1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተቃዉሞ በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ፤

Merga Yonas Bulaሰኞ፣ ሐምሌ 25 2008

በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ የወልቃይት ጠገዴን የማንነት ጥያቄ መነሻ አድርጎ፤ ሌሎች የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲሁም የሰበዊ መብቶች ረገጣ በሰላማዊ መንገድ መልስ ይሰጥበት ሲሉ የከተማዋ እና የአከባቢዉ ነዋሪዎች ተቃዉሞ ሲያሰሙ ሰንብተዋል።

https://p.dw.com/p/1JZq7
12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

[No title]

በትላንትናዉ እለትም በዚሁ ከተማ ህዝቡ ተመሳሳይ ጥያቄ ይዞ በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ታጣቂ ኃይል የሚወስደዉን ርምጃ እንደሚቃወሙ፣ የሙስሊም ማህበረሰቡ ላይ የሚወሰደዉ <ኢሰባአዊ> ርምጃዎችንም እንደሚያወግዙ፤ እንዲሁም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያለዉ የሰባዓዊና የዲሞክራሳዊ መብቶች ጥሰት እንዲቆም መጠየቃቸዉ ተዘግቧል።


በታቃዉሞዉ ላይ ከመልካም አስተዳደርና ከፍትህ ጋር የተያያዘ መፈታት ያለባቸዉ ትክክለኛ ጥያቄዎች መነሳቱን የሚናገሩት የአማራ ክልል የኮሙኒኬሸን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን በዛዉ መጠን ደግሞ <<ትክክል ያልሆኑ፣ ሕገ መንግሥቱን የሚቃረኑ መልዕክቶችም ተላልፈዋል>> ሲሉ ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል።

ሰልፈኞቹ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ እንደሚፈልጉ ለከተማ አስተዳደሩ ጥያቄ ቢያቀርቡም አንድ ሰላማዊ ሰልፍ ማሟላት የሚገባዉን አላሟሉም ስለዚህ ሰልፉ ከክልሉ እዉቅና ዉጭ ነዉ የተደረገዉ ይላሉ አቶ ንጉሱ። ይሁን እንጅ <<በጎንደር ከተማና አከባቢዉ ህዝብ ሰላማዊ ኑሮ ላይ ተፅዕኖ ሳያሳድር፣ ዲሞክራስያዊ የሆኑም ዲሞክራስያዊ ያልሆኑም ምልክቶች ተላልፎበት>> ሰልፉ በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቅ ችለዋል ይላሉ።


ማኅበረሰቡ ጥያቄ አለኝ ብሎ ሰላማዊ ሰልፍ አድርጓል ስለዚህ የክልሉ መንግስት ይህን ለመመለስ ምን እያደረገ ይገኛል ለሚለዉ ጥያቄ አቶ ንጉሡ በፍትህ እና የመልካም አስተዳደር ላይ የሚነሱት ጥያቄዎች መንግሥት እልባት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

Fasil Schloss Gonder Äthiopien
ምስል DW/Azeb Tadesse Hahn

በዚህ ጉዳይ ላይ የጎንደር ነዋሪ ነኝ ያሉ ግን ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ አስተያት ሰጭ ተቃዉሞ ማድረግ <<ጥሩ>> ነዉ ብሉም ግን ይህ ተቃዉሞ ህዝብን የሚያጋጭ ነዉ ይላሉ።

የደሴ አከባብ ነዋሪ ነኝ ያሉት ሌላ አስተያያት ሰጭ ወደ ጎንደር ሄደዉ ተቃዉሞዉ ላይ መሳተፍ ቢፈልጉም የደሕንነት ስጋት አድሮባቸዉ እንደቀሩ ከተናገሩ በኋላ ተቃዉሞዉ ትክክል እና ተገቢ ነዉ ይላሉ።

በዶቼ ቬሌ የፌስቡክ ደረ ገፅ ላይ ከተሰጡን አስተያያቶች ዉስጥ <<ቢኖር ቢኖር ሕገወጥ ግለሰብ እንጂ ሕገወጥ ሕዝብ የለም>>፣ <<በጣም የሚገርመው ነገር ህዝብ ጥያቄ እያነሳ የትምክተኛ አስተሳሰብ ነው የሚባለው ምን ያህል ንቀት እንዳለ ማሳያ ነው>> ስለዚህ <<መንግሥት ምንም አይነት ምክንያት ሳያበዛ ለተጠየቁት ጥያቄዎች ትክክለኛ ምላሽ መስጠት ነው ያለበት>> ሲሉም አስተያየተቸዉን ሰንዝረዋል።

መርጋ ዮናስ

ነጋሽ መሃመድ