1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተገን ጠያቂዎቹ ክስ መሠረቱ

ሐሙስ፣ ኅዳር 19 2006

ባህር ዉስጥ ከመስጠም የተረፉ ሶስት ኢትዮጵያዉን ተገን ጠያቂዎች ከትናንት በስተያ የቤልጂየም ጦር ሠራዊት ላይ ክስ መሠረቱ። ከሁለት ዓመታት በፊት በጀልባ የተጫኑ አፍሪቃዉያን ስደተኞች ወደጣሊያን ሲጓዙ ለአደጋ መጋለጣቸዉን ከተመለከቱ በአካባቢዉ ከነበሩ ኃይሎች ርዳታ ባለማግኘታቸዉ 63ቱ ህይወታቸዉ አልፏል።

https://p.dw.com/p/1AQE4
ምስል picture-alliance/ROPI

በጎርጎሪዮሳዊዉ 2011 መጋቢት ወር ላይ ነዉ 72 ስደተኞች ከሊቢያ ወደጣሊያን ለመጓዝ ሜዲትራኒያን ባሕር መሀል ሲደርሱ የጫነቻቸዉ የፕላስቲክ ጀልባ ድንገት ተሰናከለች። እናም ያለምንም ርዳታ፤ ምግብ እና ዉሃ ለ15 ቀናት ባህር መሃል ሊንሳፈፉ ግድ ሆነ። በወቅቱ ሊቢያ ዉስጥ በነበረዉ ሕዝባዊ አመፅ ሰበብ በነበረዉ ጦርነት ምክንያት ባህሩ ላይ የተለያዩ ሃገራት የባህር ኃይሎች ተሰማርተዋል፤ አንዳቸዉም ግን ስደተኞችን ሊያድኗቸዉ አልፈለጉም። ከአደጋዉ ከተረፉት አንዱ እንደገለጸዉ፤ አንዲት ሄሊኮፕተር አራትና አምስት ጊዜ አንዣበበችባቸዉ፤ እንደዉም ባልተለመደ ሁኔታ ዝቅ ብላ ስለነበር አብራሪዉን ሁሉ ተመልክተዋል፤ እናም ሊታደጉን ነዉ የሚል ተስፋ አደረባቸዉ። ግን ማንም ብቅ አላለም። የተጨነቁት ስደተኞች በወቅቱ ስልክ እንደደወሉላቸዉ የሚናገሩት ለስደተኞች የሚሟገተዉ አዠንሲያ ሃበሻ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አባ ሙሴ ዘርዓይ ሁኔታዉን እንዲህ ይገልጻሉ።

Italien Marine im Einsatz bei Lampedusa
ምስል Getty Images

አባ ሙሴ እንደሚሉት በተባሉት 15 ቀናት የተለያዩ ሃገራት መርከቦች ስደተኞቹ ያሉበትን አደገኛ ሁኔታ አይተዋል። ግን ሊረዷቸዉ አልሞከሩም። በአጋጣሚዉም ከመካከላቸዉ 63ቱ ስደተኞችም በርሃብና ጥማት ለሞት ተዳረጉ። በሂደቱም ዓለም ዓቀፍ የባህር ሕግ በመጣሱ በሕግ ሊጠየቁ የሚገባቸዉ አሉ።

የስደተኞቹ የድረሱልን ጥሪ ለጣሊያን የባህር ድንበር ጠባቂዎች ሲተላለፍ፤ እነሱንም ለሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን የትብብር ማዕከል እንዲሁም በስፍራዉ ለነበሩ የጦር መርከቦች ማስተላለፋቸዉ ነዉ የተነገረዉ። ይህ ጥሪም ለተከታታይ 10 ቀናት በየአራት ሰዓት ልዩነት መደጋገሙም እንዲሁ። ሊረዳቸዉ የመጣ አካል ግን አልነበረም። አዉሮፕላን፤ ወታደራዊ ሄሊኮፕተር፤ የአሳ ማስገሪያ ጀልባዎች እንዱሁም ትልቅ ወታደራዊ መርከብ ሁሉ እያዩዋቸዉ እንደዋዛ አልፈዋል። ከሞት ጋ ተፋጠዉ 15 ቀናትን ከገፉት መካከል በህይወት የተረፉት 11 ናቸዉ። 63ቱ 20 ሴቶችና 3 ህጻናትን ጨምሮ ሞቱ።

ጉዳዩን የመረመረዉ የአዉሮጳ ምክር ቤት የፓርላማ ኮሚቴ በወቅቱ የስደተኞቹን ህይወት ማትረፍ የሚያስችሉ አጋጣሚዎች መታለፋቸዉን፤ የሀገራቸዉን ሰንደቅ ዓላማ እያዉለበለቡ ሳይረዷቸዉ በአካባቢዉ ያለፉ መርከቦችም የባሕር ሕግ መጣሳቸዉን አረጋግጧል።

Spanien Frontex Boot
ምስል Desiree Martin/AFP/Getty Images

በወቅቱ የጣሊያን፤ ፈረንሳይ፤ ስፔን፤ ብሪታንያ፤ ካናዳ እና ዩናይትድ ስቴትስ የባህር ኃይሎች በአካባቢዉ እንደነበሩ የተገለጸ ሲሆን እስካሁን ካናዳን ጨምሮ፤ ጣሊያን፤ ስፔንና ፈረንሳይ ክሱ ቀርቧል። የተገን ጠያቂዎቹን ጉዳይ በመደገፍ ክሱን ወደፍርድ ቤት እንዲያመራ የሚደግፉት በአዉሮፓ የበርካታ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጥምረት ፍትህ ለማግኘት እንደሚገፋበት ነዉ ያመለከተዉ። የጥምረቱ አካል የሆኑት አባ ሙሴ ዘርዓይም ይህኑ ይገልጻሉ።

እንደእሳቸዉ እምነትም ለዚህ የሚገኘዉ ምላሽ በቅርቡ ላምፔዱዛ ደሴት ተቃርበዉ ሳለ የሚረዳቸዉ አጥተዉ ሰጥመዉ ካለቁ ወገኖች ጋ አብረዉ የነበሩና ተገደዉ ወደሊቢያ እንዲመለሱ የተደረጉትንም ጉዳይ ዓለም ዓቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ መንገድ ይከፍታል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ