1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተቃዉሞ ሰልፍና እስራት በካይሮ

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 18 2006

የግብፅ የሽግግር መንግስት የሙስሊም ወንድማማቾች ማኅበርን በአሸባሪነት ከፈረጀ በኋላ ዛሬ ለተቃዉሞ የወጡ ደጋፊዎቹ ከፖሊስ ጋ ተጋጭተዋል። ድንጋይ ይወረዉሩ እንደነበር የተገለጸዉን የቡድኑን ደጋፊዎች ለመበተንም ፖሊስ የሚያስለቅስ ጭስ ተጠቅሟል።

https://p.dw.com/p/1Ahg4
ምስል Reuters

የግብፁ ሙስሊም ወንድማማቾች ማኅበር አንጋፋና እድሜ ጠገብ ስብስብ መሆኑ ነዉ የሚገለጸዉ። በጎርጎሪዮሳዊዉ 1928ዓ,ም ተመስርቶም በግብፅ ዉስጥ አለ የተባለ በአግባቡ የተደራጀ የፖለቲካ ኃይል ሆኖ በመቆየት፤ ባለፈዉ ለምርጫ ተወዳድሮ ሞሐመድ ሙርሲን ለፕሬዝደንትነት ያበቃም በመሆኑ ይታወቃል። የሽግግር መንግስቱ ሙስሊም ወንድማማቾችን በአሸባሪነት የፈረጀዉ በአንድ የፖሊስ ሕንፃ ላይ አጥፍቶ ጠፊ ባደረሰዉ ጥቃት የ15 ሰዎች ህይወት ካለፈ በኋላ ነዉ። ሌላ አንድ ጀሃዳዊ ቡድን ለድርጊቱ ኃላፊነቱን ቢወስድም በይፋ ተጠያቂ የሆነዉ የሙስሊም ወንድማማቾች ማኅበር ነዉ። የግብፅ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆሳም ኤይሳ እንዲህ ነዉ ያሉት፤

«መንግስት እንደገና ወደኋላ መመለስ የማይችል መሆኑን በድጋሚ ማረጋገጥ ይሻል። ስለሆነም መንግሥት፤ በሕገ መንግሥት አንቀጽ 86፣ የወንጀለኛ መቅጫ ደንብ መሠረት የሙስሊም ወንድማማችነት ማህበር አባላት አሸባሪዎች ፤ ድርጅቱም አሸባሪ ነው። ስለሆነም እርሱን በጽሑፍም ሆነ በቃል ፣ የሚያበራታቱ ወይም በሌላ ዓይነት መንገድ የሚረዱና ተግባሩን በገንዘብ የሚደግፉ የወንጀል ተባባሪዎች ናቸው። እንዲሁም በአንቀጽ የተገለጠው ቅጣት፤ በማንም ተባባሪ ግለሰብም ሆነ ቡድን ላይ ተፋጻሚ ይሆናል»።

Ägypten - Proteste in Kairo
ምስል Reuters

ሙስሊም ወንድማማቾች በአሸባሪነት መፈረጁን በማዉገዝ ሰላማዊ ተቃዉሞዉን እንደሚቀጥልበት አስታዉቋል። ደጋፊዎቹም ተቃዉሟቸዉን ቀጥለዋል። ሙስሊም ወንድማማቾች ማኅበር ደጋፊዎች ቃል አቀባይ አያ አላ በጥድፊያ ቡድኑን ከአሸባሪዎች ተርታ ያሳለፈዉ ዉሳኔ ተገቢ አይደለም ሲሉ ይሞግታሉ፤

«የሙስሊም ወንድማማቾች የሚሰነዘረዉ ዉንጀላ መሠረተ-ቢስ ነዉ። አልተረጋገጠም። በጥድፊያ የተደረገ ዉንጀላ ነዉ። የሐገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አላፀደቀዉም። መንግሥት ሙስሊም ወንድማማቾችን የወነጀለበትን ፍንዳታ ያደረሰዉ ሌላ ቡድን ነዉ።»

ዋና ከተማ ካይሮ አንድ ጓዳ ሠራሽ ፈንጂ በህዝብ መጓጓዣ አቅራቢያ ፈንድቶ አምስት ሰዎች ከቆሰሉ በኋላ ዉጥረት ነግሶባታል። መንግስት ረቡዕ ዕለት ቡድኑን በአሸባሪነት ከመዘገበ በኋላ እሱን በመደገፍ አደባባይ የሚወጣ ሰልፈኛን እንደማይታገስ ፖሊስ ዝቷል። ዛሬ ከካይሮ የወጡ ዘገባዎች አልአዝሃር ዩኒቨርሲቲ ጊቢ የተማሪዎች ማደሪያ ዉስጥ ጭስ ይታይ እንደነበር ያመለክታሉ። የአዣንስ ፍራንስ ፕረስ ፖሊሶች አስለቃሹን ጭስ ከተኮሱ በኋላ ሁኔታዉ መከተሰቱን ነዉ የገለፀዉ። ተማሪዎችም ድንጋይ ወርዉረዋል። የሙስሊም ወንድማማቾች ማኅበር አባል የነበሩት የቀድሞዉ ፕሬዝደንት ሞሐመድ ሙርሲ እስር ላይ ናቸዉ።

Pro-Mursi Proteste in Kairo 04.11.2013
ምስል Khaled Desouki/AFP/Getty Images

ከእሳቸዉ ሌላም የቡድኑ አመራር አካላት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ወህኒ ወርደዋል። ሙርሲ ከስልጣን ከተነሱበት ካለፈዉ ሐምሌ ወር አንስቶም ሙስሊም ወንድማማቾች ባለማቋረጥ የተቃዉሞ ሰልፉን ቀጥሎበታል። የግብፅ የፀጥታ ኃይሎች በመላ ሀገሪቱ ዛሬ ለሰልፍ ከወጡ ደጋፊዎች ጋ ተጋጭተዋል፤ ከመቶ በላይ ሰዎችን አስረዋል። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ግጭት መቀስቀሱ ነዉ የተገለፀዉ። ካይሮ ዉስጥ መሳሪያ የተጠመደባቸዉ ተሽከርካሪዎች የከተማዉን ዋና አደባባይ መንገድ ዘግተዋል። ሙርሲ ከስልጣን ከወረዱ ወዲህ በየጊዜዉ ተመሳሳይ የተቃዉሞ ሰልፉ ቀጥሏል፤ ሰልፉን ለመበተን በሚወሰድ ርምጃም በሺዎች የሚገመቱ ሰዎች ህይወት አልፏል። በሺዎች የሚገመቱ የቡድኑ ደጋፊዎች ታስረዋል። በተለይ በከፍተኛ ስልጣን ላይ የነበሩት አባላቱ በየሰላማዊ ሰልፉ ለሞቱ በተጠያቂነት፣ በሀገር ክህደት እንዲሁም በአሸባሪነት ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ