1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ብርቱካንና ሙዝን ያነገበዉ የኬንያ ህገመንግት ህዝበ ዉሳኔ

ሰኞ፣ ኅዳር 12 1998

ኬንያዉያን በዛሬዉ ዕለት ሲያወዛግብ በሰነበተዉ አዲስ በተረቀቀዉ ህገ መንግስታቸዉ ላይ ዉሳኔያቸዉን ይሰጣሉ። የህዝበ ዉሳኔ አሰጣጡን ክንዉንም ለመታዘብ የአዉሮፓዉ ህብረትን ጨምሮ ወደ 150 የሚደርሱ ዓለም ዓቀፍ ታዛቢዎች ተገኝተዋል። አዲሱን ህገ መንግስት በመቃወም በሐምሌም ሆነ ባለፈዉ ወር በዋና ከተማዉ ናይሮቢና በሞምባሳ በተካሄዱት ሰልፎች ከፖሊስ ጋር ግጭት ተፈጥሮ በሰዉ ህይወት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል። በተቃዉሞዉም ከፓርላማ ዉጪ ያሉ ብቻ ሳይ

https://p.dw.com/p/E0jL

�ኑ በመንግስት አስተዳደር ድርሻ ያላቸዉ የፓርላማ ወገኖችም ሁሉ ይገኙበታል።

ላልተማሩት ኬንያዉያን ግንዛቤ ሲባል አዲሱን ህገመንግስት በሙዝ ነባሩን በብርቱካን መስለዉታል ኬንያዉያን።
ቅዳሜ ዕለትም አዲሱን ህገመንግስት የሚደግፉ ወገኖች ስሜታቸዉን ናይሮቢ በሚገኘዉ ዑሁሩ ወይም ነፃነት ፓርክ በመዉጣት ገልፀዋል።
ሙዝን መለያ ምልክታቸዉ አድርገዉ የወሰዱት ደጋፊዎች መድረኩን በፍሬዉ ያሸበረቁት ሲሆን በለበሱት ቲሸርት ላይም YES የሚለዉን አዎንታዊ የድጋፍ ማረጋገጫ ቃል አስፍረዉ ታይተዋል።
በሌላ ወገን ናያዮ ብሄራዊ ስታዲየም የተበሰቡት በሺዎች የሚቆጠሩት ተቃዋሚዎች ብርቱካናማ ሪቫን፤ ኮፍያ፤ ክራቫት፤ የአንገት ልብስ እንዲሁም የብርቱካን ፍሬ በእጃቸዉ ይዘዉ ወጥተዋል።
ምንም እንኳን ባለፈዉ የታየዉ ዓይነት ረብሻና ግጭት ይኖራል የሚል የደህንነት ስጋት ቢኖርም አንጻራዊ ሰላም የሰፈነበት ሰልፍ ነበር በሁለቱም ወገን የተካሄደዉ።
ባለፈዉ ወር ኪሱሙ በተባለችዉ ግዛት ምዕራባዊ ክፍል በተቃዋሚዎችና በፖሊስ መካከል በተከሰተዉ ግጭት ህፃናት ተማሪዎችን ጨምሮ አራት ሰዎች ህይወታቸዉን አጥተዋል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይም በኬንያ የወደብ ከተማ በሞምባሳ በተመሳሳይ ሁኔታ ረቂቁን ህገ መንግስት ለመቃወም የወጡ ወገኖችና ፖሊሶች ተጋጭተዉ ተጨማሪ አራት ሰዎች አልፈዋል።
አዲሱን የኬንያ ህገ መንግስት የሚቃወሙት ወገኖች የተቃዉሟቸዉ መነሻ ህገመንግስቱ ለአገሪቱ ፕሬዝደንት ከመጠን ያለፈ ስልጣን ይሰጣል የሚል ነዉ።
ደጋፊዎቹ ወገኖችም በበኩላቸዉ አዲሱ ህገ መንግስት የጠቅላይ ሚኒስትር ቦታ ለመፍጠር አመቺ አንቀፅ እንዳለዉ ይናገራሉ።
ታዛቢዎችና ተቺዎች እንደሚሉት ምንም እንኳን የጠቅላይ ሚኒስቴር ቦታ ቢኖረዉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያን ያህል ስልጣን የሚኖራቸዉ እንዳልሆነ ነዉ የሚያስረዱት።
በተቃዋሚዎቹ ወገን በድጋሚ የተነሳዉ ጥያቄም አዲሱ ህገ መንግስት በተረቀቀ ማግስት ቦማስ በተሰኘዉ የኬንያ ባህል አዳራሽ ለዉይይት ቀርቦ የተደረገለት ማሻሻያ ይካተት ነዉ።
በወቅቱ ከመንግስትና ከሲቪሉ ህብረተሰብ የተዉጣጣ ብሄራዊ ህገመንግሳዊ ሸንጎ ሲካሄድ የፕሬዝደንቱን መጠን የለሽ ስልጣን አዲስ ወደሚፈጠረዉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቦታ አካፍሎ ነበር።
ይህ ማሻሻያ ሃሳብም ኬንያዉያን በህገመንግሳቸዉ ምን ማየት እንደሚፈልጉ እንዲያጠና የዛሬ አምስት ዓመት ወደተቋቋመዉ አጣሪ ኮሚሽን ቀርቧል።
አጣሪ ኮሚሽኑም በቀድሞዎቹ የኬንያ መሪዎች በዳንኤል አራፕ ሞይና በጆሞ ኬንያታ ዘመን የታየዉ ዓይነት ከመጠን ያለፈ ስልጣን አጠቃቀም እንዳይደገም የፕሬዝደንቱ ስልጣን ይገደብ የሚል መሆኑን ደርሶበታል።
ፕሬዝደንቱ ሟይ ኪባኪና በእንግሊዝኛ ምህፃሩ NAK በመባል የሚታወቀዉ ብሄራዊ የጥምር ፓርቲያቸዉ የኬንያ ህዝብ አዲሱን ህገ መንግስት እንዲቀበል ቅስቀሳ ሲያካሂዱ ሰንብተዋል።
NAK እና የመንገዶች ሚኒስትር በሆኑት ራይላ ዖዲንጋ የሚመራዉ ነፃ ዲሞክራቲክ ፓርቲ በምህፃሩ LDP በስልጣን ላይ ያለዉ የኬንያ የቅንጅት መንግስት አካል ሲሆኑ LDP እና ዖዲንጋ አዲሱን ህገ መንግስት አጥብቀዉ ይቃወማሉ።
እነዚህ ሁለት ሰዎች ኪባኪ የኬንያ ፕሬዝደንት ሆነዉ ስልጣን ላይ ከመዉጣታቸዉ በፊት ጀምሮ የተግባቡበት ነጥብ ነበር ኪባኪ ፕሬዝደንት ሲሆኑ ዖዲንጋ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆኑ።
በፈረንጆቹ 2002ዓ.ም. በነበረዉ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅትም ዖዲንጋ የኪባኪን ብሄራዊ ቀስተደመና ቅንጅት ፓርቲን በመደገፍና በመተባበር በምርጫዉ ለማሸነፍ ከፍተኛ አስተውዖ አደረጉ።
ቅዳሜ ዕለት በነበረዉ የድጋፍ ተቃዉሞ ትዕይንት ወቅት ግን እነዚህ ሁሉ መግባባትና መተባበሮች አልታዩም ዖዲንጋ በተደጋጋሚ ፕሬዝደንቱ የድጋፍ ድምፅ ለመግዛት የፖለቲካ ስራ እየሰሩ መሆናቸዉን ሲከሱ ተሰምተዋል።
ስቴድ ማን በተባለ ቡድን ባለፈዉ ወር የተካሄደ ጥናት እንደጠቆመዉ አዲሱን ህገመንግስት የሚደግፈዉ 32በመቶ ሲሆን የማይደግፈዉ 42በመቶ ህዝብ ነዉ።
ቢቢሲ በበኩሉ ባካሄደዉ ተመሳሳይ የህዝብ ሃሳብ ማሳያ ጥናቱ 18 በመቶ የሚሆነዉ የኬንያ ህዝብ አዎንታ ድምፁን ሲሰጥ 81.5በመቶዉ ጭራሽ ተቃዋሚ ሆኖ ነዉ የተገኘዉ ለአዲሱ ህገመንግስት።
አስመራጩ አካል የይለፍ አረንጓዴ መብራት ከሰጠዉ ይህን አይነት የድምፅ ልዩነት የተመዘገበበት አዲሱ ህገ መንግስት በፕሬዝደንቱ ፊርማ ስራ ላይ የሚዉለዉ ከመጪዉ ታህሳስ 3ቀን ጀምሮ ይሆናል።
ተቃዋሚዉ ወገን ከተሳካለት ደግሞ ረቂቁን በህዝቡ ጥያቄ መሰረት የማረም ተግባር እስኪጀመር ድረስ ባለዉ ህገ መንግስት ይሰራል።
ኬንያ ከታላቋ ብሪታንያ ቅኝ ግዛትነት ነፃ ከወጣችበት የፈረንጆቹ 1963ዓ.ም. አንስቶ እስከ ዛሬ የምትመራዉ አሁን በስራ ላይ በሚገኘዉ ህገ መንግስት ነበር።