1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቦኮሐራም የካሜሩን ከፍተኛ ባለሥልጣን ባለቤትን አገተ

እሑድ፣ ሐምሌ 20 2006

ቦኮሐራም የተሰኘው የናይጀሪያ እስልምና አክራሪ ታጣቂ ቡድን ካሜሩን ውስጥ ሰርጎ በመግባት የካሜሩን ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ባለቤትን አግቶ መሰወሩን የካሜሩን መንግስት አስታወቀ።

https://p.dw.com/p/1Cjd3
Nigeria Polizist Demonstration vermisste Mädchen
ምስል picture-alliance/AP Photo

ቦኮሐራም የሚንሥትሩን ባለቤት ጨምሮ ሌሎች ሰዎችን ባገተበት ድርጊቱ በርካታ ሰዎች መገደላቸውም ተነገሯል። ቦኮሐራም የሰነዘረው ጥቃት ዛሬ ማለዳ ላይ የተፈጸመው የካሜሩን ሰሜናዊ ግዛት፣ ኮሎፋታ ከተማ ውስጥ እንደሆነ የካሜሩን የኮሙኒኬሽን ሚንስትር ኢሣ ትቺሮማ ባካሪ ገልፀዋል። የቦኮሐራም ታጣቂዎች የጥቃታቸው ዒላማ አድርገው የተንቀሳቀሱት የምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ አማዱ ዓሊ እና የአካባቢው የጎሳ አለቃ ቤቶች ላይ እንደነበረም ተጠቅሷል። የሟቾቹ እና የታጋቾቹ ሁነኛ ቁጥርን ለማወቅ ጥረት እየተደረገ በመሆኑ ምን ያህል እንደሆነ ማወቅ አይቻልም ሲሉ የመንግሥት ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

Abuja Anschlag 14.04.2014
የቦኮሐራም ቡድን በተደጋጋሚ በናይጄሪያ የቦንብ ጥቃት ያደርሳል።ምስል picture alliance/AP Photo

ምንም እንኳን ቦኮሐራም ከናይጀሪያ መንግስት ጋር በሚያደርገው ፍልሚያ ማንም ጣልቃ እንዳይገባበት ቢያስጠነቅቅም፤ የአካባቢው ሃገራት ቦኮሐራምን ለመዋጋት በሚያደርጉት የጋራ ጥረት የካሜሩን መንግስት ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱ ይታወቃል። በተያያዘ ዜና ከናይጄሪያ ሰሜናዊ ከተሞች ግዙፍ በሆነችው የካኖ ከተማ አንድ የካቶሊክ ቤተክርስትያን ውስጥ ዛሬ በደረሰ የቦንብ ጥቃት ቢያንስ አምስት ሰዎች መገደላቸውን ፖሊስ አስታወቀ። ጥቃት አድራሹ የናይጀሪያው አሸባሪ ቡድን ቦኮሐራም ስለመሆኑ ግን እስካሁን አልታወቀም። ሆኖም ከአራት ወራት በፊት ማሮው ውስጥ የተያዙ 22 የቦኮሐራም ተጠርጣሪዎች ከትናንት በስትያ ከ10 እስከ 20 ዓመታት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ ተበይኖባቸው እንደነበር መጠቀሱ ይታወቃል።

ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ