1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቡድን-ሃያና የፊናንስ ገበያው ጥገና

ሐሙስ፣ ኅዳር 2 2003

ዓለምአቀፉን የፊናንስ ቀውስ ተከትሎ የተጠራው የቡድን-ሃያ መንግሥታት መሪዎች የመጀመሪያ ጉባዔ ዋሺንግተን ላይ ከተካሄደ ሁለት ዓመት ገደማ ሆነው።

https://p.dw.com/p/Q2iH
ምስል Orgranisationskomitee G20 Seoul Summit

የነዚሁ በኢንዱስትሪ ልማት የተራመዱት መንግሥታት መሪዎች በፊታችን ሐሙስና አርብ ደግሞ ደቡብ ኮሪያ ርዕሰ-ከተማ ሶውል ላይ አምሥተኛ ጉባዔያቸውን ያካሂዳሉ። ለመሆኑ አዲስ የዓለም የፊናንስ ስርዓትን በማስፈን ቀውሱ እንዳይደገም ለማድረግ ያኔ የተደረሰበት ስምምነት እስከምን ገቢር ሊሆን ችሏል? በዚህ ረገድ ቢቀር ከሌላ ቀውስ የሚያድን ወሣኝ ደረጃ ላይ ተደርሷል ብሎ መገመቱ በወቅቱ በጣሙን የሚያዳግት ነው። ዓለምአቀፉ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ኦክስፋም በበኩሉ ቡድን-ሃያ መንግሥታት ለቀውሱ ተጠያቂ ላልሆኑት ድሆች አገሮች የበለጠ እንዲያደርጉ ነው ዛሬ በጉባዔው ዋዜማ ያሳሰበው። ድርጅቱ ታዳጊ አገሮች በቡድኑ ውስጥ በሰፊው ሊወከሉ እንደሚገባቸውም አስገንዝቧል።

ሃይል የሆነው የቡድን-ሃያ ስብስብ ሁለት-ሶሥተኛው የዓለም ሕዝብ የሚወከልበት መድረክ ነው። ቡድኑ ዘጠና በመቶውን የዓለምን ኤኮኖሚ አቅምና ከአምሥት አራት ዕጁን የዓለም ንግድ ድርሻም የያዘ መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም በዓለም ኤኮኖሚ ሂደት ላይ ያለው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው። ቡድን-ሃያ በፊናንስ ሚኒስትሮች ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰበሰበው የእሢያን፣ የብራዚልንና የሩሢያን የፊናንስ ቀውስ ተከትሎ እ.ጎ.አ. በ 1999 ዓ.ም. ነበር።
ከዚያን ወዲህ በተከተሉት ዘጠኝ ዓመታት ሚናው ለዘብ ብሎ ሲቆይ የአሜሪካው ሌህማን ብራዘርስ ባንክ ክስረት ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ቀውስን ካስከተለ በኋላ ግን ተልዕኮውና ተፈላጊነቱ የጠነከረ ይሆናል። ቡድን-ሃያ በመንግሥታት መሪዎች ደረጃ የዛሬ ሁለት ዓመት ዋሺንግተን ላይ በመሰብሰብ ቀውሱን ለማስወገድ የሚበጁ ናቸው የተባሉ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ የተስማማውም ከዚህ ግንዛቤ በመነሣት ነበር።
በጊዜው የመንግሥታቱ መሪዎች አንድነት ምናልባት ከዛሬው የበለጠ ነበር ቢባል የተሳሳተ አይሆንም። ቀውሱ መደገም እንደሌለበትና ለዓለም ኤኮኖሚ ፈውስ ብሄራዊ ጥቅም ወደ ኋላ መባሉ አስፈላጊ በመሆኑ ስምምነቱ የጠነከረ ሆኖ ነው በጊዜው የታየው። ይሁን እንጂ የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም የአይ.ኤም.ኤፍ አስተዳዳሪ ዶሚኒክ-ሽትራውስ-ካህን እንደሚሉት ዛሬ ከሁለት ዓመታት በኋላ ያ የጊዜው የአንድነት መንፈስ እየደበዘዘ የሄደ ነው የሚመስለው።

“በእኔ አመለካከት ከዚህ ቀውስ የተገኘው ዋነኛ ግንዛቤ በትብብር የመስራቱ አስፈላጊነት ይመስለኛል። ይህ በዓለምአቀፍ ደረጃ በሚደረገው የኤኮኖሚ ትብብር ላይ ከዚህ ቀደም ያልነበረ አንድ አዲስ ክስተት ነው። ለዚሁ ጠንካራ ፍላጎት መኖሩም በተከተሉት የለንደን፣ የፒትስበርግና የቶሮንቶ ጉባዔዎች መንጸባረቁ ታይቷል። ግን አያይዤ መናገር የምፈልገው ይህ መንፈስ ጨርሶ ባይጠፋም እየተዳከመ በመሄድ ላይ መሆኑን ነው። ይህ ደግሞ አደገኛ ነገር ነው። በመሆኑም ሁሉም ዓለምአቀፍ ለሆነው ቀውስ ብሄራዊ መፍትሄ እንደሌለ መገንዘብ ይኖርበታል። በአንድ እየተሳሰረች በሄደች ዓለማን ማንም ብቻውን ሊራመድ አይችልም”

እርግጥ ተሳታፊዎቹ ወገኖች ሁሉ ይህን አያጡትም። ችግሩ እያንዳንዱ በራሱ ብሄራዊ ችግሮች መጠመዱ ላይ ነው። ለምሳሌ ያህል መንግሥታቱ የፊናንስ ገበያ ጥገና ዕቅዳቸውን በብሄራዊ ፓርላማዎች ለማስጸደቅ የሚያደርጉት ጥረት በየጊዜውና በየቦታው አስቸጋሪ ሲሆን መታየቱ አልቀረም። በጥቅሉ ቡድን-ሃያ መንግሥታት የለውጥ ዕቅዳቸውን ገቢር በማድረጉ ረገድ እስካሁን ያሳዩት ዕርምጃ ብዙም የሚያረካ አይደለም። ይህ ለምሳሌ በተለይ የባንኮችን ድርሻ በተመለከተ የጀርመኗ ቻንስለር የወሮ/አንጌላ ሜርክልም አመለካከት ነው።
“የቀውሱን ወጪ በመሸከሙ ረገድ የፊናንሱ ዘርፍ ተሳትፎ የበለጠ ሊሆን በቻላ ነበር”

ጀርመን በአገር ውስጥ የበኩሏን የባንኮች ተሳትፎ ደምብ አስፍናለች። ግን ችግሩ ቡድን-ሃያ መንግሥታት ዓለምአቀፍ በሆነ የፊናንስ ገበያ ግብር ሊስማሙ አለመቻላቸው ነው። እርግጥ አውሮፓውያን መንግሥታት በወሰዷቸው አንዳንድ የለውጥ ዕርምጃዎች በመጪው የሶውል ጉባዔ ላይ ቀና ብለው ሊቀርቡ ይችላሉ። የፊናንስ ገበያ ቁጥራቸውን ግልጽ በሆነ ሁኔታ አሻሽለዋል። አደገኛ የፊናንስ ተግባራት ሊታገዱ ይችላሉ፤ ትርፍ ለማጋበስ በሚጥሩ የፊናንስ ነጋዴዎች ላይ ልጓማቸውን ለማጥለቅም አስፈላጊውን ዕርምጃ ወስደዋል። እርግጥ ይህ ሆኖም በሌላ በኩል የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሢዮን ፕሬዚደንት ሆሴ-ማኑዌል-ባሮሶ መጪውን የሶውል ጉባዔ የሚመለከቱት በስጋትም ጭምር ነው።

“የመንግሥታቱ መሪዎች ጉባዔ የሚካሄደው አስቸጋሪ በሆነ ወቅት ነው። ስለዚህም ቡድን-ሃያ የዓለም ኤኮኖሚ በወቅቱ የሚያስፈልገውን ቅንጅት ለማስፈን ለመቻሉ መፈተሻ እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም። ወደፊትም የምንወስደውን ዕርምጃ ሁሉ በጋራና በትብብር ማድረግ ይኖርብናል። ይህ ማለት ደግሞ በዓለምአቀፍ ደረጃ የሚከሰት ሚዛን ዓልባነት ለሁሉም አስጊ መሆኑንና በኤኮኖሚ የጠነከሩት ታላላቆቹ አገሮች ለመፍትሄው አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸው መቀበል ማለት ነው”

የወቅቱ ሃቅ ግን ብሄራዊ ጥቅምን ላለማስቀደም ቃል ቢገባም ቅሉ በዚህ ጥያቄ ላይ የቡድን-ሃያ ዓባላት ዛሬም በሃሣብ ብዙ የተራራቁ መሆናቸው ነው። እያንዳንዱ በመጀመሪያ ደረጃ የራሱን ብሄራዊ ኤኮኖሚ በማጠናከሩ ሃሣብ ላይ ማተኮሩ የተሰወረ ነገር አይደለም። ታዲያ ችግሩ ይሄው እያስከተለ ያለው የሚዛን ዝቤት ለቀጣይ ዓለምአቀፍ ቀውስ በር ከፋች እየሆነ መምጣቱ ላይ ነው። ዛሬ በመንግሥታት የንግድ ገቢና ወጪ ሚዛን፤ ማለት ወደ ውጭ በሚነገደውና ወደ ውስጥ በሚገባው ምርት መካክል ያለው የሚዛን ዝቤት አዲስ የኤኮኖሚ ውዝግብን እንዳያስከትል ያሰጋል።

እንደ ምሳሌ ለመጥቀስ ቻይና የብሄራዊ ምንዛሪዋን የዩዋንን ዋጋ ዝቅ አድርጋ በመያዝ በርካሽ ምርቶቿ የገበያ ፉክክርን መርሆ አዛብታለች በሚል በቤይጂንግና በዋሺንግተን መካከል የተያዘው ውዝግብ አንዱ ነው። ውዝግቡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የምንዛሪ ጦርነት የሚል አነጋገር በኤኮኖሚው መድረክ ላይ ደጋግሞ እንዲሰማም አድርጓል። በዚህ በጀርመን የአገሪቱ ቻንስለር አንጌላ ሜርክል በጉዳዩ የሚያስቀድሙት ከምላሽ ይልቅ ጥያቄን ነው።

“ዘላቂ፣ ጠንካራና ሚዛን የጠበቀ የዓለም ኤኮኖሚ ዕድገትን ለማስፈን ምንድነው በጋራ ማድረግ የምንችለው?”

ሜርክል መልሱን የተለያዩት ሃገራት ኤኮኖሚ የፉክክር ብቃት ነጸብራቅ ለሆኑት ለገበያው ሃይላት መተዉን ነው የመረጡት። የምንዛሪው ልውውጥ ተመንም ከዚሁ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ጉዳይ ነው። ለዚህም ነው አንዳንዶች “ሰለ ምንዛሪዎች የዓለም ጦርነት” እስከማውራት መድረሳቸው። ቀደም ሲል በጠቀስነው የቤይጂንግና የዋሺንግተን ቅራኔ መሠረት ለምሳሌ ቻይና ሆን ብላ የምንዛሪዋን ዋጋ ዝቅ በማድረግ የንግድ ጥቅሟን ለመስጠበቅ መጣሯ ያለና ብዙ የተነገረለት ጉዳይ ነው። ዛሬ ደግሞ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓንና ብራዚል የቻይናን ፈለግ እየተከተሉ በመራመድ ላይ ናቸው። ነገም ሌሎች ይከተላሉ። እንግዲህ አደገኛ ፍክክር ነው የተጀመረው። ችግሩ ምናልባት በረጅም ጊዜ ማሰሪያ ያገኝ እንደሆን እንጂ ከነገ በስቲያ ሶውል ላይ በሚከፈተው የቡድን-ሃያ መሪዎች ጉባዔ ሊፈታ ይችላል ብሎ የሚጠብቅም የለም።

“የምንዛሪ ልውውጡ መጠን አወሳሰን በአማካይ የጊዜ ስሌት የአንድን አገር ብሄራዊ ኤኮኖሚ መሠረታዊ ይዞታ መረጃዎች ወይም ዳታ የሚያንጸባርቅ ሊሆን የሚገባው ነው። የፉክክር ብቃትን የሚያዛባ የምንዛሪ ልውውጥ ፖሊሲ ግን መወገድ ይኖርበታል”

የምንዛሪው ልውውጥ ዝቤት በበለጸገው ዓለም ብዙ ሲያነጋግር ዓለምአቀፉ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ኦክስፋም በበኩሉ ትኩረቱን ያሳረፈው በድሆች አገሮች ዕጣ ላይ ነው። ድርጅቱ ሶውል ላይ የሚሰበሰቡት የቡድን-ሃያ መንግሥት መሪዎች ባንኮችን በመሳሰሉት ታላላቅ የፊናንስ ተቋማት ላይ ጠንካራ ግብር በመጣል ገንዘቡን ለዓለም ድሃ ሕዝብ በስራ ላይ እንዲያውሉ በዛሬው ዕለት ጠይቋል። በፊናንስ ሽግግር፣ በምንዛሪ ንግድና ሌሎች መንገዶች በዓመት ቢያንስ 400 ቢሊዮን ዶላር ሊገኝ እንደሚችል ከወዲሁ በጥናት የተደረሰበት ጉዳይ ነው። ጥሪው ተቀባይነት ቢያገኝ’ና ገቢር ቢሆን ምንኛ በበጀ!

የዓለም ባንክ እንደሚገምተው በቅርቡ የኤኮኖሚ ቀውስ ለባሰ ድህነት የተዳረገው የዓለም ሕዝብ ቁጥር ከ 64 ሚሊዮን ይበልጣል። ያሳዝናል፤ ጥቂት ሃብታሞች ለፈጠሩት ቀውስ ድሆች አገሮች የዕዳው ተሸካሚዎች መሆናቸው። ሃቁ ይህ ሲሆን ቡድን-ሃያ ይህን የመለወጥ ግዴታውን መወጣት ይኖርበታል። ኦክስፋም ታዳጊ አገሮች በዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም ውስጥ የተሻለ ድምጽ እንዲኖራቸው፤ እንዲሁም የአፍሪቃን ሕብረት የመሳሰሉት የአፍሪቃ፣ የእሢያና የላቲን አሜሪካ የአካባቢ ማሕበራትም በቡድን-ሃያ ውስጥ ቋሚ መቀመጫ እንዲሰጣቸው ነው የሚያሳስበው።
የሆነው ሆኖ ጉባዔው ከሁለት ዓመት በፊት የተነሳበትን መንፈስ መልሶ በማስፈን የወደፊት ዕርምጃ ለማድረግ መቻሉ ለሁሉም ነገር ወሣኝ ነው የሚሆነው። የምንዛሪውን ልውውጥ ችግር በተመለከተ የቡድን-ሃያን ሊቀ-መነርነት ከደቡብ ኮሪያ የምትረከበው ፈረንሣይ በርዕስነት ጊዜዋ ለጉዳዩ ማዕከላዊ ትኩረት እንደምትሰጥ አስታውቃለች። በወቅቱ ለሶውሉ ጉባዔ ከሁሉም በላይ ዋናው ነገር ግን ቡድን-ሃያ ምንም እንኳ ቀውስ የወለደው ስብስብ ቢሆንም የሁሉም ዕጣ የተሳሰረ መሆኑን ማሳየቱና አንድነት መኖሩን ማስመስከር መቻሉ ነው።

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሰ