1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

በጎርጎሮሳዊው 2016 ዘጠኝ የውጭ ኩባንያዎች ብቻ በኢትዮጵያ ሥራ ጀምረዋል።

ረቡዕ፣ ጥቅምት 30 2009

በኢትዮጵያ የሚሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች ቁጥር ከቀደሙት አመታት አኳያ ሲነፃፀር በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱ እየተነገረ ነው። በጎርጎሮሳዊው 2016 በኢትዮጵያ የተሰማሩ ኩባንያዎች ቁጥር ዘጠኝ ብቻ መሆኑን አንድ የመዋዕለ-ንዋይ ትንተና ተቋም ገልጧል።

https://p.dw.com/p/2SQz8
Hawassa Umweltfreundlicher Industrie Park Äthiopien
ምስል DW/G.Tedla

ባለወረቶች ከኢትዮጵያ አፈግፍገዋል?

የአገራትን ኤኮኖሚ በተነፃፃሪ ግምገማ መዝነው ከሚያወጡ ሶስት ግዙፍ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ፊች ሬቲንግስ ከሁለት አመታት በኋላ ለኢትዮጵያ በሰጠው ትንበያ እንደጸና ነው። ኩባንያው ባለፈው ጥቅምት 9 ቀን 2009 ዓ.ም ይፋ ያደረገው ትንተና ለወራት በዘለቀ ድርቅ እና ኹከት የቀላቀለ ተቃውሞ ለተፈተነው የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ቢ ሰጥቶታል። የፊች ሬቲንግስ የመካከለኛው ምሥራቅ እና አፍሪቃ ቡድን ኃላፊ እና የኢትዮጵያ ተንታኝ  የሆኑት ኤሚሊ ዉ እንደሚሉት በአገሪቱ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ እና ኹከት አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ሕልውና የሚያሰጋ አይደለም።

«በጥቅምት ወር መጀመሪያ ይፋ ባደረግነው የኢትዮጵያ ግምገማ ነጠላ ቢ አፅድቀናል። ይህ የተረጋጋ ምልከታ ነው። ይህ በ2014 ለኢትዮጵያ ግምገማ ካደረግን ጊዜ ጀምሮ የመጀመሪያችን ነው። ይህ ግምገማ መሠረት ያደረገው በአገሪቱ ማክሮ ኤኮኖሚ መረጋጋት ላይ ነው። በአገሪቱ በቅርቡ የተከሰተው ኹከት እና ሕዝባዊ ተቃውሞ በሥልጣን ላይ ላለው መንግሥት አፋጣኝ ሥጋት ነው ብለን አናምንም።» 
መቀመጫውን በዩናይትድ ኪንግደም እንዳደረገው ቬሪስክ ማፕልክሮፍት መረጃ ከሆነ በኢትዮጵያ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ 24 ኩባንያዎች በሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ኪሳራ ደርሶባቸዋል። አስራ አንድ ፋብሪካዎች ተቃጥለዋል። ሰባት የውጭ የአበባ እና ፍራፍሬ አምራች ኩባንያዎች ንብረቶች ወድመዋል። ከእነዚህ መካከል ለ2000 ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል ፈጥሮ የነበረው የኔዘርላንድስ ኩባንያ-አፍሪቃ ጁስ ይገኝበታል። እስከ ጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም. ድረስ ከተመራጭ የውጭ መዋዕለ-ንዋይ መዳረሻ የምሥራቅ አፍሪቃ አገሮች ተርታ የምትመደበው ኢትዮጵያ አሁን ሁነኛ ፈተና ገጥሟታል። በምሥራቅ አፍሪቃ የተሻለ መረጋጋት የነበራት ኢትዮጵያ በውጭ ባለወረቶች ዘንድ የነበራት እይታ ከተቃውሞው በኋላ መቀየሩን  የቬርሲክ ማፕልክሮፍት ተቋም የምሥራቅ አፍሪቃ ተንታኟ ኤማ ጎርደን ይናገራሉ። 
«መረጋጋት ባጣው ቀጣና እጅግ የተረጋጋች ተደርጋ ትታይ የነበረችው ኢትዮጵያ በኩባንያዎች ዘንድ ባላት ተቀባይነት ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል። በርካታ ባለወረቶች በተለይም የአበባ እና ፍራፍሬ አምራቾች በተቃውሞ እና ኹከቱ መጠን ተገርመዋል። መንግሥት ደሕንነታቸውን ለማስጠበቅ ቃል ቢገባም ብዙዎቹ ጥቃት ተፈፅሞባቸዋል። ባለ ወረቶቹ ንብረቶቻቸው በሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች መጠቃቱን ገልጠዋል። ይህ በአገሪቱ በሚገኙት ባለ ወረቶች ላይ የከፋ ተፅዕኖ አሳድሯል። አንድ ኩባንያ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ያለውን ሥራ አቁሟል። ወደ 12 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ የደረሰበት ኩባንያው የወደመውን ንብረት መልሶ በመገንባት ሥራ መቀጠል አዋጪ አይደለም ብሎ አምኗል። ሌሎች በርካታ ኩባንያዎች ያላቸውን ምርጫ እየመረመሩ ይገኛሉ። መንግሥት የማካካሻ ጥያቄዎችን እየመረመረ በመሆኑ ይህ በኩባንያዎቹ ውሳኔ ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል። ኩባንያዎቹ አሁን የተፈጠረው መረጋጋት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተፈጠረ አሊያም ለረጅም ጊዜ የሚቀጥል እና ደሕንነታቸው የሚጠበቅ መሆኑን ማረጋገጥ ይሻሉ። ብዙዎቹ ኩባንያዎች ጥቃት የተፈጸመባቸው ከመንግሥት ጋር ባላቸው ቅርበት ብቻ ሳይሆን በአወዛጋቢው የመሬት አጠቃቀም እንደሆነ ይረዳሉ ብዬ እገምታለሁ።  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የመሬት አጠቃቀም ውዝግቡን የሚፈታ ባለመሆኑ በመፃዒው ጊዜ ኩባንያዎቹ ሥጋት ይኖርባቸዋል ማለት ነው።»
ድንበር ተሻጋሪ ኩባንያዎች በሌሎች አገራት እህት ኩባንያ በመፍጠር የሚጀምሯቸውን መዋዕለ-ንዋይ እየተከታተለ የሚመዘበው ግሪንፊልድ ትራከር ባወጣው ሐተታ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በኢትዮጵያ በሥራ ላይ የሚሰማሩ የውጭ ባለወረቶች ቁጥር ማሽቆልቆሉን ገልጧል። በኩባንያው መሠረት በመገባደድ ላይ በሚገኘው የጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም. በኢትዮጵያ በሥራ ላይ የተሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች ቁጥር ዘጠኝ ብቻ ነው። ይህ ቁጥር በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም. 25 በ2014 ደግሞ 31 ነበር። የኢትዮጵያ ተቃውሞ አሁን ከደረሰበት ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት ከአንድ አመት በላይ ፈጅቷል። መቀመጫቸው ለንደን ላይ ያደረጉት የቬሪስክ ማፕልክሮፍት ተንታኝ ኤማ ጎርደን የውጭ ኩባንያዎች ተቃውሞው በሥራቸው ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተፅዕኖ ይህን ያክል ይከፋል ብለው አልጠበቁም የሚል እምነት አላቸው። 

Äthiopien Gedeo Grundstücke Brand Protest
ምስል W/O Aynalem/R.Abeba

«ብዙዎቹን ያስደነገጠው የተቃውሞ እና የኹከቱ ደረጃ ይመስለኛል። በእነዚህ አካባቢዎች የተሰማሩት ኩባንያዎች በመሬት አጠቃቀም ዙሪያ ያለውን ውዝግብ እያወቁ ነው። ብዙዎቹ ኩባንያዎች ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ሥራ በመፍጠር አዎንታዊ ግንኙነት ለማዳበር ሞክረዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች ያገር ሽማግሌዎች ተቃዋሚዎቹን በማስቆም ጥቃት መከላከላቸው ተሰምቷል። ነገር ግን ከአካባቢው ነዋሪዎች ሠራተኛ በመቅጠር፤ ሥራ በመፍጠር እና ገንዘብ ወጪ በማድረግ አወዛጋቢው የመሬት አጠቃቀም የሚፈጥረውን አደጋ ለማስቀረት ሙከራዎች ነበሩ።  ያልተረዱት ነገር ይመስለኛል በኦሮሚያ የነበረው የሕዝብ ቅሬታ ኩባንያዎቹ ከገመቱት እና ከጠበቁት በላይ እንደሆነ ነዉ።»

Äthiopien 40. Jahrestag TPLF
ምስል DW/T. Weldeyes


የኢትዮጵያ የውጭ መዋዕለ ንዋይ ምንጭ የሆኑ አገሮች ለዜጎቻቸው ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎች በመስጠት ላይ ናቸው። ግሪንፊልድ ትራከር ያወጣው ዘገባ እንደሚጠቁመው ከጎርጎሮሳዊው ኅዳር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ከዩናይትድ ስቴትስ፤ ደቡብ አፍሪቃ፤ ሕንድ፤ ቱርክ፤ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች፤ ጀርመን እና ዩናይትድ ኪንግደም አንድም ኩባንያ በኢትዮጵያ የመዋዕለ-ንዋይ ሥራ አልጀመረም። ኩባንያው ይህን እጅግ አሳሳቢ ሲል ይገልጠዋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጠን ያደረግንው ሙከራ አልተሳካም። የፊች ሬቲንግስ የመካከለኛው ምሥራቅ እና አፍሪቃ ቡድን ኃላፊ እና የኢትዮጵያ ተንታኝ   የሆኑት ኤሚሊ ዉ የአገሪቱ ፖለቲካ እጅጉን አሳሳቢ እንደሆነ ይናገራሉ።


«አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ሁኔታ አጥጋቢ እና ጊዜውን የጠበቀ መረጃ ማግኘት አንዳንድ ጊዜ እንቸገራለን። በኢትዮጵያ በተለያዩ ብሔሮች መካከል ያለው ግንኙነት በቀላሉ ሊሰበር የሚችል ነው። በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በንፅፅር አነስተኛ ቁጥር ያለዉን ብሔር የሚወክል ነው። ሊፈጠር የሚችለው የከፋ ነገር የርስ በረስ ጦርነት ነው። አሁንም ግን በኢትዮጵያ የብሔራዊ አንድነት ሥሜት አለ። ነገር ግን በመንግሥት ላይ ያለው ቅሬታ፤ የፖለቲካ ነፃነት እጦት ወደ ከፋ ደረጃ ሊያደርስ የሚችል ነው።»
ዓለም አቀፍ ኩነቶችን እየተከታተለ የሚተነትነው እና ትንበያ የሚሰጠው ጂኦፖለቲካል ፊውቸር የተሰኘ የድረ-ገፅ መፅሔት ወቅታዊው የኢትዮጵያ አለመረጋጋት በኤኮኖሚው ላይ የአጭር ጊዜ ጫና ቢያሳድርም የከፋ የረጅም ጊዜ ተፅዕኖ አይኖረውም ብሏል። የኢትዮጵያ መንግሥት አሁንም የምዕራባውያን መንግሥታት ድጋፍ እንዳለው የጠቆመው መጽሔቱ ተቃዋሚዎችም የተበታተኑ መሆናቸውን ጠቅሷል።  ኤማ ጎርደን በኢትዮጵያ ለሚገኙም ይሁን ወደ ፊት መሰማራት ለሚሹ የውጭ ኩባንያዎች ጊዜው የመጠባበቂያ እንደሆነ ይናገራሉ ተንታኟ የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ባለሐብቶቹን ሥጋት የሚቀርፍበት አንዳች መንገድ ያሻዋል ባይ ናቸዉ።

«ለብዙዎቹ የውጭ ባለወረቶች የአሁኑ ወቅት የመጠባበቂያ ነው። አሁን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዴት እንደሚሰራ፤ መንግሥት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ ምን ማድረግ እንዳቀደ ማወቅ ይሻሉ። ይመስለኛል ብዙዎቹ በኢትዮጵያ በሥራ ላይ የተሰማሩትም ይሁኑ ወደፊት መሰማራት የሚፈልጉት ባለወረቶች መንግሥት ለተቃዋሚዎች ተገቢውን ምላሽ መስጠቱን መመልከት ይፈልጋሉ። በጸጥታ ኃይል የሚጠበቅ ደኅንነት ሳይሆን ጥያቄዎቹ ለዘለቄታው ምላሽ ማግኘታቸውን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ። ምክንያቱም በጥበቃ የሚገኝ ደኅንነት ዘላቂ አይሆንም።» 


የትንተና ተቋማቱም ይሁን ባለሙያዎቹ አሁን ጋብ ያለው የኢትዮጵያ ተቃውሞ እንደ ማስጠንቀቂያ ሊወሰድ እንደሚገባው አበክረው ያስጠነቅቃሉ። ተቃውሞው አሁን ያሳደረው ተፅዕኖ  የከፋ ቢሆንም በጊዜ መፍትሔ ካልተበጀለት የውጭ ባለሐብቶቹን ማሸሽ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን ደሕንነት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል ባይ ናቸው። 


እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሰ