1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ብሪክስና የጋራ ልማት ባንክ ውጥኑ

ረቡዕ፣ የካቲት 27 2005

ብሪክስ በሚል አሕጽሮት የሚጠሩት በተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚገኙ አምሥት ሃገራት በቅርቡ ደቡብ አፍሪቃ ከተማ ደርባን ላይ የመሪዎች ጉባዔ ያካሂዳሉ።

https://p.dw.com/p/17qxX
ምስል Reuters

የስብስቡ መንግሥታት መሪዎች አፍሪቃ ውስጥ ሲሰበሰቡም ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን ቡድኑ ከጊዜ ወደጊዜ ክብደት እያገኘ መምጣቱ የተሰወረ ነገር አይደለም። በበለጸገው ዓለም ፊት የማይናቅ ሃይል እየሆነ በመሄድ ላይ ይገኛል።

የብሪክስ መሪዎች ጉባዔ ዋና ዓላማ ለቡድኑ ጥንካሬና ተደማጭነት ታላቅ ድርሻ የሚኖረው የጋራ የልማት ባንክ እንዲቋቋም በተያዘው ጥረት ወሣኝ ዕርምጃ ማድረግ ነው። ከጉባዔው የግድ ስኬት ይጠበቃል። የብሪክስ የልማት ባንክ ሕያው ከሆነ በዕውነትም በብዙዎች ዘንድ ትልቅ ዕርምጃ እንደሚሆን ይጠበቃል። ይህ የደቡብ አፍሪቃ ጥቁሮች የንግድ ም/ቤት ጸሐፊ የሳንዲል ዙንጉ ዕምነትም ነው።

በብሪክስ መንግሥታት መካከል እያደገ ያለውን ንግድ ለተመለከተ እርግጥም የባንኩ አስፈላጊነት ጨርሶ አያጠያይቅም። ምክንያቱም ሳንዲል ዙንጉ እንደሚያስረዱት እነዚህ ሃገራት በወቅቱ የልማት ገንዘብ አቅራቢ ተቋማት በዓለም ባንክና በዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም IMF ዘንድ የደረሱበት የመሰላቸት ሁኔታ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ዋናው ችግርም በተለይ የተቋማቱ ቢሮክራሲ ነው። ገንዘብ ለማግኘት ውጣ ውረዱ ይበዛል።

ብድር ለመስጠት በገንዘብ ተቋማቱ የሚቀመጠው መስፈርት፣ ከብድሩ የተሳሰረው ቅድመ-ግዴታና ብድር የመስጠቱ ውሣኔ ጉትትነት እንግዲህ ሲበዛ አታካቾች ናቸው። ብሪክስ ሃገራት ደግሞ ዛሬ ሰፊ መዋቅራዊ ግንባታ በማካሄድ ላይ የሚገኙ እንደመሆናቸው መጠን በነበረው ሁኔታ ሊቀጥሉ አይችሉም። ለዚህም ነው የራስ ልማት ባንክን የማቆሙ አስፈላጊነትና በዚሁም ቢሮክራሲን ማምለጡ አጣዳፊ እስከመሆን የደረሰው።

BRIC Medwedew
ምስል picture alliance/dpa

እንደ ስብስቡ ፍላጎት የሚቋቋመው የልማት ባንክ ቁልፍ ማተኮሪያ የሚያደርገው በብሪክስ መንግሥታት ክልል ውስጥ ለሚካሄደው ሰፊ መዋቅራዊ ግንባታ ገንዘብ ማቅረቡን ነው፤ ፍሮንቲየር አድቫይዘሪይ በመባል የሚታወቀው ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ተቀማጭ የሆነ የመጤ ገበዮች አማካሪ ቡድን የስልታዊ ምርምር መሪ ሃና ኤዲንገር የሚናገሩት። የደቡብ አፍሪቃው የፊናንስ ሚኒስትር ፕራቪን ጎርድሃን እንዳስረዱትም ባንኩ የታቀደው የውስጥ ቁጠባን ለማዳበርና በአዳጊ አካባቢዎች የሚካሄዱ ፕሮዤዎችን ለማገዝ ነው።

በምርምሩ ተቋም ግምት በተለይም በሕንድና በደቡብ አፍሪቃ ይህን መሰሉን ፕሬዤ ለማራመድ ብሪክስ ሃገራት በሚቀጥሉት አሥርና ሃያ ዓመታት ውስጥ ቢያንስ 15 ትሪሊየን ዶላር ሳያስፈልጋቸው አይቀርም። በሌላ በኩል በወቅቱ አፍሪቃ ውስጥ በመዋቅራዊ ግንባታ ረገድ 480 ቢሊዮን ዶላር ጉድለት እንዳለ ነው ጥናቶች የሚያመለክቱት። እንግዲህ አዲሱ የብሪክስ ባንክ ይህን ችግር ለመቋቋም የሚረዳ እንደሚሆን ይጠበቃል።

የአፍሪቃ ልማት አዲስ ሽርክና ዋና ሃላፊ ሊኔት ቼን በፊናቸው እንደሚሉት የብሪክስ ልማት ባንክ አፍሪቃ የምትመርጠው አበዳሪ ወገን ሊሆን ይገባዋል። አፍሪቃ ውስጥ ሌሎቹ የልማት ባንኩ ገንዘብ ሊፈስባቸው የሚችሉ ዘርፎች አረንጓዴ ቴክኖሎጂ፤ ማለት የተፈጥሮ እንክብካቤን የጠበቁ ፕሮዤዎች፣ ባዬ-ነዳጅ፣ ግድቦችና ኑክሌያር የሃይል ማመንጫ ይዞታዎችን ይጠቀልላሉ። ሆኖም አፍሪቃ ውስጥ ስራ ላይ የሚውለው የብሪክስ ልማት ባንክ ገንዘብ ድርሻ በጅምሩ መለስተኛ እንደሚሆን ነው ሃና ኤዲንገርን የመሳሰሉ ተመራማሪዎች የሚጠብቁት።

በነዚሁ አመለካከት አፍሪቃ ውስጥ ተፈጥሮን ለጠበቁ ፕሮዤዎች ገንዘብ መውጣቱ ባይቀርም በመሠረቱ ግን ዘርፉ የአዲሱ ባንክ ቀደምት ማተኮሪያ አይደለም። ዘርፉ ትኩረትን ሊስብ የሚችለው የአካባቢ ትስስርንና የአካባቢ ገበዮችን ለማዳበር አገር አቋራጭ የሆኑ የማመላለሻና የኤሌክትሪክ ሃይልን የመሳሰሉ ፕሬዤዎች ሲታሰቡ ነው።

Infografik Wachstumsraten BRICS-Staaten und Lateinamerika

በያዝነው የጎርጎሮሳውያኑ መጋቢት ወር መጨረሻ ደርባን ላይ የሚካሄደው የብሪክስ መንግሥታት መሪዎች ጉባዔ ቀደም ሲል እንደጠቀስነው በአፍሪቃ ምድር የመጀመሪያው ሲሆን ባለሥልጣናት የፖለቲካው ክበብ ጽኑ የኤኮኖሚና የፊናንስ መሠረትም እንዲኖረው ለማድረግ በርካታ ስብሰባዎችን ሲያካሂዱ ነው የቆዩት። አዲሱ ባንክ የብሪክስን የትብብር መንፈስ እንደሚያጠነክርና ድርጅታዊ መሠረቱንም የጸና እንደሚያደርግ የቅርብ ታዛቢዎች ዕምነት ነው።

ለግንዛቤ ያህል ብሪክስ በሚል አሕጽሮት የተጠቃለሉት አምሥት ተራማጅ ሃገራት ከ 2,9 ሚሊያርድ የሚበልጥ ሕዝብ ሲኖራቸው ይህም ወደ ሰባት ሚሊያርድ ከሚጠጋው የዓለም ሕዝብ ቁጥር አንጻር አርባ በመቶው መሆኑ ነው። ስብስቡ በ 13,901 ሚሊያርድ ዶላር ገደማ ሃያ በመቶውን የዓለም አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት ድርሻም ይይዛል። ይህም በዓለም ንግድ፣ ኤኮኖሚና ፖለቲካ ረገድ ያለውን ክብደት ጉልህ አድርጎ የሚያሳይ ነው።

ስብስቡ እስካሁን ከጎርጎሮሳውያኑ 2009 አንስቶ ዓመታዊ የመሪዎች ጉባዔ ሲያካሂድ ደቡብ አፍሪቃ በቻይና አግባቢነት ዓባል የሆነችው በ 2011 ነበር። በቅርቡ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የሚካሄደው እንግዲህ አምሥተኛው የመሪዎች ጉባዔ ሲሆን ምናልባትም ታላቁ ሊባል ይችል ይሆናል። ለማንኛውም ስብስቡ ወደፊት በዓባላት ደረጃም እየሰፋና በዓለም ኤኮኖሚ ላይ ያለውን ተጽዕኖም እያጠነከረ መሄዱ የሚቀር አይመስልም። እርግጥ እዚህ ላይ የቻይና የወደፊት ዕርምጃ ጎጂም ሆነ ገምቢ የራሱ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

ወደተነሣንበት ርዕስ እንመለስና የብሪክስ ልማት ባንክ መቋቋም ለስብስቡ ታሪካዊ ዕርምጃና ተሰሚነትን የሚያዳብር፤ እንዲሁም ከራሱ የወጣ፤ ራሱ የጸነሰው የመጀመሪያው ድርጅታዊ አካል ነው የሚሆነው። ሃና ኤርዲንገር እንደሚያስረዱት በብሪክስ ውስጥ ከወዲሁ በርካታ የስራ ቡድኖችና መድረኮች ቢኖሩም የባንኩ መፈጠር ዓለምአፈቀፉን የፊናንስ ስርዓት ለመጠገን ሃሣብ በማቅረብ ከተወሰነ ከፖለቲካ ውይይት መድረክ የቡድኑን ጥቅም ወደሚያስጠብቅ የደቡቡ ዓለም ሃይል መራመዱን የሚያረጋግጥ ነው የሚሆነው።

ትልቅ አነጋገር ፤ ትልቅ ተሥፋ፤ ሆኖም ሊሳካ የሚችል ነገር ነው። የደቡብ አፍሪቃ ስታንዳርድ ባንክ ባለሙያዎች የጋራው ልማት ባንክ በጅምሩ የ 50 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል ሊኖረው እንደሚችል ይገምታሉ። አምሥቱ የብሪክስ ዓባል መንግሥታት ብራዚል፣ ሩሢያ፣ ሕንድ፣ ቻያናና ደቡብ አፍሪቃ እያንዳንዳቸው አሥር ቢሊዮን አዋጥተው ማለት ነው። የባንኩ ሕያው መሆን ለግል ባለሃብቶች በአፍሪቃ በሚካሄዱ ድንበር አቋራጭ ንግዶች ዋስትና እንዲሰማቸው የሚያደርግ እንደሚሆንም ተሥፋ የሚጥሉ አሉ።

BRICS Gipfel in Neu Delhi März 2012
ምስል Reuters

ለማንኛውም ተቀማጭነቱ ቻይና ውስጥ የሆነው የደቡብ አፍሪቃ ስታንዳርድ ባንክ የፊናንስ ባለሙያ ጀረሚይ ስቲቭንስ እንደሚገምቱት የደርባኑ የመሪዎች ጉባዔ ብዙ ነገሮችን ግልጽ ማድረጉ አይቀርም። የሆነው ሆኖ ባንኩ ብሪክስ ውስጥ ይበልጥ ጥንካሬና ትስስር ለማስፈኑ ቅድሚያን እንደሚሰጥ ከወዲሁ የሚጠበቅ ነው። የልማት ባንኩ እርግጥ ዝግ ብሎ ይጀምር እንጂ ከጊዜ ጋር እየሰፋ መሄዱ ግን እንደማይቀር ጀረሚይ ስቲቨንስን የመሳሰሉ የፊናንስ አዋቂዎች ይተነብያሉ። ከፖሊሲ አንጻር ሲታይም የብሪክስ ልማት ባንክ አማራጭ የገንዘብ ምንጭ እንጂ የዓለም ባንክና የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም ተቀናቃኝ አይሆንም።

በብሪክስ ስብስብ ውስጥ ታላቅ ተጽዕኖ ያላት በኤኮኖሚ ሃያሏ ቻይና ስትሆን የአዲሱ ባንክ መቀመጫ ወይም ማዕከል ቫንግሃይ ላይ እንዲሆንና የአገሪቱን ምንዛሪ ዩዋንን መገልገያው እንዲያደርግ ግፊት ማድረጓ የማይቀር ነው። የቻይና ባለሥልጣናት ዓላማም የአገሪቱ ምንዛሪ የኤኮኖሚዋን ያህል ክብደት እንዲያገኝና አገር ውስጥ ያሉ ኩባንያዎቿና ባለሃብት ዜጎቿ በራሳቸው ምንዛሪ መነገድ እንዲችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው።

እርግጥ አንዳንድ የፊናንስ ታዛቢዎች እንደሚሉት የዩዋን በብሪክስ ልማት ባንክ ውስጥ መነገጃ መሆን ከዝና አልፎ ለቻይና ያን ያህል ጥቅም ይኑረው አይኑረው ገና ግልጽ አይደለም። ለነገሩ የቻይና ፍላጎት ቢሟላ እንኳ ብሪክስ ከሌላ ሶሥተኛ ወገን ጋር የፊናንስ ልውውጥ ማድረግ በሚኖርበት ጊዜ ዩዋኑን ወደ ዶላር መመንዘሩ ግድ ነው የሚሆነው።

ያም ሆነ ይህ የብሪክስ ልማት ባንክ መቋቋም ለአዳጊ ሃገራት አማራጭ የገንዘብ ምንጭን የሚከፍት ሲሆን በሌላ በኩል የዋሺንግተኑ ዓለምአቀፍ የገንዘብ ተቋማት ተጽዕኗቸውን እንዲያለዝቡ እያደር ግፊት ሊፈጥር የሚችልም ነው። ለታዳጊው ዓለም ደግሞ ይህ መጥፎ አይደለም።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ