1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተመራጩ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 30 2004

የፈረንሳይ ህዝብ ባለፈው እሁድ አዲስ ሶሻሊስት ፕሬዝዳንት መርጧል ። ተመራጩ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ ተሰናባቹ ኒኮላ ሳርኮዚ በተስማሙባቸው የአውሮፓ ህብረት የቁጠባ እቅዶች ላይ እንደገና እደራደራለሁ በማለታቸው ሁሉም ዓይኑን ጥሎባቸዋል ።

https://p.dw.com/p/14rvT
ምስል picture-alliance/dpa

የፈረንሳይ ህዝብ ባለፈው እሁድ አዲስ ሶሻሊስት ፕሬዝዳንት መርጧል ። ተመራጩ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ ተሰናባቹ ኒኮላ ሳርኮዚ በተስማሙባቸው የአውሮፓ ህብረት የቁጠባ እቅዶች ላይ እንደገና እደራደራለሁ በማለታቸው ሁሉም ዓይኑን ጥሎባቸዋል ። የኦልንድ ማንነትና የፖለቲካ መርሃቸው የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው ።

« ሃገሪቱን እንደገና ተስፋ ለማስጨበጥ በመቻሌ ኩራት ይሰማኛል »

እሁድ ሚያዚያ 28 ፣ 2004 ዓ.ም በተካሄደው 2 ተኛ ዙር የፈረንሳይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ድል የተቀዳጁት ሶሻሊስቱ ፍራንሷ ኦልንድ በማሸነፋቸው የተሰማቸውን ደስታ ለደጋፊዎቻቸው ቱል በተባለው ከተማ እንደገለጹት ።

Frankreich Wahlen 2012 Francois Hollande Wahlsieg
ምስል Reuters

የ 57 ዓመቱ ኦሎንድ ፣ ከ 1ዓመት በፊት ፣ ከዓለም በኢኮኖሚ እድገት 5 ተኛ ከአውሮፓ ደግሞ 2 ተኛ ደረጃ ላይ ለምትገኘዋ ለባለፀጋዋ ሃገር ፈረንሳይ ትልቅ የፖለቲካ ሥልጣን ይበቃሉ ብሎ የገመተም አልነበር ። እኝህ ከዓመት በፊት እዚህ ይደርሳሉ ተበለው ያልተጠበቁት በአንዳንዶች አገላለጥ እንደ ፕሬዝዳንት ኒኮላ ሳርኮዚ ልታይ ልታይ የማይሉት ሶሻሊስት ፖለቲከኛ ፣ ተጨማሪ 5 ዓመታት በሥልጣን ለመቆየት አልመው ከተነሱት ሳርኮዚ ጋር ለመወዳደር ያበቃቸው ባለፈው ዓመት በፓርቲያቸው ውስጥ የተከሰቱ አዳዲስ ሁኔታዎች ናቸው ። የፈረንሳይ ሶሻሊስት ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ እጩ ሆነው የመቅረብ እቅድ የነበራቸው የቀድሞው የዓለም የገንዘብ ድርጅት በእንግሊዘኛው ምህፃር IMF ሃላፊ ዶሚኒክ ስትራውስ ካን ኒውዮርክ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በወሲብ ቅሌት ተከሰው ለምርመራ ከተያዙ በኋላ ከIMF ሃላፊነት እንደወረዱ እጩ ሆኖ የመቅረብ እቅዳቸውንም ፉክክሩ ከመጀመሩ በፊት መሰረዛቸው ኦሎንድ የርሳቸውን ቦታ እንዲይዙ ምክንያት ሆነ ። ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ በእጅጉ በዓለም የኢኮኖሚ ዝግመት በተለይም ደግሞ በአንዳንድ የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ባጋጠመው የኤኮኖሚ ቀውስ ና መፍትሄው ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ይንቀሳቀሱ የነበሩት ኒኮላ ሳርኮዚ ሥልጣን ሲይዙ ለህዝቡ የተሻለ ህይወት ለማምጣት የገቡትን ቃል ተግባራዊ ማደረግ አለመቻላቸው አንዱ የውድቀታቸው መንስኤ ተደርጎ ተወስዷል ።

Francois Hollande
ምስል dapd

ፈረንሳይን በአሰከፊው የኢኮኖሚ ቀውስ ወቅት የመሩት ሳርኮዚ በግራዎቹ ከባህሉ አፈንገጥው የባለፀጎች ወዳጅ በመሆን ሲተቹ ፣ በቀኝ ፅንፈኞች ደግሞ ቃላቸውን ያጠፉ ተደርገው ነወ የሚወቀሱት ፣ለዘብተኛዎቹ በበኩላቸው የጀመሩትን የተሃድሶ እርምጃዎች በማቆም ነው ሲያብጠለጥሉዋቸው የከረሙት ። ይህ ሁሉ ተደማምሮ እምብዛም የፖለቲካ ልምድ የሌላቸውን ፣ ዝምተኛና ያን ያህልም ትኩረት የሚስቡ እንዳልሆኑ የሚነገርላቸውን የኦልንድን የፕሬዝዳንትነት እድል በር አስፋ ። በአውሮፓ ህብረት እቅዶችና ውሳኔዎች ላይ ተመሳሳይ አቋም በመያዝ እጅና ጓንት ሆነው በመሥራታቸው ሜርኮዚ የተሰኘ የጋራ ስም የወጣላቸው የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኒኮላ ሳርኮዚና የጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የጋራውን ሸርፍ ዩሮን ከውድቀት ለማዳን ላደረጉት ጥረት የዓለም አድናቆት እየቀዘቀዘ ሲሄድ ሳርኮዚና መሰሎቻቸው የሚደጋግሙትን ቁጠባ ና የበጀት ቁጥጥር የሚሉትን ቃላት ኦሎንድ በምርጫ ዘመቻቸው እድገት በሚለው መቀየራቸው የድላቸውን በር ከፋች ሆኗል ። ኦሎንድ በዘመቻው ወቅት ደጋግመው ያነሱት የእደገት መርሃ ግብር የእሁድን የመለያ ምርጫ ለማሸነፍ እንዳበቃቸው ነው የሚነገረው ። ከድሉ በኋላ ለደጋፊዎቻቸው ባሰሙት ንግግር ይህኑኑ እቅዳቸውን በምን ዓይነት ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ እንዳሰቡ ተናግረዋል።

Francois Hollande Nicolas Sarkozy besuchen ein Sägewerk
ምስል Reuters

« የፕሬዝዳንቱ የመጀመሪያ ግዴታ አሁን በሃገሪቱን የተደቀነውን ተግዳሮት ለመቋቋም ሃገሪቱን ማስተባበርና ዜጎቿና በማህራዊ ኑሮ ማስተሳሰር ነው ። ችግሮቹ ብዙዎች ናቸው ከባድም ናቸው ። የመንግሥትን እዳ ለመቆጣጠር የበጀት ጉድለታችንን ማስተካከል ይኖርብናል ። የህብረተሰባችን መርህ ሁሉም በእኩልነት ያለአንዳች አድልዎ በመንግሥት የሥራ ተቋማት እንዲሳተፍ ማብቃት ነው ። በአካባቢዎች ሁሉ እኩልነት ሊስፍን ይገባል አንዳንድ የተወሰኑ የከተማ ከፊሎችንና የገጠር አስተዳደሮችን ማለቴ ነው ። »

በኦሎንድ አባባል መፍትሄ የሚያሻቸው የፈረንሳይና ፈረንሳውያን ጉዳዮች በዙ ናቸው ። በዚህ ረገድም ከርሳቸውም ብዙ እንደሚጠበቅ ያውቃሉ ። እነዚህን ችግሮች የሚፈቱባቸው መንገዶችም መፈተኛዎቻቸው መሆናቸውን ጠንቅቀው እንደተገነዘቡ ለመረጣቸው ህዝብ አስታውቀዋል ።

« ሌላው ተጨማሪ ተግዳሮት የአውሮፓ አዲስ መዋቅር የሥራ እድል እድገትና የተሳካ መፃኤ እድል ናቸው ። የሪፐብሊካቸው ፕሬዝዳንት እንድሆን የመረጡኝ ፈረንሳውያን በሁለት ወቅታዊ ጉዳዮች ሳይመዝኑኝ አይቀሩም ብዮ አስባለሁ ። እሱም ፍትሃዊ መሆን አለመሆኔን የወጣቱን ፍላጎት በትክክል የተገነዘብኩ መሆን አለመሆኔ ነው »

Frankreich Wahlen 2012 Francois Hollande Wahlsieg
ምስል dapd

ኦሎንድ መካከለኛ ገቢ ከነበረው ቤተሰብ ነው የተወለዱት ። እናታቸው የማህበራዊ አገልግሎት ሠራተኛ የነበሩ ሲሆን አባታቸው ደግሞ የአንገት በላይ ሐኪም ናቸው ።  የፓሪሱ የፖለቲካ ጥናቶች ተቋም ምሩቅ ኦሎንድ ወደ ፖለቲካው መጠጋት የጀመሩት የዩኒቨርስቲው የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሳሉ ፍርንሷ ሚተሯን ባልተሳካላቸው እጎአ የ 1974 ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ነበር ። ያኔ ኦሎንድ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሥጠት ቢካፈሉም የሶሻሊስት ፓርቲ አባል የሆኑት ግን ከ 5 ዓመታት በኋላ ነበር ። ከዚያም በ 1981 በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር የ26 ዓመቱ ኦሎንድ ደቡብ ፈረንሳዩ Corrèzeውስጥ ነበር ለፈረንሳይ ብሔራዊ ምክር ቤት ምርጫ ከጊዜ በኋላ ፕሬዝዳንት ከሆኑት ዣክ ሺራክ ጋር ተወዳድረው ቢወድቁም ለ 2ተኛ ጊዜ በ 1988 በዚሁ ስፍራ ተወዳድረው አሸንፈዋል ። በ1993 ቱ ምርጫ አልቀናቸውም ። ከዚያም የፓርቲያቸው ቃል አቀባይ የሆኑት ኦሎንድ እንደገና በ Corrèzeተወዳድረው በ 1997 ምክር ቤት ገቡ ። በዚሁ ዓመት የፈረንሳይ ሶሻሊስት ፓርቲ ዋና ፀሀፊ ሆነው ተመረጡ  ። በዚሁ ሃላፊነት ለ11 ዓመታት የቆዩት ኦሎንድ ከ 2001 እስከ 2008 ድረስ የቱል ከተማ ከንቲባ በመሆን አገልገለዋል  ። ከዚያም ከፓርቲያቸው ዋና ፀሃፊነት የለቀቁት ኦሎንድ ወዲያውኑ የኮሬዝ ብሔራዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው በምርጫ እሳካሸነፉበት ጊዜ ድረስ በዚሁ ሃላፊነት እየሰሩ ነበር  ነበሩ ። ኦሎንድ በዚህን መሰሉ የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸው አንድም ጊዜ የሚኒስትርነት ሥልጣን እንኳን አግኝተው አያውቁም ። ኦሎንድ በምርጫ ዘመቻቸው እንዳሉት በአውሮፓ ህብረት ዩሮን ከውድቀት ለማዳን በተስማማበት ውል ላይ እንደገና እንደሚደራደሩ አስታውቀዋል ። ይህም የደጋፊዎቻቸውን ቁጥር ካበዙት ውስጥ አንዱ ነው ። ይህም ትኩረት መሳቡን ኦልንድ ባለፍው እሁድ ባሰሙት ንግግር አልሸሸጉም ።

Francois Hollande Wahlkampf
ምስል Reuters

« አውቃለሁ ዛሬ የአውሮፓ ህዝብ ዛሬ በኛ ላይ ነው ዓይኑን የጣለው ። ውጤቱ እንደታወቀ ይመስለኛል በብዙዎቹ የአውሮፓ ሃገራት እፎያታና ተስፋ አሳድሯል ። የቁጠባ እርምጃ ያለ ምንም ዓይነት አማራጭ የሌለው ሆኖ ሊታይ እንደማይገባ እናሳያለንና ። የኔ ሃላፊነት በአውሮፓ እድገት የሥራ እድልና ብልፅግና እንዲገኝ መሥራት ነው በአጭሩ መፃኤ እድል እንዲስምር ማድረግ ነው ። »

ኦሎንድ 60 ሺህ አስተማሪዎችን ሥራ እንደሚያስይዙ ፣ የሳርኮዚን የጡረታ ማሻሻያ በከፊል እንደሚቀይሩ በሚሊየነሮችም ላይ የ75 በመቶ ታክስ ክፍያ ሥራ ላይ እንደሚያውሉ ተናግረዋል ። ኦሎንድ የፈረንሳይ ኤኮኖሚ እንደሚጠናክር ተስፋቸው ነው ። ይሁንና ባለሞያዎች ይህ ርሳቸው ተግባራዊ አደርጋለሁ ካሉት የበጀት ማስተካካከያ ጋር እንዴት አብሮ መሄድ እንደሚችል እየጠየቁ ነው ።   

በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ከአንድ ሶስተኛው በላይ የፈረንሳይ ህዝብ  ከዮሮ ማህበርና ከሸንገን ስምምነት መውጣትን ለሚደግፉት ፓርቲዎች ነው ድምፁን የሰጠው ።

የኤኮኖሚው ምሁር ኦሎንድ ህዝባቸው ከርሳቸው የሚጠበቀውን ለማሟላት ፈጥነው መንቀሳቅስ ና ብዙም አስተያየት ላልሰጡበት የበጀት ቅነሳ መልስ መፈለግ እንደሚገባቸው ተደጋግሞ የሚነሳ አስተያየት ነው ።

ሂሩትመለሰ

ሸዋዮ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ