ሶስት ተከታታይ ጥቃቶች ከተፈጸሙ በኋላ የመንግስቱ የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ በትንሹ 87 ሰዎች ተገድለዋል። ፕሬዝዳንት ፒየር ንኩሪንዚዛ የአሩሻውን ስምምነት በመጣስ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን ለምርጫ ለመቅረብ መወሰናቸውን ተከትሎ የተፈጠረው ቀውስ ያሳሰበው የአፍሪቃ ህብረት 5000 የሰላም አስከባሪ ወታደሮችን ወደ ቡሩንዲ ለመላክ አሳብ አቅርበው ነበር። ሃሳቡን ግን የቡሩንዲ ባለስልጣናት አልተቀበሉትም። በአፍሪቃ ህብረት እቅድ ላይ የመከረው የአገሪቱ ምክር ቤት ሃሳቡን ሙሉ በሙሉ መቃወሙ ተሰምቷል። ከምክር ቤቱ አባላት መካከል የአገሪቱን ፖሊስ «ስራችሁን ስሩ» እንላቸዋለን ያሉት ሪቨሪየንናዲኩሪዮ አንዱ ናቸው።

«የዚህ ህዝብ ወኪሎች እንደመሆናችን ወደቡሩንዲ ወታደሮች ለመላክ የሚስማሙ ሃገራትን እንጎበኛለን። ምክር ቤቶቻቸዉ ቡሩንዲን ለማጥቃት ይፈልጉ እንደሆን እንጠይቃቸዋለን። እዚያም ቢሆን ሰዎች አለመሞታቸዉን እንጠይቃለን ምክንያቱም መሞት እና የዘር ማጥፋት ልዩነት አለዉና። አራት ሰዉ ከሞተ ዘር ማጥፋት አይደለም። ምክር ቤት ስላለዉ ወደአፍሪቃ ኅብረትም ሄደን የፓን አፍሪቃ ፓርላማ እንዴት ከአፍሪቃ ኅብረት ጋር ሊተባበር እንደቻለ እንጠይቃለን።»

Burundi Soldaten Sicherheitskräfte Militär
ምስል picture-alliance/dpa/D. Kuroawa

የቡሩንዲ ብሔራዊ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አጋቶን ራዋሳ በዕለተ አርብ የተሰማውን የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ የመላክ ሃሳብ ባይቀበሉትም በአገሪቱ ዜጎች እየተገደሉ መሆናቸውን ግን አልካዱም።

«ዛሬ ምንነቱ ባልታወቀ አጋጣሚ የሚገደሉ ቡሩንዲያዉያን መኖራቸዉ በጣም አሳዛኝ ነዉ። ምናልባትም ግን የከፋ ችግር ያለባቸዉ ጎረቤት ሃገራት ይኖራሉ። በአንዲት መንደር እንኳን ቢሆን ያም ችግር ነዉ። ቡሩንዲ አንድ ናት። ይህም ብሔራዊ ችግር መሆኑን መረዳት አለብን።»

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጅምላ ግድያ መከላከል አማካሪ አዳማ ዲየንግ- አጋቶን ራዋሳ «ምንነቱ ባልታወቀ አጋጣሚ» ያሉት የቡሩንዲ ግድያ እንዲጣራ እየወተወቱ ነው። አዳማ ዲየንግ በዕለተ ረቡዕ በሰጡት መግለጫ የቡሩንዲ መንግስት በአገሪቱ እየተፈጸሙ ያሉ ግድያዎች በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ፈቃድ መስጠት ይኖርበታል ሲሉ ተናግረዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ዛይድ ራዓድ አል-ሁሴይን በበኩላቸው በቡሩንዲ ሊቀሰቀስ የሚችል የርስ በር ጦርነት አሊያም የዘር ፍጅት በቀጣናው አገራት ላይ ጭምር የከፋ ተጽዕኖ ያሳድራል። ኮሚሽነሩ በቡሩንዲ እየተፈጸሙ የሚገኙ ግድያዎችን በመመርመር ወንጀለኞቹን ወደ ተጠያቂነት የማምጣት ኃላፊነት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ላይ የተጣለ መሆኑን ተናግረዋል። ለዚህ ሁሉ ግን ፕሬዝዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛ እና መንግስታቸው ከዓለም አቀፉ ተቋም ጋርም ይሁን ከአፍሪቃ ህብረት ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ አይደሉም።

የቡሩንዲ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ሪቻርድ ንዞ ሙንጌ ፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛ ተቃውሞና ግጭቱን እያባባሱት ነው ሲሉ ይከሳሉ።

«ፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛ ውዝግቡን በማብረድ ፈንታ በህዝቡ ዘንድ ፍርሐት እንዲስፋፋ ነው ያደረጉት። ተቃዋሚዎች በሚኖሩባቸው ሰፈሮች ሁሉ ፍርሃት መስፋፋቱን ብቻ ነው ልናገር የምችለው።»

ታሲየን ሲቦማና የተቃዋሚው ሕብረት ለብሔራዊ ብልጽግና (Union for National Progress) ፓርቲ አባል ሲሆኑ በሰኔ ወር በተካሄደው ምርጫ ተሳትፈው ቢያሸንፉም ምክር ቤት ለመግባት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ለታሲየን ሲቦማና ምርጫው ፍትሐዊም ተዓማኒም አልነበረም።

«እንደተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የአፍሪቃ ሕብረት ያሉ ተቋማት የዘር ማጥፋትን የመሰሉ ወንጀሎችን በቸልታ አይመለከቱም። 90 በመቶዉ የምክር ቤት ተመራጭ የCNDD-FDD አባል በሆነበት ምክር ቤት እንዲህ ያለዉን ወንጀል ማጣጣል በጣም የተለመደ ነዉ። ገዢዉ ፓርቲ በወንጀሉ ኃላፊነት አለበት። ሕዝቡን ከጥቃት ለመከላከል የሚመጣዉን የዉጭ ጣልቃ ገብነት ያለዉን ኃይል በሙሉ ተጠቅሞ ይታገላል።»

Burundi Armee findet Waffen in der Hauptstadt Bujumbura
ምስል Reuters/J. P. Aime Harerimana

የቀድሞው የሑቱ አማጺ መሪ የዛሬው የቡሩንዲ ፕሬዝዳንት አገራቸው ወደ የር በርስ ጦርነት ማጥ በተዘፈቀችበት የጎርጎሮሳዊው 1994 ዓ.ም. ነበር በምርጫ ወደ ስልጣን የመጡት። ሰውየው ከአምስት አመታት በፊት በድጋሚ ከተመረጡ ጀምሮ በተቃዋሚዎቻቸው እና የመገናኛ ብዙሃን ላይ አፈና የሚፈጽሙ አምባገነን ሆነዋል የሚል ክስ ይቀርብባቸዋል። ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን በእጩነት የቀረቡበት ምርጫውንም ያሸነፉበት የዘንድሮው ምርቻ ግን በተቃዋሚዎቻቸው እና ተቺዎቻቸው ብቻ ሳይሆን በብሩንዲ ዜጎች ዘንድም ያለው ተቀባይነት አለማግኘቱ ይነገራል። ንኩሩዚዛ ከአገሪቱ ድምጽ ሰጪዎች የሰባ በመቶውን ድምጽ አግኝተው አሸነፉ መባሉ እንደ አጋቶን ርዋሳ ባሉ ተቃዋሚዎች ዘንድ «ቀልድ» ተብሎ ተተችቷል። ፕሬዝዳንቱ ከቀጣናው አገራት መሪዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያላቸው ግንኙነት አብዝቶ ሻክሯል። በቡሩንዲ ዜጎች ዘንድ በጥርጣሬ የሚታዩ ግን ደግሞ የሚፈሩ ሰው ሆነዋል። ከፓርቲያቸው የዴሞክራሲ ተከላካይ ብሄራዊ ካውንስል ፓርቲ (National Council for the Defense of Democracy) ውጪ። ፕሬዝዳንቱ ከአገሪቱ የጸጥታ ተቋማት ውጪ ያሉ ታጣቂ ኃይሎችን በመጠቀም በተቃዋሚዎቻቸው ላይ አፈናና ግድያ ይፈጽማሉ እየታባሉም ይታማሉ። ከእነዚህም መካከል የፖሊስና የጦር ሰራዊቱን መለዮ በመልበስ አሰቃቂ ግድያ ይፈጽማል የሚባለው እና የፓርቲው የወጣቶች ክንፍ እንደሆነ የሚነገርለት ኢምቦኔየኩሬ ታጣቂ ቡድን አንዱ ነው። በዓለም አቀፉ ቀውስ ተመልካች ቡድን የአፍሪቃ ክፍል ሐላፊ ኮንፈርት ኤሮ አሁን በብሩንዲ እየተፈጸመ ከሚገኘው ግድያና ከሚታየው አለመረጋጋት ይበልጥ የወደፊቱ እጅጉን ያሰጋቸዋል።

«የአሁኑ መንግስት ከዚህ በላይ በመላ አገሪቱ የመሳሪያ አሰሳ ሊጀምር እንደሚችል ምልክት ነው። ሌላው ደግሞ ተቃዋሚዎች በመንግስት ላይ ጥቃት ሊጀምሩ ይችላሉ። ወይም አንዱ ማህበረሰብ ከሌላው ማህበረሰብ ከዚህ በባሰ ሁኔታ በመላ አገሪቱ ሊጋጭ ይችላል።»

ፕሬዝዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛም ይሁኑ መንግስታቸው በአገሪቱ ሊቀጣጠል ዳር ዳር ለሚለው ሌላ ግጭት መንዔ ይሆናሉ የሚል ስጋት በዓለም አቀፍ ተቋማትና የቀጣናው አገራት ዘንድ ቢደመጥም ማንም ሊገስጻቸው አልቻለም። ቡሩንዲ እስከዛሬ ድረስ ዜጎቿ በየጎዳናው የሚገደሉባት አሊያም ስደትን የመረጡባት አገር ሆናለች።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ