1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቤተ-እስራኤላውያኑን የፈተነው ስር የሰደደ ዘረኝነት

ሰኞ፣ ሚያዝያ 26 2007

የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት ሮይቭን ሪቭሊን እስራኤል በኢትዮጵያ አይሁዶች አያያዝ ላይ ስህተት መፈጸሟን አምነዋል።ጠቅላይ ሚኒስቴር ቤኒያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው በአገሪቱ የተንሰራፋውን ዘረኝነት ለማስወገድ በጋራ ልንቆም ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/1FK1y
Jerusalem: Demonstration äthiopischer Juden
ምስል Reuters

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቤኒያሚን ኔታንያሁ የቤተ-እስራኤላውያን ማህበረሰብ መሪዎችን ለሶስት ሰዓታት ካነጋገሩ በኋላ «ዘረኝነትን ለማስወገድ በጋራ መቆም ይገባናል።» ሲሉ መናገራቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል።ቤተ-እስራኤላውያን በሚደርስባቸው መገለልና መድሎ እንዲሁም የፖሊስ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ላይ ከመሪዎቹ ጋር የመከሩት ኔታንያሁ መንግስታቸው ለችግሩ ያስቀመጠው የአጭርና የረጅም ጊዜ መፍትሄ ስለመኖሩ የተሰማ ነገር የለም።

ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በእየሩሳሌም ከተማ የተጀመረው የቤተ-እስራኤላውያኑ ተቃውሞ ትናንት ወደ ቴል አቪቭ ተዛምቷል። ሁለት ፖሊሶች አንድ ቤተ-እስራኤላዊ ወታደር ሲደበድቡና ሲያንገላቱ የሚያሳይ የሁለት ደቂቃ የቪዲዮ ምስል መሰራጨቱን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ የሚያወግዘው የአሁኑን ድርጊት ብቻ ሳይሆን ለዘመናት ተቀብሮ የከረመውን ዘረኝነት ጭምር መሆኑን በእስራኤል የኢትዮጵያ አይሁዶች ማህበር ቃል አቀባይ ሃና ኤላዛር ይናገራሉ።

netanjahu israel ministerpräsident regierung
ምስል picture-alliance/dpa

«በትምህርት ቤትም ይሁን፤በወታደርነትም ይሁን በስራችን ቦታም ይሁን ብዙ ችግሮች አሉ።ወታደሩን ፖሊስ ሲመታው እነዚህ ችግሮች በአንድ ላይ ነው የወጡት።ይህን የተቃውሞ ሰልፍ ያደረጉት ኢትዮጵያን የማያውቁ በእስራኤል የተወለዱ ልጆች ናቸው።ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያዊ እንጂ እንደ እስራኤላዊ አድርገው አይመለከቷቸውም። እነዚህ ልጆች እኛ የተወለድንው እዚህ(እስራኤል) ነው። መብታችንን መጠበቅ አለባችሁ ነው ያሉት።»

በጎርጎሮሳዊው የዘመን አቆጣጠር በ1980ዎቹና 90ዎቹ ወደ እስራኤል የተጓዙት የኢትዮጵያ አይሁዶች ከስምንት ሚሊዮን የአገሪቱ ዜጎች መካከል 135,500 ያህል መሆናቸውን የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘገባ ይጠቁማል። ከእነዚህ መካከል 86,000 ያህሉ ከኢትዮጵያ የተጓዙ ሲሆኑ 50,000ዎቹ ደግሞ ኢትዮጵያን የማያውቁ በእስራኤል የተወለዱ ናቸው። ከኢትዮጵያ የተጓዙትም ይሁኑ በእስራኤል የተወለዱት ከቀደሙት የአገሪቱ አይሁዳውያን ጋር የመዋሃዱ ጉዳይ ግን እንዲህ ቀላል አልሆነላቸውም። የማህበረሰባዊ ጉዳዮች ጥናት ተቋም የሆነው ብሮክዳሌ ማዕከል ይፋ ባደረገው ጥናት የአንድ ወንድ እስራኤላዊ አማካኝ የገቢ መጠን 10,000 ሼክል ወይም 2,500 ዶላር አካባቢ ሲሆን የቤተ-እስራኤላዊ ግን 7,000 ሼክል ወይም 1,800 ዶላር አካባቢ ነው። በትምህርት እና የስራ እድል ጥቁሮቹ አይሁዳውያን ከነጮቹ ጋር አይስተካከሉም። የመኖሪያ ቤት የማግኘት ጉዳይም ቢሆን ከሌላው እስራኤላዊ በተለየ ለእነሱ ፈተና ነው።

በዕለተ እሁዱ የቴል-አቪብ ተቃውሞ ከ10,000 በላይ ሰዎች መሳተፋቸውን አስተባባሪዎቹ ቢናገሩም የአገሪቱ ፖሊስ ቁጥሩን ወደ 3,000 ዝቅ አድርጎታል። የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሮይቭን ሪቭሊን እስራኤል በኢትዮጵያ አይሁዶች አያያዝ ላይ ስህተት መፈጸሟን አምነዋል። «ተቃዋሚዎቹ በእስራኤል ማህበረሰብ ልብ ውስጥ የተሰነቀረውን ቁስል አጋልጠዋል።» ያሉት ፕሬዝዳንቱ «ስህተት ፈጽመናል ችግሮችን በአግባቡ አልተመለከትንም፤አላደመጥንም።» ሲሉ መናገራቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል። ሃና ኤላዛር እስራኤላውያን «እንደ አዲስ ገቢ፤ገና ምንም የማናውቅ አድርገው ነው የሚያዩን» ሲሉ ከኢትዮጵያ ከ30 አመታት በፊት እስራኤል ለገቡት አይሁዳውያን ያላቸው አመለካከት አሁንም አለመቀየሩን ያስረዳሉ።

Israel Tel Aviv Protestaktion äthiopische Juden Ausschreitungen
ምስል Reuters/Baz Ratner

በእለተ እሁዱ የቤተ-እስራኤላውያን የአደባባይ ተቃውሞ በበርካታ ሰዎች ላይ አነስተኛ የአካል ጉዳት መድረሱንና 43 ሰዎች መታሰራቸውን የአገሪቱ ፖሊስ አስታውቋል። ተቃዋሚዎች ድንጋይና ጠርሙሶች ሲወረውሩ ፖሊስ በአስለቃሽ ጭስና ተተኳሾች ተቃውሞውን ለመበተን ጥረት ማድረጉን የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ድብደባና እንግልት ተፈጸመበት የተባለውን ወታደር አግኝተው ያነጋገሩ ሲሆን ጉዳዩን ፈጸሙ የተባሉት ፖሊሶች ለጊዜው ከስራ ታግደዋል። ሃና ኤላዛር ቤተ-እስራኤላውያኑ ያካሄዱት የተቃውሞ ሰልፍ ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት አላቸው።«በተለያዩ ጊዜ በሚነሱ ተቃውሞዎች አንዳንድ ማጉረምረሞች በመንግስት ባለስልጣናት ችግሩን ለመፍታት ቃል ይገባል።ነገር ግን በተግባር ምንም የሚውል ነገር የለም።» የሚሉት የአፍሪካ ስደተኞች ልማት ማዕከል ሃላፊ አቶ ዮሃንስ ባዩ «ስር ለሰደደው ዘረኝነት ስር ነቀል ለውጥ ያሻዋል።»ሲሉ ይናገራሉ።

እሸቴ በቀለ

ተክሌ የኋላ