1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

የባሕር ውስጥ ማሳ ለዓለም የምግብ ግብዓት ምርት ሁነኛ አማራጭ?

ሐሙስ፣ መስከረም 19 2009

የቀድሞው አሳ አስጋሪ የባሕር ውስጥ ገበሬ ሆኗል። ብሬን ስሚዝ ከኒው ዮርክ አቅራቢያ በሚገኝ የባሕር ዳርቻ የማሳያ እርሻውን መከወን ከጀመረ ሰነባበተ። ስሚዝ የሰው ልጅ የአመጋገብ ሥርዓትን ለመቀየር ሁነኛው መንገድ የባሕር ውስጥ እርሻ ነው የሚል እምነት አለው።

https://p.dw.com/p/2Qgdc
Invasive Algen auf Hawaii
ምስል Rainer Dückerhoff

ተስፋ የተጣለበት የባሕር ዉስጥ ማሳ

 

ከ150 ሚሊዮን ቶን በላይ የፕላስቲክ ተረፈ ምርት በውቅያኖስ ላይ ተንሳፎ ይገኛል። የተራቡ አዳኝ የዓሣ ዝርያዎች ከፍ ያሉ ፕላስቲኮች ምግብ እየመሰለ ያሳስታቸዋል። ብዙ ፕላስቲክ ከዋጡ ደግሞ ይገድላቸዋል። ሳይንቲስቶች እንደ ሻርክ እና አሳነባሪ ያሉ ግዙፍ የባሕር ውስጥ አዳኝ እንስሳት ቁጥር በ910 በመቶ ለማሽቆልቆሉ አንዱ ምክንያት ይኸው ጉዳይ እንደሆነ ያትታሉ። በዓለም ላይ ከሚገኙ የዓሣ ዝርያዎች መካከል እስከ 80 በመቶ የሚሆኑት ዝርያቸው ለመጥፋት አደጋ እስኪጋለጥ በሰው ልጅ ተጠምደዋል። ይህ ከቀጠለ በባለሙያዎቹ እምነት በውቅያኖስ የሚኖሩ እንስሳት ሁሉ ተጠምደው ያልቃሉ።

ዝልግልግ እና ሙልጭልጩ የባሕር ተክል አሊያም አልጌ ባደጉት አገሮች የምግብ ጠረጴዛዎች ላይ ተወዳጅነቱ እየጨመረ የመጣ የምግብ ግብዓት ከሆነ ከራረመ። በርካታ ዝርያዎች ያሉት ይህ አልጌ ለሺህ ዓመታት (በተለይ በጃፓን፣ በኮሪያ እና በቻይና) በምግብነት አሊያም በመድሐኒትነት ሲያገለግል ቢቆይም አሁን ግን ቁጥሩ ወደ ሰባት ቢሊዮን ለተሻገረው የሰው ልጅ ሁነኛ የምግብ ፍጆታ ሊሆን እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል። ከአንድ ሺህ በላይ ዝርያዎች ያሉት አልጌ በጣዕም እና የንጥረ-ምግብ ይዘቱ የዳበረ ነው ይላሉ የሥነ-ምግብ ተመራማሪዎቹ። የአልጌ ዝርያዎችን አምርተው ለገበያ በማቅረብ ሥራ ላይ ከተሰማሩት መካከል ራሱን «የባሕር ውስጥ ገበሬ» ብሎ የሚጠራው ብሬን ስሚዝ አንዱ ነው። ብሬን ስላለፈ ታሪኩ ሲያወራ ከድምፁ ውስጥ ቁጭት ይደመጣል።

«ትምህርቴን አቋርጬ ዓሣ አጥማጅ የሆንኩት የ14 ዓመት ልጅ እያለሁ ነበር። ለአስርት አመታት በፋብሪካ ጀልባዎች ላይ ተቀምጬ ሥነ-ምህዳራችንን በሚጠፋ መንገድ ለማክዶናልድ ሳንድዊች ዓሣ አጠምድ ነበር። በጣም ልጅ ነበርኩ። ነገር ግን እጅጉን አጥፊ በሆነ መንገድ ጥራቱ ዝቅተኛ የሆነ የምግብ ግብዓት እናመርት ነበር። በውቅያኖስ ላይ የነበረኝ ታሪክ ሥነ-ምሕዳር የሚያቃውስ ነበር።»

በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የሰሜን አትላንቲክ ሥነ-ምሕዳር ወድሞ ነበር። በጊዜው በዓሣ ማሥገር የሚተዳደሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሥራ አጥ ሆኑ። ብሬን «አረንጓዴ ማዕበል» (Green wave) በተሰኘ ለትርፍ ያልተቋቋመ እና በአልጌ ምርት ካተኮረ ሥራ ጋር የተዋወቀው ያኔ ነበር።

«ምግብ እንደ ድሮው በተመሳሳይ መንገድ ማምረት አንችልም። እንደ ቀደመው ዘመን አካባቢን እየበከልን መቀጠልም አንችልም። ይህም ምንም አይነት ግብዓት የማይፈልግ የአመራረት ሥልት ነው። ውኃም ሆነ ማዳበሪያ አይፈልግም። በምድራችን ላይ ዘላቂ የምግብ ምንጭ ነው። በተጨማሪም  በምድራችን ላይ በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ የሚቀርብ ምግብም ነው።»

Great Barrier Reef Korallenriff
ምስል Mia Hoogenboom for ARC Centre of Excellence for Coral Reef Studies

በጎርጎሮሳዊው 2014 ዓ.ም. ከባሕር ውስጥ አልጌ የማምረት ሥራው ከስድስት ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ዋጋ ነበረው። ዛሬ ይኸው የአመራረት ሥልት በቻይና፤ በኮሪያ እና በኤንዶኔዥያን በመሳሰሉ አገሮች የባሕር ዳርቻዎች ሲስፋፋ ይታያል። ከባሕር ውስጥ የሚመረቱት በርካታ ዝርያ ያላቸው አትክልቶች በንጥረ-ምግብ የበለፀጉ ናቸው። አልጌዎቹ በካልሲየም፤ መዳብ (ኮፐር) ፤አዮዲን እና ብረት (አይረን) ማዕድኖች የበለፀጉ ናቸው። ፕሮቲን፤ ፋይበር (አሰር) ፣ ቫይታሚን በተለይም ቫይታሚን ኬ ያላቸው እነዚሁ አልጌዎች  የካሎሪ እና ስብ ይዘታቸው አነስተኛ ነው። ለምግብ ግብዓትነት የሚውሉት አትክልቶች ባላቸው በርካታ የቀለም አይነት፤ ቅርፅ፤ መጠን የገበያውን ቀልብ ገዝተዋል። አንድ ኪሎ ግራም አልጌ በዛሬ ገበያ አስራ አንድ ዩሮ ወይም 271 ብር አካባቢ ይሸጣል።

አሜሪካዊው ስሚዝ ዛሬም ኑሮውን የሚገፋው በባሕር ላይ ህይወቱ ቢሆንም የአልጌ አመራረትን ዘላቂ ማድረግ ዋንኛ ትኩረቱ ነው። 20 ሔክታር የሚሰፋውን የባህር ላይ እርሻ ለማስጀመር ያስፈለገው አንድ ጀልባ እና ዘር ለመግዛት 30 ሺህ ዶላር ብቻ ነበር። ስሚዝ የባሕር ውስጥ እርሻውን ሲያዘጋጅ ሳይንቲስቶች ድጋፍ አድርገውለታል።

በባሕር ውስጥ የሚቀመጠው እና የውኃ ውስጥ ነዋሪ ነፍስ ያላቸው ነገሮች እንዲራቡ የሚያግዘው ሰው ሰራሽ ማገጃ ከ150 በላይ ፍጥረታትን ይሰበስባል። ከብረት፤ ብሎኬት እና የብረት ቁርጥ ራጭ የሚሰራው ማገጃ አልጌ የሚመረትበትን አካባቢ በጀልባዎች አደጋ እንዳይደርስበት ይከላከላል። አንዳንዶቹ የመጠለያ መልክ ያላቸው በመሆናቸው ዓሣዎች እና የባሕር እንስሳት እንቁላል የሚጥሉበት፤ የሚሰባሰቡበት እና የሚራቡበት ከባቢ ይፈጥራሉ። መሸርሸርንም ይከላከላሉ። አልጌ በባሕር ውስጥ ማሳ ተዘርቶ እስኪሰበሰብ እና ለገበታ እስኪቀርብ ድረስ ስድስት ወራት ይፈጃል።

ብሬን ስሚዝ ባሕር ውስጥ የሚመረተው ሰብል ወደ ፊት ሁነኛ የሰው ልጅ ምግብ ግብዓት ይሆናል የሚል እምነት አለው። ከአርባ በላይ አገሮች የእሱን የባሕር ውስጥ የአመራረት ስልት ለመጋራት ፈቃደኝነታቸውን ገልጠዋል።

ባሕር ውስጥ ከሚመረቱት መካከል ኬልፕ የተሰኙት ዝርያዎች በሰላጣ መልክ እንደሚበላዉ ኩከንበር ተዘጋጅተው ለረጅም ጊዜ ሳይበላሹ መቀመጥ ይችላሉ። ቅጠላቅጠሎቹን በፓስታ ምትክ መጠቀም እጅጉን እየተለመደ መጥቷል። በሞቀ ውኃ ውስጥ ለአጭር ጊዜ ከተነከረ በኋላ ጠቆር ያለ አረንጓዴ ቀለም ይይዛል። እነዚህ የብሬን ስሚዝ ምርቶች ሪበንን በመሳሰሉ የኒው ዮርክ ምግብ ቤቶች ተወዳጅነትን አትርፈዋል። ማርቲን ብሮክ የሪበን ምግብ ቤት ዋና ምግብ አብሳይ ነው።

«ኬልፕን ልዩ የሚያደርጋቸው ነገር በንጥረ-ምግብ የበለፀጉ ናቸው። ሁል ጊዜም በትኩስነታቸው ብቻ አይደለም የምትመገባቸው። ሲቀዘቅዝም ልትመገበው ትችላለህ። እንደ ሰላጣም ያገለግላል። ወፈር እንዳለ ጭማቂም ሊዘጋጅ ይችላል።»

እስከ ዛሬ ድረስ የኬልፕ ዝርያዎች በአብዛኛው በእስያ ምግቦች ውስጥ ብቻ የነበሩ ቢሆንም አሁን ግን የሌሎች አገሮችን የምግብ ጣዕም እና ፍላጎት በመቀየር ላይ ይገኛል።

«ከወተት የበለጠ ካልሲየም አለው። ከቀይ ሥር የበለጠ በአይረን የበለፀገ ነው። በአጠቃላይ በበርካታ ንጥረ-ምግቦች የዳበረ ነው። በውስጡ ያለው ስብ ደግሞ አነስተኛ ነው።» ይላል ማርቲን ብሮክ።

Damselfish
ምስል picture-alliance/Mary Evans Picture Library

የተባበሩት መንግስታት ዩኒቨርሲቲ ባለፈው ዓመት ይፋ ባደረገው ጥናት መሠረት በጎርጎሮሳዊው 2014 ዓ.ም. በባሕር ላይ ከተሰበሰበው 27.3 ሚሊዮን ቶን ምርት አልጌ 49% ድርሻ ነበረው። የዩኒቨርሲቲው ጥናት አሁንም በፍጥነት እየተስፋፋ የሚገኘው ይኸው ዘርፍ ለአምራቾቹም ሆነ ለከባቢ አየር አዳዲስ ፈተናዎችን እየፈጠረ እንደሆነ አትቷል። ወቅታዊው የባሕር ምርት እድገት በባሕር ውስጥ ያልነበሩ የፍጥረታት በሽታዎች እና ተባዮች መስፋፋት በር ሊከፍት እንደሚችል ይኸው ጥናት ጠቁሟል። ሳይንቲስቶች የተሻለ የምግብ ግብዓት ፈጥሮ በባሕር ውስጥ ለማምረት የሚያደርጉት ጥረትም በጥናቱ የተጠቀሰ ሌላ ስጋት ነው።

በአሜሪካ የምትሔድበት እንጂ የመጣህበት ፍሬ የለውም የሚሉት አባባል አላቸው። ብሬን ስሚዝ የሚሔድበትን ጠንቅቆ ያውቃል። ዓላማው ዓለምን የተሻለ ቦታ ማድረግ ነው።

«በእኔ ፍላጎት አንድ ቀን በጀልባዬ ላይ መሞትን እመርጣለሁ። ያ የእኔ ስኬት እና ህልም ነው። ይህ ሥራ ቀሪ ህይወቴን በውቅያኖስ ላይ እንዳሳልፍ ያግዘኛል። በተጨማሪም አንድ ፍሬ ያለው ነገር እንድሠራ ይረዳኛል። አገራችንን ለመመገብ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የራሴን ትንሽ አስተዋፅዖ እንዳበረክት፤ የከባቢ አየር ለውጥንና በረሃማነትን ለመከላከል።»

የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ባለሙያዎች የባሕር ውስጥ ምርት የሚያስከትላቸው ጫናዎች መኖራቸውን ባይክዱም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉትም በድረ-ገጽ ባሰፈሩት መረጃ ላይ አመልክተዋል። እጅጉን ለተጎዳው የምድር የዓሣ ሐብት አማራጭ መሆን እንደሚችልም ገልጠዋል። በተለይ ዳይናማይት የተሰኘውን መርዛማ ንጥረ-ነገር በመጠቀም ዓሣ ለሚያሰግሩ አገሮች አማራጭ የሥራ ዘርፍ እና የምግብ ግብዓት የመሆን እድል እንዳለው አስፍረዋል። በባሕር ውስጥ የምግብ ግብዓት የሚያመርቱ እንደ ብሬን ስሚዝ ያሉ ባለሙያዎች ጎን ለጎን የዓሣ ርባታን ለማሳደግ እውቀቱም ክህሎቱም አላቸው።

ተስፋ የተጣለበት የባሕር ዉስጥ ማሳ

 

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ