1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቡርኪና ፋሶ፤ የሕዝባዊ አመፅ ግጭት ምድር

ሰኞ፣ መስከረም 10 2008

አምና ይኸኔ በተቃዉሞ ሠልፈኞች ጩኸት፤ በጎማ ቃጠሎ ጢስ፤ ጠለስ፤ በአስለቃሽ ጋስ ጉም ታፍና ለነበረችዉ ዋጋዱጉ ዘንድሮም-አምና ነዉ።እርግጥ ነዉ የአደባባዩ ሠልፈኛ ብዛት፤ የመፈክር፤ ተቃዉሞዉ ጩኸት መጠንም እንዳምናዉ አይደለም።ጥይት ዉጦት፤ ግድያና ፍርሐት ተክቶታል

https://p.dw.com/p/1Ga2W
ምስል AFP/Getty Images/S. Kambou

የቡርኪና ፋሶ ሕዝባዊ አመፅ

ትንሽ ናት።ወደብ አልባ፤ ደሐ፤ እና የአስራ-አራት ሚሊዮን ሕዝብ ሐገር።የአረብ ሕዝባዊ አብዮት ሰሜን አፍሪቃን ከማጥለቅለቁ ከብዙ ዓመታት በፊት ጨቋኝ መሪዎች በሕዝባዊ ሠልፍ ከሥልጣን ተወግደዉባታል። የአደባባይ ሠልፉ ሕዝባዊ ድል ግን እንደ ዛሬዋ ግብፅ በጦር መኮንኖች መፈንቅለ መንግሥት ተጨናጉሎባታል። የያኔዋ የላይኛዉ ቮልታ።የሶሻሊስት ካፒታሊስቶቹ ሽኩቻ የአፍሪቃን ፖለቲካ ሲነዉጠዉ አዉቅ ብሔረተኞች ብልጭ ብለዉ በቅፅበት ጠፍተዉባታል።ቡሪኪና ፋሶ።መፈንቅለ መንግሥት፤ ወታደራዊ አገዛዝ፤የይስሙላ ምርጫ ለግማሽ ምዕተ-ዓመት ያጀሉት ሕዝባዊ አመፅ፤ አምና ገንፍሎ-ለድል በቅቶ ነበር።ባመቱ ዘንድሮ ለነፃ ምርጫ ስትዘጋጅ ግን የዴሞክራሲ ተስፋዋ በሌላ መፈንቅለ መንግሥት ተቀጨ።የመፈንቅለ መንግሥቱ ሠበብ፤ አስተጋብኦቱና የሐገሪቱ ፖለቲካዊ ዳራ ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።

አምና ይኸኔ በተቃዉሞ ሠልፈኞች ጩኸት፤ በጎማ ቃጠሎ ጢስ፤ ጠለስ፤ በአስለቃሽ ጋስ ጉም ታፍና ለነበረችዉ ዋጋዱጉ ዘንድሮም-አምና ነዉ።እርግጥ ነዉ የአደባባዩ ሠልፈኛ ብዛት፤ የመፈክር፤ ተቃዉሞዉ ጩኸት መጠንም እንዳምናዉ አይደለም።ጥይት ዉጦት፤ ግድያና ፍርሐት ተክቶታል።ሮብ ለሐሙስ አጥቢያ ርዕሠ-ከተማይቱ እንዲያ ነበረች።

«አብዛኛዉ ሰዉ በየቤቱ ተሸሽጎ ነዉ ያደረዉ።ከማታ ጀምሮ እስኪነጋ ድረስ ከየአቅጣጫዉ ተኩስ ሥንሰማ ነዉ-ያደርነዉ።ቀጥታ የራዲዮ ሥርጭቶች ተቋርጠዋል። ጋዜጠኞች ሲደበደቡ፤ የመብት ተሟጋቾች ሲያዙ፤ ሌሎቹ ሲታደኑ ነዉ-ያደርን-የዋልነዉ።»

የዶቸ ቪለዉ ዘጋቢ ሪሻርድ ቲነ።ከተደበቀበት ሥፍራ እንደተናገረዉ።መፈንቅለ መንግስቱን የመሩት የክብር ዘብ አዛዥ ጄኔራል ዢልበር ዲንደር ወታደራዊ ሁንታዉ ለብዙ ጊዜ ሥልጣን ላይ እንደማይቆይ ቢያስታዉቁም ያመናቸዉ የለም።

መፈንቅለ መንግሥቱን የሚቃወመዉ ሕዝብ በየአካባቢዉ ተቃዉሞዉን ማሰማቱን አለቆመም ።የዚያኑ ያሕል የወታደራዊዉ ሁንታ ታማኝ ጦር ተቃዋሚዎችን በጥይት መደብደቡን እንደቀጠለ ነዉ።ቡርኪናቤዉ የምዕራብ አፍሪቃ የጋዜጠኞች ማሕበር ፕሬዝደንት ፒተር ኩዋኩዋ ዛሬ እንደታዘበዉ አንዳድ ከተሞች የተወረሩ ያክል ኦና ናቸዉ።ሌሎች ደግሞ የተቃዉሞ ሠልፈኛና የጦር ሐይሉ መፋለሚያ ሆነዋል።

«መፈንቀለ መንግሥቱ ሐሙስ እንደታወጀ ወታደሮች በየአዉራ ጎዳናዉ በተሰበሰበዉ ሕዝብ ላይ ሲተኩሱ ነበር።ተኩሱን ፍራቻ ሰዉ በየሥፍራዉ በመደበቁ ከተሞቹ ጭር ብለዉ ነበር።እንደሰማሁት ብዙ ሰዎች ተገድለዋል።በመቶ የሚቆጠሩ ቆስለዋል።እና አንዳድ ከተሞች የተወረሩ መስለዉ ነበር።ከአርብ ጀምሮ ግን በትላልቅ ከተሞች የተቃዉሞ ሰልፍ እየተደረገ ነዉ።የጦር ሐይሉ እርምጃ ላላ ባለባቸዉ አካባቢዎች ቅዳሜም የአደባባይ ተቃዉሞዉ ቀጥሎ ነበር።»

ቡርኪና ፋሶ።የሰልፍ-አመፅ፤ የግድያ- የለዉጥ፤ መፈንቅለ መንግሥት፤ ዑደት ምድር።

ከ700 ዓመተ-ዓለም ጀምሮ ሰዉ ተለይቷት አያዉቅም።እንደ አብዛኞቹ የምዕራብ አፍሪቃ ሐገራት ሁሉ የግዛት ክልል፤ ድንበር፤የዘር፤ ሐይማኖት ልዩነት በማይታወቅበት በዚያ በሩቁ ዘመን ከአምስት መቶ የሚበልጡ ጎሳ ተወላጆች ይኖሩባት ነበር።የአረብና የአዉሮጳ ነጋዴዎች የዝሆን ጥርስ፤ ወርቅና የከበሩ ድንጋዮች ለመዝረፍ ከሁሉም በላይ ባሪያ ለመፈንገል አካባቢዉን ከረገጡበት ጊዜ ጀምሮ ግን በሐብት ክፍፍል፤ በመሬት ይዞታ ሰበብ ግጭት፤ ቁርቁስ መጠፋፋት ተለይቷት አያዉቅም።

ዛሬም እንዲሁ ናት።

የአዉሮጳ ቅኝ ገዢዎች በብዙዎቹ የአፍሪቃ ሐገራት እንዳደረጉት ሁሉ በንግድ፤ ሐገር በማሰስ እና ክርስትናን በመስበክ ስም ያዘመቷቸዉ ሰላዮች ያሰባሰቡት መረጃ ፤የብሪታንያ፤ የፈረንሳይና የጀርመን መንግሥታትን ትኩረት እኩል በመሳቡ የዚያ ምድር ሐብት ካገሬዉ ተወላጆች አልፎ የአዉሮጶችም መሻኮቻ ሆነ።

ብሪታንያና ፈረንሳይ በ1896 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ባደረጉት ሥምምነት የፈረንሳይ ቅኝ ገዢዎች ሙሉ በሙሉ ሲቆጣጠሯት እስከ 1980ዎቹ ድረስ የዘለቀ ሥሟን፤ እስካሁን የቀጠለ ፖለቲካዊ ምሥቅልቅሏን፤ ድንበሯንም ቀየሱላት።በ1960 በፈረንሳዮች ፈቃድና ይሁንታ ነፃ ስትወጣ፤ ፈረንሳዮች በሰጥዋት ስም የፈረንሳዮችን የመሠለ መንግሥት አቆመች። République de Haute-Volt። ማዉሪስ ያሜዮጎ-የመጀመሪያዉ ፕሬዝደንት ሆኑ።

የቅስና ትምሕር አልሆን ብሏቸዉ ለፈረንሳይ ቅኝ ገዢዎች በሒሳብ ሠራተኝነት ሲያገለግሉ የወጣትነት ዘመናቸዉን ያሳለፉት ያሜዮጎ በተለይ በዛሬዋ ኮትዲቯር በሠረቱበት ዘመን የቅኝ ገዢዎችን ግፍ በቅርብ ሥላዩ ያአዲስ ሐገራቸዉን ፖለቲካዊ ሥርዓት በጥሩ መደላድል ለማሳረፍ ይጥራሉ የሚል ተስፋ ማሳደራቸዉ አልቀረም።

ሥልጣን እንደያዙ ያስረቀቁት ሕገ-መንግሥት በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እንዲመሠረት የሚደነግግ፤ የመደራጀትና የመናገር ነፃነት የሚያስከበር ዓይነት በመሆኑ ሰዉዬዉ የተጣለባቸዉን ተስፋ ገቢር የሚያደርጉ መስለዉም ነበር።ከመምሰል ግን አላለፈም።

ምርጫ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ከሚመሩት የቮልታዎች ዴሞክራሲያዊ ሕብረት (UDV-በፈረንሳይኛ ምሕፃሩ) በስተቀር ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችን በሙሉ አገዱ።ፕሬዝደንቱ እርምጃቸዉን እንዲለዉጡ የታገዱት የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፤ የሠራተኛና የሙያ ማሕበራት ተጠሪዎች ያሰሙት ተቃዉሞ የፕሬዝደንቱን አቋም የሚያስለዉጥ አልሆነም።ተቃዉሞዉ ከርሮ በእስከያኔዋ አፍሪቃ ብዙም ላልተለመደ የአደባባይ ሠልፍ ሕዝቡን አሳደመ። የላይኛዉ ቮልታ የመጀመሪያዉ መንግሥት በመጀመሪያዉ ታላቅ ሠልፍ ከሥልጣን ተወገደ።ሕዝብ አመፀ።የመሪነቱን ሥልጣን ግን ጦር ሠራዊቱ ተቆጣጠረዉ።1966።የጦር ሐሉ አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አቡበከር ሴንጉሌ ላሚንዛ የሚመሩት ወታደራዊ መንግሥት በሌላ ሕዝባዊ አመፅ ተወግዶ ሌላ የጦር መሪ ሥልጣኑን እስኪይዝ ድረስ ምዕራባ አፍሪቃዊቱን ሐገር እስከ 1980 ድረስ መርቷል።

የሴጉሌን መንግሥት ከሥልጣን ያስወገዱት ኮሎኔል ሳዬ ሰርቦ ከሁለት ዓመት በላይ አልገዙም።በተረኛ መፈንቅለ መንግሥት አድራጊ ከሥልጣን ተወገዱ።ከተደጋጋሚዎቹ መፈንቅለ መንግሥቶች ሁሉ በ1983 የተደረገዉ ሥር ነቀል፤ የዚያችን ሐገር የእስከዚያ ዘመን ፖለቲካዊ፤ምጣኔ ሐብታዊ ይትበሐል ለመለወጥ የሞከረ ነበር።በተለይ የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ እና አስተባባሪ ሻለቃ ቶማስ ኢሲዶሬ ኖል ሳንካራ የጀመሩት የፖለቲካና የምጣኔ ሐብት መርሕ ትንሺቱን ወደብ አልባ ሐገር የአፍሪቃዉያን አብነት አድርጓት ነበር።

ቅኝ ገዢዎች ለሐገራቸዉ የለጠፉትን ሥም ቡርኪና ፋሶ (የሐቀኞች ሐገር እንደማለት ነዉ) ብለዉ የለወጡት፤ የምጣኔ ሐብት መዋቅሮችዋን ባዲዲስ መሠረት ላይ የጣሉት ወጣቱ መሪ፤ የሚከተሉት ግራ ፖለቲካና ብሔረተኝነት ምዕራቡን ዓለም በተለይም የሐገራቸዉን የቀድሞ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይን የሚያስከፋ ነበር።

ሳናካራ፤« ወታደር ፖለቲካዊ ዕዉቀት ከሌለዉ ወንጀል ለመፈፀም መጠቀሚያ መሳሪያ ይሆናል የሚል አባባል ነበራቸዉ።» አልተሳሳቱም።የፈረንሳይና የዩናይትድ ስቴትስ የስለላ ድርጅቶች የነሳንካራን የቅርብ ወዳጆች አስተባብረዉ ወጣቱን መሪ ከሥልጣን አስወግደዉ ከነተባባሪዎቻቸዉ አስገደሏቸዉ።1987 ነበር-ዘመኑ። የሳንካራን መንግሥት ከሥልጣን ያስወገዱትን፤ እነሳንካራን ያስገደሉት ብሌዝ ኮምፓኦሬ ያቺን ሐገር ይገዙ ገቡ።

ሳንካራ ዛሬም ድረስ የአፍሪቃ ቼ ኮቬራ እየተባሉ መወደስ፤መደነቅ፤ መሞጎሳቸዉ አልቀረም።

«ለኛ የልማት፤የፍትሕ፤ድሐነትን የመዋጋት አብነት ናቸዉ።የድሆች ፕሬዝደንት የሚሏቸዉ አሉ።ይሁንና እሳቸዉ ነፃነትና ፍትሕ የሚሹ የሁሉም ፕሬዝደንት ነበሩ።»

አሉ የቡሪካና ፋሶዉ የፖለቲካ አዋቂ ባለፈዉ ወር።የ«ሁሉም» ፕሬዝደንት ከተወገዱ በሕዋላ ሥልጣን የያዙት ኮምፓኦሬ የትንሺቱን ሐገር ሕዝብ ለ27 ዓመታት ሠጥ ለጥ አድርገዉ ገዝተዋል። እራሳቸዉ ያስረቀቁትን ሕገ-መንግሥት ሽረዉ ለተጨማሪ ዘመን ለመግዛት ሲሞክሩ ግን ያ ሕዝብ እደገና አምፅ በአደባባይ ሠልፍ ከሥልጣን አስወገዳቸዉ።አምና ጥቅምት።ኮምፓኦሬ ከተወገዱ በሕዋላ ሥልጣን የያዘዉ ጊዚያዊ መንግሥት በያዝነዉ ወር ማብቂያ ምርጫ እንዲደረግ አቅዶ ነበር።

የምርጫዉ ሲጠበቅ የኮምፓኦሬ የቅርብ ታማኝ የነበሩት ጄኔራል ዢልበር ዲንዴር ጊዚያዊ መንግሥቱን አስወግደዉ የአለቃቸዉን መንበር ጠቀለሉት። ጀርመናዊዉ የፖለቲካ ተንታኝ አሌክሳንደር ሽትሮሕ እንደሚሉት ጄኔራሉ መፈንቅለ መንግሥት እንደሚያደርጉ ከወራት በፊት የታዩ ምልክቶች ነበሩ።

«የዢልበር ተባባሪዎች (የሽግግር መንግሱትን) አጥብቀዉ ከሚተቹ የቡርኪና ፋሶ (ልሒቃን) መካካል ናቸዉ።ዲንዴር በሽግግር መንግሥቱ ዉስጥ ምንም አይነት ሥልጣን የላቸዉም ይሁንና በሐገሪቱ ዉስጥ ካሉ ጥቂት የኮምፓኦሬ ታማኝ አገልጋዮች ጎላ ብለዉ የሚታዩ ሰዉ ናቸዉ።ባለፉት ወራት ዲንዴር ከኮፓኦሬ ጋር ግንኘነት አላቸዉ፤ መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግም ሳያስቡ አይቀርም የሚል ጭምጭምታ ይሰማ ነበር።»

ጄኔራሉ እንደሚሉት መፈንቅለ መንግሥቱን ያደረጉት ለቀድሞ አለቃቸዉ አዝነዉ፤ ወይም በቅድሞ አለቃቸዉ ታዘዉ አይደለም።ጊዚያዊዉ መንግሥት የኮምፓኦሬ ፓርቲ አባላትን በምርጫዉ እንዳይሳተፉ ማገዱን በመቃወም ነዉ-እንጂ።ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን የቡሩኪና ፋሶ ፖለቲካ ዛሬም ከጦር ሠራዊቱ ቁጥጥር ነፃ አለመዉጣቱን ጠቋሚ፤ሕዝባዊ አመፅ አምባገነኖችን ከሥልጣን ከማስወገድ ባለፍ ሕዝባዊ መንግሥት ለመመሥረት አቅም እንደሌለዉ ከግብፅ ቀጥሎ የዘመኑ ተጨማሪ አብነት ነዉ።

የተለያዩ መንግሥታት፤ የአፍሪቃና የአዉሮጳ ሕብረቶች መፈንቅለ መንግሥቱን አዉግዘዉታል።በተለይ የአፍሪቃ ሕብረት የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪዎች እስከ ነገ-ማክሰኞ ድረስ ሲቢላዊዉን አስተዳደር ካልመለሱ ማዕቀብ የጉዞና የገንዘብ ማዕቀብ እንደሚጥልባቸዉ አስጠንቅቋል።የምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ማሕበረሰብ (ECOWAS) በበኩሉ ወታደራዊዉ ሁንታዉ ሥልጣን እንዲለቅ እያባበሉ ነዉ።

ነገ አቡጃ-ናይጄሪያ የሚሰበሰቡት የምዕራብ አፍሪቃ መሪዎች ወታደራዊዉ ሁንታ ካነሳቸዉ ጥያቄዎች በምርጫዉ የቀድሞዉ ፕሬዝደንት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ይወዳደሩ የሚለዉ ተቀባይነት እንዲያገኝ፤ ወታደራዊ ገዢዎቹ ሥልጣን ከለቀቁ ምሕረት እንዲደረግላቸዉ ለማግባባት አቅዷል።የምዕራብ አፍሪቃ የጋዜጠኞች ማሕበር ፕሬዝደንት ፒተር ኩዋኩዋ እንደሚለዉ የኢኮዋስ ሐሳብ አግባቢ ይመስላል።የቡርኪና ፋሶ ሕዝብ ግን አልተቀበለዉም።

«ከምርጫዉ የታገዱ ወገኖች በምርጫዉ እንዲሳተፉ መፍቀድ ጥሩ ሐሳብ ይመስለኛል።ምክንያቱም ቡርኪና ዉስጥ እንዳየነዉ ዓይነት የሚዋልል የፖለቲካ ሽግግር እያለ የተወሰኑ ፖለቲካ ፖርቲዎችን ከምርጫ ማግለል መጥፎ ዉጤት ያስከትላል።ይሁንና የቀድሞዉን ሥርዓት የሚቃወመዉ ሕዝብ የዚያ ሥርዓት አራማጆች በምርጫ መሳተፍ የለባቸዉም የሚል ጠንካራ አቋም ነዉ-ያለዉ።»

ምርጫዉ እራሱ ሥለ መደረጉ በግልፅ የታወቀ ነገር የለም።እርግጥ ነዉ ጄኔራል ዲንዴር ጊዜዉ ይገፋ እንጂ ምርጫ እንደሚደረግ ቃል ገብተዋል።ይሁንና ጄኔራሉ ምርጫ በሚሉት ግርግር እንደ ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል-ሲሲ ወታደራዊ ዩኒፎርማቸዉ በኮት-ከራቫት ቀይረዉ በምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሐገር ትልቅ ወንበር ላይ ቂብ እንዳሉ ላለመቀጠላቸዉ ምንም ዋስትና የለም።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 


 

Burkina Faso Präsident Thomas Sankara
ምስል picture-alliance/dpa
Burkina Faso Protest gegen die Präsidentengarde in Ouagadougou
ምስል Reuters/J. Penney
Burkina Faso Ouagadougou General Gilbert Diendere
ምስል Getty Images/AFP/S. Kambou
Blaise Compaore Präsident von Burkina Faso Archiv Juli 2014
ምስል AFP/Getty Images/Sia Kambou