1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ባህላዊዉ ማስተማርያ እንቆቅልሽ እና ተረት

እሑድ፣ ታኅሣሥ 11 2002

በአገራችን በባህላችን የምናጫወታቸዉ እንቆቅልሾች ዘይቤያዊ አነጋገሮች የቋንቋ ማለት የመናገር የማዳመጥ ችሎታችንን እንደምናዳብርበት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ምሁራን አጫዉተዉናል።

https://p.dw.com/p/L9J7
ምስል AP

እንቆቅቅሽ ልጆችን በማስተማር ማህበራዊ ግንኙነትን ጉዳዮችን በማሳወቅ በኩል አገልግሎት ይሰጣልም ብለናል ታድያ እንቆቅልሽ ለህጻናት ብቻ ብለን የምንተወዉም አይደለም፣ በባህላችን በብዙ አካባቢዎች አዋቂቆዎች እንቆቅልህ ምናዉቅልህ ብለዉ በመጀመር ይጠያየቁት እንጂ እንደ እንቆቅልሽ ሁሉ ስዉር ጥያቄን በመጠያየቅ እራሳቸዉንም ሲፈታተኑበት ይታያል። ለምሳሌ ይሉናል መምህር መስፍን መሰለ «አንድ አባት ሊሞቱ ሲሉ ለልጆቻቸዉ ይናዘዙና ያላቸዉን ፈረሶች ለማዉረስ ይፈልጋሉ፣ አባት ያላቸዉን አስራ ሰባት ፈረሶች ድርሻ ድርሻቸዉን እንዲወስዱ ያደርጋሉ፣ አንደኛዉ አንድ ሶስተኛ፣ ሌላዉ አንድ ስድስተኛ፣ ሌላዉ ደግሞ አንድ ዘጠኛ እንዲወስዱ ያደርጋሉ። በዚህ መልኩ ግን ፈረሶቹ ሞተዉ ካልተከፋፈለ በስተቀር አባትየዉ እንዳሉት በትክክል ለልጆቹ ድርሻቸዉን ሊያገኙ አልቻሉም። ስለዚህ መፍትሄዉን ለማግኘት ልጆች ሽማግሌ ጋር ይሄዳሉ፣ ታድያ ሽማግሌዉ እንደ መፍትሄ የራሱን አንድ ፈረስ ይጨምርና፣ እንደተባለዉ ለልጆቹ ያከፋፍልና፣ የተረፈዉን አንድ ፈረስ ወደ ራሱ ይመልሳል» ይሄ ታድያ ይላሉ መምህር መስፍን በመቀጠል «ይህ አይነቱ ጥያቄ የእንቆቅልሽ አንዱ ገጽታ ብለን የምንለዉ ነዉ፣ አዋቂዎችም ለመፈተን ይሄዳል» ልጆችም ሆነ አዋቂቆች እንቆቅልሽ የሚጠያየቁት ስራ ሲሰሩ ሊሆን ይችላል፣ በአረሞ ላይ፣ በአጨዳ ላይ፣ ዉቅያ ላይ፣ ወይም ተሰብስበዉ የማህበር ጠላ ሲጠጡ ሊሆን ይችላል፣ በዝያን ግዜ አዕምሮን ለመፈተሽ፣ ግዜ ለማሳለፍያ፣ እንደ መዝናኛ ይሆናል። እንቆቅልሽ አዋቂዎች ጋር በዘፈን በግጥም መልክ ሊቀርብ ይችላል አንዳንድ ግዜ ሴትና ወንድ በጨዋታ መካከል እንቆቅልሽ ብለዉ ሊያቀርቡትም ይችላሉ። ለምሳሌ ሴትዋ እንዲህ ስትል በግጥም መልክ ጥያቄዋን ታቀርባለች
ከሎሚ ላይ ጠርሙስ፣ ከጠርሙስ ላይ ባላ፣ ከባላ ላይ ጎታ፣ ከጎታ ላይ ሳንቃ፣ ከሳንቃ ላይ ሽጉጥ፣ ከሽጉጥ ላይ መንቀል፣ ከመንቀል ላይ ደረት፣ ከደረት እላይ ኩስኩስት፣ ከኩስኩስት ላይ ኮከብ፣ ከኮከብ ላይ ዘንዶ፣ ከዘንዶ ላይ ሜዳ፣ ከሜዳ ላይ ቅል፣ከቅል ላይ ሃር፣ ከሃር ላይ ጤዛ፣ ከጤዛ ላይ ብር፣ ይህንን የፈታ ከኔ ጋር ይደር! ስትል ትጠይቃለች። ወንዱ በበኩሉ እንዲህ ሲል መልስ ይሰጣል
ሎሚዉ ተረከዝሽ፣ ጠርሙሱ ባትሽ ነዉ፣ ባላዉም ጭንሽ ነዉ፣ ጎታዉም ሆድሽ፣ሳንቃዉም ደረትሽ ነዉ፣ ሽጉጡም ጡትሽ፣ መንቀል አንገትሽ ነዉ፣በረዶዉ ጥርስሽ፣ ኩስኩስት አፍንጫሽ ነዉ፣ ኮከቡም አይንሽ፣ ዘንዶዉም ቅንድብሽ ነዉ፣ሜዳዉም ግንባርሽ፣ ቅሉም ራስሽ ነዉ፣ ጤዛዉም ነዉ ወዝሽ፣ ሃሩም ነዉ ጸጉርሽ፣
ብሩም ሳዱላሽ ነዉ፣ ይህንን ፈታሁኝ ይዤሽ ማደሪ ነዉ! ሲል ይመልሳል። ይህን አይነቱን የእንቆቅልሽ አጠያየቅ ዘዴ በአዋቂዎች ወይም በወጣቶች አካባቢ እንደ መዝናኛ ሲገለገሉበት ይታያል። መምህር መስፍን መሰለ ሌላም አላቸዉ «ዘጠኝ አፈ ደረቅ፣ ሁለት አፈ ለምለም፣ ሶሶስት አፈ ከፋታ፣ ቀሚሴን ይዉሰደዉ፣ ይህንን የፈታ፣ ብላ ሴትዋ አጠር ባለ መልኩ ትጠይቃለች። ተጠያቂ ወንዱም ዘጠኝ አፈ ደረቅ፣ ምንድነዉ ሁለት አፈከፋታ፣ ምንድ ነዉ ብሎ፣ በህብረተሰቡ ወይም በማህበራዊ ግንኙነት ዉስጥ ወይም በተፈጥሮ ካለ ነገር ዉስጥ መፈተሽ ይጀምራል። እናም ታድያ በመልሱ
ሁለት አፈ ለምለም፣ ሃምሌ ነሃሴ ነዉ፣ ዘጠኝ አፈ ደረቅ ዘጠኝ ወር በጋ ነዉ፣ ሶስት አፈ ከፋታ የወንድ ሱሪ ነዉ፣ ይህንን ከፈታሁ ቀሚስሽን ሳይሆን አንቺን ነዉ አንቺን ነዉ፣ ብሎ መልስ ያስቀምጣል» እናም እንቆቅልሽ ይላሉ በመቀጠል «ህጻናቱን ለማሳደግ አዋቂዉን ለማዝናናት አዕምሮን ለመፈተሽ ይጠቀሙበታል፣ ብለን ብንል የተሻለ ይሆናል ብዩ አስባለሁ» እንቆቅልሽ ጨዋታ በባህሪዉ ለልጆች ነዉ የተወሰነ አድርገን የምናስበዉ ግን ከዝያ አልፎ ዘመናዊ ዘፈኖቻችንም ዉስጥ እናገኘዋለን እንደዉም ይላሉ መምህር መስፍን የሙሉቀን ሙዚቃዎች ለዚህ ተጠቃሾች ናቸዉ። ተረትን እንቆቅልሽን በጥቂቱ አሰባስበናል ያድምጡ!

አዜብ ታደሰ