1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሊ ብሔራዊ የአንድነት  ጉባኤ

ሰኞ፣ መጋቢት 18 2009

በማሊ የሀገሪቱ መንግስትና በተቃዋሚዎች መካከል የብሄራዊ አንድነት ጉባኤ ተጀመረ። በሀገሪቱ ዋና ከተማ ባማኮ በዛሬዉ ዕለት የተጀመረዉ ጉባኤ ሰላምን፤ ብሄራዊ አንድነትና እርቅን ዋና አላማ ያደረገ ነዉ ተብሏል።

https://p.dw.com/p/2a4Qn
Gemeinsame Patrouillie von Rebellen und Soldaten in Mali
ምስል picture alliance/dpa/B.Ahmed

The conference of national unification in Mali - MP3-Stereo

ከ300 በላይ ተሳታፊዎች ይገኙበታል የተባለዉ ይህ ጉባኤ፤ በሀገሪቱ ለአመታት የዘለቀዉን የርስበርስ ጦርነት እልባት ይሰጣል በሚል  ብዙዎች ተስፋ ቢጥሉበትም፤ ከወዲሁ አንዳንድ ተቃዋሚወች ከጉባኤዉ ራሳቸዉን ማግለላቸዉን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ከባማኮ ዘግቧል።

በጎርጎሮሳዊዉ የዘመን ቀመር በ1960 ዓ,/ም ከፈረንሳይ ነጻነቷን ያገኘችዉ ምእራብ አፍሪካዊት ሀገር ማሊ፤ በአፍሪካ በጥጥ ምርቷ ትታወቃለች። ሀገሪቱ ከቅኝ ተገዢነት ነጻ ብትወጣም በጎሮጎሮሳዊዉ 1992 ዓ,ም ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ለ23 ዓመታት በአምባ ገነን አገዛዝ ስር ቆይታለች። ማሊ ምንም እንኳ የባህር በር ባይኖራትም ከአዲሱ የስርአት ለዉጥ ማግስት በኢኮኖሚ እድገት፤ በዲሞክራሲ እንዲሁም በማህበራዊ መረጋጋት ረገድ አዎንታዊ ለዉጦች አሳይታ ነበር። 

 አዎንታዊ ለዉጡ ግን የዘለቀዉ ለ 10 ዓመታት ብቻ ነዉ። በጎርጎሮሳዊዉ የዘመን ቀመር  ከ2012 ዓ,ም ጀምሮ አዝዋድ የተባለዉን ሰሜናዊ የሀገሪቱን ክፍል ለመገንጠል ነፍጥ ባነሱ የተዋሬግ አማጺያንና ሀገሪቱ በሸሪያ እንድትተዳደር የሚፈልጉ አክራሪ የእስልምና ኃይሎች በየፊናቸዉ ከመንግሥት ጋር ግጭት ዉስጥ በመግባታቸዉ፤ ማሊ በእርስበርስ ጦርነትና በተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶች እየታመሰች ትገኛለች። በዚህም ምክንያት በሀገሪቱ 95 በመቶ የሚሆነዉ ወጣት ለሥራ አጥነት ተጋልጧል ። በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል ጋዮ ከተማ በአንዲት አነስተኛ  የመዝናኛ ስፍራ  ቴሌቪዥን እየተመለከተ ካትሪን ጋንዝለር ያገኘችዉ ወጣት ኢሳ ቦናካና እንደሚለዉ አብዛኛዉ ወጣት  በየቀኑ በእንዲህ ያሉ  ስፍራወች ተቀምጦ ሲቆዝም ይዉላል። 
                        
«እዚህ ምንም የሚሠራ ነገር የለም። ፋብሪካዎች የሉም። እዚህ ለሚዉሉት ወጣቶች የሥራ ዕድል ለማመቻቸት መዋዕለ ንዋይ አልፈሰሰም። ማንም ሥራ ማግኘት አይችል ነዉ። ተመልከቱ  ሥራ ፈልጎ ማግኘት ስለማይቻል ነዉ በየቀኑ እዚህ የምንመጣዉ። ተስፋ የምናደርገዉ መንግሥት ችግራችንን አዳምጦ ሥራ ይፈጥርልናል ብለን ነዉ። ነገር ግን በአሁኑ ስአት ምንም የለም።»

የአዝዋድ ነፃ አዉጭ ብሄራዊ ንቅናቄ በምህጻሩ ኤም ኤን ኤል ኤ የተባለዉ የተዋሬግ አማጽያንና የአንድነት ንቅናቄ የተባለዉ እስላማዊ አክራሪ ቡድን ከመንግሥት ጋር በሚያደርጉት ግጭትና የሽብር ጥቃት የተነሳ በሀገሪቱ ቱሪዝምና የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ከማሽቆልቆሉ ባሻገር ለሀገሬዉ በሰላም ወጥቶ መግባትም ፈተና ሆኗል። በጋዮ ከተማ የሶንጋይ ጎሳ ባህላዊ መሪ ሙሳ ማይጋ ይናገራሉ።

«በጣም ግልጽ ነዉ። የፀጥታዉ ሁኔታ እዚህ በቀላሉ የተጠበቀ አይደለም። በነጻነት መንቀሳቀስ አልቻልንም። በጣም ተገድበናል። ይህ መሆን አልነበረበትም።»

ይህንን ችግር ለመፍታት በተለያዩ ጊዜያት በአማጺያኑና በመንግሥት መካከል ድርድሮች ተካሂደዋል። እስካሁን ግን የረባ መፍትሄ አልተገኘም። በሀገሪቱ ዋና ከተማ ባማኮ  በመንግስትና በተቃዋሚወች መካከል የብሄራዊ አንድነትና እርቅ ጉባኤ በዛሬዉም እለት  ተጀምሯል።

Mali Bamako - Debatte zu Migration
ምስል DW/D. Köpp

በጉባኤዉ ከ300 በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ የሚጠበቅ ሲሆን ትኩረቱን በጎርጎሪዮሳዊዉ 2015ዓ,ም በተፈረመዉ የሰላም ስምምነት መሠረት፤ የሰላም፤ የእርቅና የብሔራዊ አንድነት መግባቢያ ሰነድ ማጽደቅ ላይ ያደረገ ነዉ። የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ቦባካር ኪታ በጉባኤዉ የመክፈቻ ስነስርአት «የምንፈልገዉ የተዋሃደች ማሊን በመሆኑ ለሁሉም በራችን ክፍት ነዉ» ብለዋል። ጉባኤዉ ከአስር አመት በላይ በሀገሪቱ የዘለቀዉን ቀዉስ ይፈታል የሚል ተስፋ የተሰነቀበት ቢሆንም ከባማኮ የወጣ ዘገባ እንደሚያመለክተዉ የቀደሞ አማፅያን እና የማሊ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጉባኤዉ ራሳቸዉን አግለዋል። የዛዋድ የተባበረዉ ንቅናቄ፣ የቀድሞ የአማፅያን ጥምረት እንዲሁም የማሊ የተቃዋሚ ቡድኖች፤ ለዉይይትና ለዝግጅት የተሰጠዉ ጊዜ አነስተኛ መሆን  በጉባኤዉ እንዳይገኙ እንዳደረጋቸዉ አስታዉቀዋል። እንዲያም ሆኖ ባህላዊዉ የጎሳ መሪ ሙሳ ማያጋ፤ በማሊ ቀዉሱ እንዲያበቃ ከተፈለገ ለሀገር ፍቅር ሲባል ራስን ማሸነፍ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል። ጉባኤዉ እስከ እሁድ ይዘልቃል።

ካትሪን ጋንዝለር/ፀሐይ ጫኔ

ሽዋዬ ለገሠ