1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቬርነር ፎን ብራውን፣

ረቡዕ፣ መጋቢት 19 2004

ህልማቸው ፤ ራእያቸው ወደ ኅዋ፣ በተለይም ወደ ጨረቃ መጓዝ ፤ የሚቻልበትን መላ መሻት ነበር። ይሁንና ፣ የታሪክ ሰዎች እንደሚሉት፤ ከዲያብሎስ ጋር አንድ ውል ተዋዋሉ፤ ማለት፤ በናዚዎች ትብብር ፣ በቅድሚያ ፤ የሂትለርን አስደናቂ የተሰኘ

https://p.dw.com/p/14Tww
ምስል AP

ህልማቸው ፤ ራእያቸው ወደ ኅዋ፣ በተለይም ወደ ጨረቃ መጓዝ ፤ የሚቻልበትን መላ መሻት ነበር። ይሁንና ፣ የታሪክ ሰዎች እንደሚሉት፤ ከዲያብሎስ ጋር አንድ ውል ተዋዋሉ፤ ማለት፤ በናዚዎች ትብብር ፣ በቅድሚያ ፤ የሂትለርን አስደናቂ የተሰኘ ሮኬት ሠሩ፤ «V-2» የተሰኘውን! በአህጽሮት V-2 እየተባለ የሚጠቀሰው የጦር መሣሪያ ወይም ሮኬት፣ በጀርመንኛው Vergeltungswaffe የሚሰኘው ነው። በጀርመንኛ ፣ የመበቀያ ጦር መሣሪያ ማለት ነው ትርጉሙ! እናም የመጀመሪያው V-1 ከዚያ ቀጥሎ V-2 በመጨረሻም A-4፣ እነዚህ ሁሉ ሮኬቶች ሲሠሩ ፣ ቬርነር ፎን ብራውን በዋናነት መሣተፋቸው አልቀረም። የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲያከትም ፣ በዕውቀታቸው እጅግ ይፈለጉ የነበሩት ፎን ብራውን፤ ወደ ዩናይትድ በመሻገር፣ እስከ ኅልፈተ-ኅይወታቸው የኖሩት በዚያ ነው። በእጅጉ፣ የዕድሜ ጸጋ የታደሉ ቢሆኑ ኖሮ ፣ ባለፈው ዓርብ እ ጎ አ መጋቢት 23 ቀን ፣ መቶኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ለማክበር በበቁ ነበር።
ጤናይስጥልኝ እንደምን ሰነበታችሁ? በዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ ፣ የቬርነር ፎን ብራውንን የሥራ ክንውኔ መለስ ብለን እንቃኛለን።

USA Deutschland Wernher von Braun mit Walt Disney in Redstone Arsenal
ምስል picture-alliance


የሮኬቱ ሊቅ ቬርነር ፎን ብራውን፣ የምርምርና የሮኬት ሥራን በዩናይትድ እስቴትስ በመቀጠል፤ በመጨረሻ፤ ወደ ጨረቃ ለመጓዝ አቅድ በተያዘለት የ»አፖሎ» መርኀ ግብር
መሪ ድርሻ ያበረከቱ ኢንጅኔር ናቸው።
በትውልድ ጀርመናዊ የሆኑት ቬርነር ፎን ብራውን፣ እ ጎ አ መጋቢት 23 ቀን 1912 ዓ ም፤ አሁን በፖላንድ ሥር በምትገኘው Wirsitz ብሮምበርግ(ፖዘን) ከተማ አቅራቢያ፣ የጀርመን ንጉሳዊ መንግሥት የ ፎን ፓፐን ካቢኔ ፤የምግብ ጉዳይ ሚንስትር ከነበሩት አባታቸው፣Freiherr Magnus von Braun ተወለዱ። ገና ለጋ ወጣት እያሉ የሮኬት ሥራ ጀማሪ በነበሩት Oberth የርችት ሮኬት አዘጋጁ።
ፎን ብራውን ፤ በርሊን በሚገኘው የፈረንሳይ የሁለተኛ ደረጃ የቀለም ትምህርት ቤት በኋላም ፣ በ እሽፒከሩግ፤ በ Hermann -Lietz-Schule ተምረዋል። ከዚያም በበርሊን Borsigwerken የቴክኒክ ትምህርት ከመቅሰማቸውም፤ በበርሊን የሥነ -ቴክኒክ ከፍተኛ ተቋም ፊዚክስና የተፈጥሮ ሳይንስ ተምረዋል። እንግዲህ ገና ተማሪ ሳሉ ጀምሮ የሮኬት ቅርጽ ማውጣትና መሥራት ጀምረው ነበር። ይህን የሚያደርጉትም የሮኬት መፈተሻ በሆነው ራይኒከንዶርፍ፣ በታዋቂው የሮኬት ሥራ ጀማሪ ሩዶልፍ ኔበል ተቆጣጣሪነት ነበረ። ቬርነር ፎን ብራውን፣ ፍቅራቸው ከሮኬት ጋር ብቻ አልነበረም። ኅዋ፤ ሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ይመስጣቸው ነበር። በሥነ-ፈለክ ፍቅር የተለከፉት ገና በልጅነት ዕድሜያቸው ነው። ወላጆቻቸውም፣ ዝንባሌአቸውን ተገንዘበውላቸው ያበረታቱአቸው ነበር። ራሳቸው ቬርነር ፎን ብራውን ለጋ ወጣት ሳሉ ወላጆቻቸው ያደረጉላቸውን እንዲህ ያስታውሳሉ።----

Bildergalerie Wernher von Braun
ምስል picture-alliance / dpa


1,«በ 1925 ዓ ም፤ ያኔ የ 13 ዓመት ልጅ ነበርሁ፤ ወላጆቼ፤ አንዲት ትንሽ የሰማይ አካላትን መመልከቻ መሣሪያ (ቴሌስኮፕ) ሰጡኝ። በዚያ ቴሌስኮፕ፣ ማታ- ማታ፤ ረዘም ላለ ጊዜ፣ ጨረቃንና ከዋክብትን እመለከት ነበር።»
ቬርነር ፎን ብራውን ትኩረታቸው ሩቅ ለሚመጥቁ ሮኬቶች ሥራ ነበረ። በመጸው 1937 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት፤ጀርመን ለመጀመሪያ ጊዜ ሮኬት ሞከረች። የሮኬት ጦር መሣሪያ ለማምረት ፣ በተለይ (A4 ወይም V-2 )የተሰኘውን ሮኬት ለማምረት፤ 15,000 ሠራተኞች በተሠማሩበት ፋብሪካ፣ Dornberger አዛዥ፣ von Braun ደግሞ፣ የቴክኒክ ሥራ አስኪያጅ ሆኑ። እ ጎ አ ጥቅምት 3 ቀን 1942 ዓ ም፤ የመጀመሪያው A4 (Aggregat 4(የማሺኖች ጥምረታዊ ተግባር 4)ወደ ሰማይ ነጎደ ።
በመጀመሪያ ይህን ፕሮጀክት ፣ ለናዚዎቹ ሥርዓት ፍጹም ታማኞች የነበሩት፣ እና Fritz Todt Albert Speer አልፈቀዱትም ነበር ። ሂትለርም ቢሆን፤ ሮኬት ዋጋ ያለው መሣሪያ ነው ብሎ አያስብም ነበር። ይሁን እንጂ፤ በሰሜናዊው ምሥራቅ ጀርመን ፤ በሜከልንቡርግ ፎርፖመርን ፌደራል ክፍለ ሀገር፤ በምሥራቅ ባህር Usedom ደሴት ላይ የምትገኘው የባህር ኃይልና የሮኬት መፈተሻ ጣቢያ ፣ Peenemünde እ ጎ አ ነሐሴ 17 እና 18, 1943 ዓ ም፣ 560 የብሪታንያ (ሮያል ኤር ፎርስ)አየር ኃይል ጦር አኤሮፕላኖች፤ 1,800 ቶን በሚመዝኑ ቦንቦች የሮኬት መሥሪያውን ፋብሪካ ካወደሙና የ 170 ሰዎችን ህይወት ከቀጠፉ፤ በተጨማሪም፣ ተገደው በሥራ ላይ የነበሩ 500 የጦር ምርኮኞችን በስህተት በተደረገ ድብደባ ከገደሉ በኋላ፤ ናዚ ጀርመን፣ ዘግየት ብላ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ፣ በወሰደችው እርምጃ

Wernher von Braun mit Ehefrau Maria
ምስል picture-alliance / Sven Simon

፣እ ጎ አ ሰኔ 13 ቀን 1944 ዓ ም፤ የመጀመሪያው V-1 ሮኬት፣ ኢንግላንድን መታ። በዚያው ዓመት መስከረም 8 ፣ V-2 ሮኬት በኢንግላንድ ላይ ተመሳሳይ አደጋ አደረሰ። ሂትለር ከዚያ ቀደም ሲል በ 1942 ዓ ም፤ 5,000 ፣ V-2 ሮኬቶች እንዲመረቱ አዞ ነበር። በአይግላንድ ላይ ከ 2,500 በላይ V-2 ሮኬቶች ቢጣሉም፤ የእንግሊዝን ደንዳናነትንም ሆነ ቁርጠኛ የመዋጋት ሞራል ሊሰብር አልቻለም። በያኔዋ ጀርመን አባባል እነዚያ የመበቀያ ጦር መሣሪያዎች የተባሉት ሮኬቶች የተሠሩት በ ቬርነር ፎን ብራውን አስተባሪነት እንደነበረ የታወቀ ነው። ጦርነቱ በማክተም ላይ እንዳለ ፎን ብራውን አብዛኛውን የቤተ -ሙከራ መሣሪያወቻቸውን በተለይም ለኅዋ ምርምር የሚበጁትን ከውድመት ለማትረፍ ወደ ቱዑሪንገን አዛወሯቸው። በኋላም ወደ ደቡብ ጀርመን ባየርን (ባቬሪያ) አቀኑ። በዚያም ከሌሎች 130 ያህል ባልደረቦቻቸው ጋር እ ጎ አ በ 1945 ዓ ም፤ ወደ ዩናይትድ እስቴትስ ተጓዙ። የስይንስና ሥነ ቴክኒክ ጠበብቱ ወደ ፎርት ብሊስ ፤ቴክሳስ ከተወሰዱ በኋላ፣ የሮኬት ሞተር መሥራትና የኅዋ ጉዞን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ማትኮራቸውን ቀጠሉ። በ 1955 ዓ ም ሁሉም በኅብረት የዩናይትድ እስቴትስ ዜጎች ሆኑ።
ለናዚዎች መንግሥት ያበረከቱት ድርሻ ተረሳ፤ ልዩ ክብካቤም ነው የተደረገላቸው። ስለዚህ ም ጉዳይ ራሳቸው ፎን ብራውን እንዲህ ብለው ነበር።

Wernher von Braun im Disney-Film "Morgen zum Mond"
ምስል picture-alliance / akg-images


3,«በቴክሳስ የተደረገልን አቀባበል ፣ በሚያስደንቅ ሁኔታ በወዳጅነት መነፈስ የተመላ ነበር።»
ሶቭየት ኅብረት፤ እ ጎ አ፣ በጥቅምት ወር 1957 ዓ ም፤ «እስፑትኒክ» የተባለችውን ሳቴላይት ካመጠቀች በኋላ ፤ ዩናይትድ እስቴትስ የተለያዩ ሙከራዎችን ካደረገች በኋላ፤ እ ጎ አ በየካቲት 1958 በጁፒተር ሲ ሮኬት እርዳታ፣ «ኤክስፕሎረር 1 » የተባለችውን መንኮራኩር ለማምጠቅ በቃች። ለዩናይትድ እስቴትስ የኅዋ ጉዞ መርኀ- ግብር ፣ ዐቢይ ድርሻ ያበረከቱት፣ ቬርነር ፎን ብራውን፤በሐምሌ ወር 1969 ዓ ም፤ 2 አሜሪካውያን ጨረቃን ለመርገጥ የበቁበትን 41 ቶን የሚመዝነው ፤ የአፖሎ 11 መንኮራኩር ተልእኮ እጅግ ኃይለኛ በነበረው «ሳተርን 5 » በተሰኘው ማስፈንጠሪያም ሆነ ተኳሽ ሮኬት በኩል ፤ የእርሳቸው ህልም ጭምር እውን እንዲሆን አብቅተዋል።
2,«የኅዋ ጎዞን የተሳካ ለማድረግ፤ የጨረቃን የግፊት ኃይልም ለመቋቋም ፣ በዚያው በጨረቃ ማረፊያ ቤት መሥራት ይኖርብናል። ላልተለመደው የአየር ጠባይ የሚስማሙ ጨረቃ ላይ የሚጓዙ ልዩ ተሽከርካሪዎች ያስፈልጉናል። ጠፈርተኞች ወጣ ብለው ፤ በዚያ የጨረቃ ምድር የሚፈልጓቸውን አንዳንድ ቦታዎች ለመጎብኘት ይቻላቸው ዘንድ ማመቻቸት ያሻል።»
ዩናይትድ እስቴትስ ውስጥ፤ ከ ቨርነር ፎን ብራውን ጋር አብረው ከሠሩት አሜሪካውያን የኅዋ ምርምር ኢንጂኔሮች መካከል፤ ዴቪድ ክሪስተንሰን የተባሉት፤

Wernher von Braun
ምስል AP


«ያኔም ሆነ አሁን የእውነቱን ለመናገር የእርሳቸውን ያክል ችሎታ ኖሮት እርሳቸው የሠሩትን ያክል የሠራ ከቶ ማንንም አላውቅም።» ሲሉ መሥክረውላቸዋል።
መጋቢት 29 ቀን 2004 ዓ ም፤ 80 ኛ ዓመታቸውን የሚያከብሩት ክሪስተንሰን፣ ከሌሎች ቬርነር ፎን ብራውንን ከሚያውቋቸው ሰዎች ጋር ሆነው፣ የፊታችን ዓርብ ፣ በ Huntsville ከተማ በሚገኘው የ አላባማ ዩኒቨርስቲ ፤ የዝካሬ ዲስኩር ያሰማሉ።

ቨርነር ፎን ብራውን፤ ለሮኬት ሳይንስ ባበረከቱት ድርሻ ሳቢያ በተወለዱባት ሀገር በጀርመንና ሁለተኛ ዜግነት ባገኙባት ሀገር ፣ ከዚያም አልፎ በዓለም ዙሪያ ገናና ስም ነው ያላቸው። በሃንትስቪል የተለያዩ ህንጻዎችና ተቋማት፤ የእርሳቸውን ስም የሚያስታውሱ ሲሆን፤ በጀርመን አያሌ ጎዳናዎች በእነህ ታዋቂ ሮኬት ሠሪ ስም ይጠራሉ። በጨረቃም ፤ አንድ የተሰረጎደ የተራራ ጫፍ፣ ፎን ብራውን የሚል ስያሜ ነው የተሰጠው። ቬርነር ፎን ብራውን፣ እ ጎ አ በ 1970ኛዎቹ ዓመታት መግቢያ ገደማ ፣ አለመግባባት በመፈጠሩ፣ የአሜሪካውን ብሔራዊ የበረራና የኅዋ ምርምር መ/ቤት መልቀቅ ግድ ሆኖባቸው ነበር። በኩላሊት ካንሰር ሳቢያ፤ በ 65 ዓመታቸው፤ ዩናይትድ እስቴትስ ፤ አሌክሳንድሪያ ፤ ቨርጂኒያ ውስጥ፤ ያረፉት ፤ እ ጎ አ ሰኔ 16 ቀን 1977 ዓ ም ነው።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ