1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቦኮ ሀራም ያስፋፋው ጥቃት

ቅዳሜ፣ ኅዳር 11 2008

በሰሜናዊ ናይጀሪያ የሚንቀሳቀሰው እስላማዊ ፅንፈኛ ቡድን ቦኮ ሀራም ከዓለም የከፋዉ አደገኛ ቡድን መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ። ዓለም አቀፍ የሽብር ጥናት መዘርዝር እንዳመለከተዉ ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ 2014 በሽብር ጥቃት ቦኮሃራም የገደላቸው ሕይወት በ317 ከመቶ ይበልጣል። በ2014ዓም ብቻ ቦኮሃራም የ6,644 ሰዎችን ሕይወት አጥፍቶዋል።

https://p.dw.com/p/1H9m5
Anschlag von Boko Haram in Yola, Nigeria
ምስል Reuters/Stringer

ቦኮ ሀራም ያስፋፋው ጥቃት

በአዳማዋ እና በካኖ ፌዴራዊ ግዛቶች ዋና ከተሞች ዮላ እና ካኖ ከተሞች አጥፍቶ ጠፊዎች ባለፈው ረቡዕ በጣሉት ጥቃት ከ50 የሚበልጡ ናይጀሪያውያን ሕይወታቸውን አጥተዋል። ብዙዎችም ቆስለዋል። ይህንኑ ጥቃት እስላማዊ ፅንፈኛ ቡድን ቦኮ ሀራም ሳይጥለው እንዳልቀረ ተገምቶዋል።

ቦኮ ሀራም ባካባቢው ባስፋፋው የሽብር ተግባር ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ብዙዎች በሚገኙባት የአዳማዎ ግዛት ዋና ከተማ ዮላ አጥፍቶ ጠፊዎች ከአራት ቀናት በፊት በጣሉት ጥቃት ቢያንስ 34 ሰዎች ሲገደሉ፣ 80 የሚሆኑ መቁሰላቸውን የከተማይቱ ፖሊስ አስታውቋል። አሸባሪዎቹ ቦምቦቹን ያፈነዱት የደራ ንግድ ይካሄድባቸው በነበሩ የገበያ ቦታዎች ነበር። ከዮላው ጥቃት ቀጥሎም በሌላዋ የሰሜን ናይጀሪያ ከተማ ካኖ በአንድ የእጅ ስልክ መሸጫ የገበያ ቦታ በተጣለ ጥቃት ቢያንስ 15 ሰዎችመሞታቸውን እና ፖሊስ ጉዳዩን በማጣራት ላይ መሆኑን የካኖ ፌዴራዊ ግዛት ፖሊስ ኮሚሽነር ሙሀማድ ሙሳ ካትሲና ገልጸዋል።

« ምርመራው አሁንም እንደቀጠለ ነው። በመሆኑም ዝርዝር መግለጫ ለመስጠት አልችልም። ከዓይን ምስክሮች መረዳት እንደቻልነው፣ ስድስት ሂጃብ የለበሱ ሴቶችን ያሳፈረ አንድ ሻሮን ፎልክስቫገን ተሽከርካሪ ወዳካባቢው መጣ። ሁለቱን እዚህ አወረደ። ሌሎቹ አራት ጉዟቸውን ቀጠሉ ። የመጀመሪያዋ ሴት ቦምቡን በቦታው ስታደምጥ ሌላኛዋ ቆማ ትጠብቅ ነበር። አጥፍቶ ጠፊዎቹ ባጠመዱት ፈንጂ ከሌሎቹ ጋር ተገድለዋል። »

ይህንኑ ጥቃት የጣሉት ሁለቱ ሴቶች የ11 እና የ18 ዓመት ሳይሆኑ እንደልቀሩ ነው የተገለጸው። ቦኮ ሀራም በሰሜን ምሥራቅ ናይጀሪያ በቀጠለው የሽብር ተግባር ላይ በወጣት ሴት አሸባሪዎች መጠቀምን እንደ አዲስ ስልት ይዞዋል።

Boko Haram Gouverneur Jibrilla in Yola Afrika Nigeria
ምስል DW/A.Kriesch

በዮላ እና ካኖ ከተሞች ጥቃቶቹ የተጣሉት የናይጀሪያ ፕሬዝደንት መሀማዱ ቡሀሪ ዮላን ከጎበኙ እና የሃገራቸው ጦር ቦኮ ሀራምን ከሞላ ጎደል ድል እንዳደረገ በዚያ ካረጋገጡ ከሶስት እና አራት ቀናት በኋላ መሆኑ፣ ያካባቢው ሕዝብ የፕሬዚደንት ቡሀሪ አባባልን እንዲያጠያይቅ አድርጎታል። ይሁንና፣ የአዳማዋ ፌዴራዊ ግዛት ዋና አስተዳዳሪ መሀመድ ኡማር ጂብሪላ ቦኮ ሀራም በርግጥ እየተሸነፈ መሆኑ እንደማያጠራጥር ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል።

«ትክክል ነው፣ ቦኮ ሀራም ድል እየተመታ ነው። የሚጥላቸው ጥቃቶችም ግራ የመጋባቱ ምልክት ነው። የጥቃቱ ጠንሳሾች ብዙ ሰው ለመግደል ሲሉ ለሕፃናት ገንዘብ አከፋፍለዋል። ፕሬዚደንቱ ትክክል ናቸው። ቦኮ ሀራም በቅርቡ ያለፈ ታሪክ ይሆናል። ናይጀሪያም ሰላም ትሆናለች። ፕሬዚደንታችን እና አዲሱ የፀጥታ ኃላፊዎች ግሩም ስራ በመስራት ቦኮ ሀራምን እንዲያፈገፍግ ማድረጉ ችለዋል። መንግሥትም ህብረተሰቡን የማንቃት ሰፊ ስራ ሰርቷል። ምክንያቱም ይህ የሃገሪቱ ጦር ብቻውን የሚያካሂደው ውጊያ አይደለም። ህብረተሰቡም በዚሁ ትግል ላይ መሳተፍ አለበት። ሁላችንም ነቅተን መጠበቅ አለብን። »

Von Boko Haram zurückgelassener Panzer in Yola, Adamawa, Nigeria
ምስል picture alliance/AA/M. Elshamy

የሽብር ጥቃት ሁሉንም የሚነካ መሆኑ ካለፈው ሳምንት የፓሪስ ጥቃት በኋላ እየጎላ መምጣቱን ያመለከቱት የአዳማዎ ግዛት ዋና አስተዳዳሪ ጂብሪላ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአሸባሪዎችን ጥቃት ለማብቃት ተባብረው መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል።

ቦኮ ሀራም ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ ባስፋፋው ጥቃት ቢያንስ 17,000 ሰው ሕይወት ሲጠፋ ከ2,6 ሚልዮን በላይ ደግሞ ከቤት ንብረት አፈናቅሎዋል።

አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ