1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተቃውሞ በደቡብ አፍሪቃ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 18 2008

በደቡብ አፍሪቃ ገዢው የአፍሪቃውያን ብሔረተኞች እንቅስቃሴ»፣ በምህፃሩ፣ «ኤ ኤን ሲ» የፊታችን እጎአ ነሀሴ ሶስት፣ 2016 ዓም ለሚካሄደው የፕሪቶርያ ከተማ ምክር ቤት ምርጫ ለከንቲባነቱ ቦታ ከጥቂት ጊዜ በፊት አንድ እጩ በተወዳዳሪነት አቅርቦዋል።

https://p.dw.com/p/1JChu
Südafrika Proteste in Pretoria gegen Bürgermeister-Kandidat
ምስል Reuters/S. Sibeko

[No title]

ይኸው የገዢው ፓርቲ ውሳኔ የ«ኤ ኤን ሲ» ያካባቢ ቅርንጫፎችን ፍላጎት ያላከበረ ነው። የፕሪቶርያም ሕዝብ ማዕከላዩ መንግሥት ላካባቢ ምክር ቤታዊ ምርጫዎችም እጩዎችን የመረጠበትን ርምጃውን በጥብቅ በመንቀፍ በከተማይቱ ግዙፍ ተቃውሞ ከጀመረ አምስተኛ ቀኑን ይዞዋል። በተቃውሞው በቀጠለው ተቃውሞ ወቅት ተሽከርካሪዎች እና በተለይ አውቶቡሶች ብቻ ሳይሆኑ፣ በውጭ ዜጎች የተያዙ መደብሮችም በእሳት ጋይተዋል። በዚሁ ጊዜ በተፈጠረው ግጭትም ቢያንስ አራት ሰዎች ሞተዋል። ፖሊስም መደብሮችን ዘርፈዋል ያላቸውን 40 ተጠርጣሪዎችን አስሮዋል።
ተቃውሞው እና ግጭቱ እዚህ ደረጃ ላይ ለደረሰበት ድርጊት ገዢው የአፍሪቃውያን ብሔረተኞች እንቅስቃሴ» ተጠያቂ ነው በሚል በፕሪቶርያ በሚገኘው የደቡብ አፍሪቃ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩት የፖለቲካ ተንታኝ ሳሞዶዳ ፊኬኒ ወቅሰዋል።
« በ«ኤ ኤን ሲ» ውስጥ ያለው ማህበራዊ ችግር ራሱ ባለፉት አስር ዓመታት ስር በሰደደው የአንጃ ክፍፍል እየተባባሰ መጥቶዋል። ይኸው ክፍፍል በፈጠረው የፖለቲካ ባህልም ውስጥ የኃይል ተግባር እንደ ፖለቲካ መግባቢያ መሳሪያ ሆኖ ማገልገል ጀምሮዋል። »

ይሁንና፣ ፊኬኒ አክለው እንደገለጹት፣ ተቃውሞ ከወጡት መካከል ብዙዎቹ ለፕሪቶርያ ከንቲባነት እጩ ሆነው የመቅረብ ፍላጎት የነበራቸው እና ፍላጎታቸው የፓርቲውን ድጋፍ ያላገኘላቸው የ«ኤ ኤን ሲ» አባላት ደጋፊዎች ናቸው። ለከንቲባነቱ ስልጣን እጩ ሆኖ የቀረበው የፓርቲ አባል ከሌላ ግዛት የመጣ ነው፣ እና የከተማይቱ ሕዝብ እጩ ተወዳዳሪው ስላካባቢው በቂ እውቀት የለውም በሚል በፓርቲው ውሳኔ አኳያ ብርቱ ወቀሳ ሰንዝሮዋል።

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የኃይል ተግባር እጎአ ከ2010 ዓም ወዲህ እየጨመረ መጥቶዋል። ዋና ጽሕፈት ቤቱ በፕሪቶርያ የሚገኘው እና በእንግሊዝኛ ምህፃሩ፣ «አይ ኤስ ኤስ» የተባለውዓለም አቀፍ የፀጥታ ጥበቃ ተቋም ኃላፊ ዶክተር ጃኪ ሲልየርስ ከጥቂት ጊዜ በፊት ያካሄደውን ጥናት ጠቅሰው እንዳስረዱት፣ የኃይሉ ተግባር እየተባባሰ ለሄደበት ድርጊት ከፖለቲካ አመራር መንግሥት በኩል ተጠያቂነት መጓደሉ ነው።

Südafrika Proteste in Pretoria gegen Bürgermeister-Kandidat
ምስል picture-alliance/Zuma Press/Xinhua

« ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በወቅቱ የሚታየው፣ ቀደም ሲል እንዳልኩት፣ የምትሰራው ነገር ካላንዳች ርምጃ የሚታለፍበት አሰራር ነው። እንበል፣ ቁሳቁሶችን ብትሰብር ቅጣት አይጠብቅህም። ስለዚህ፣ መሰባበርህን ቀጥል፣ ምክንያቱም፣ ትኩረት ታገኛለህ። ችግሩ ያለው ውሳኔ የሚወሰድበት አሰራር ሂደት ተጠያቂ ባልሆነ አመራር መውጣቱ ነው። አመራሩ ተጠያቂ ካልሆነ እና መሰባበርን የመሰለ የኃይል ተግባር ፈፅመህ የማትቀጣ ከሆነ ፣ ይህንን በአካባቢ አስተዳደር ደረጃስ ለምን አታደርግም? »

«ኤ ኤን ሲ» ግን የሰሞኑ ሁከት እና ግጭት የራሳቸውን ጥቅም ለማስቀደም በማሰብ ወደ ፓርቲው ሰርገው የገቡ ሰዎች ስራ ነው ብሎ እንደተመለከተው የ«ኤ ኤን ሲ» ዋና ጸሐፊ ግዌዴ ሞንታሼ ገልጸዋል።

« ይህንን ሁከት ያቀዱ የ«ኤ ኤን ሲ» መሪዎች የሆኑ ሰዎች ስም እና ፎቶግራፎች አሉን። ይህ አሳፋሪ ተግባር በመሆኑ ፣ ስማቸው የተጠቀሱትን ሰዎች ፖሊስ ሊከባቸው እና ሊያስራቸው ይገባል ። ከዚያ በዚሁ ችግር አኳያ የሚያስፈልገውን ርምጃ እንወስዳለን።»

ሁከቱ እና ግጭቱ ጆሀንስበርግን እና ፕሪቶርያን በሚያጠቃልለው በጋውቴንግ ግዛት ሊቀጥል እንደሚችል ፖሊስ አስጠንቅቋል።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ