1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተግባር የናፈቀዉ የአየር ንብረት ለዉጥ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 9 2008

ቦን ከተማ የአየር ንብረት ለዉጥ ተመልካች ጉባኤ ፓሪስ ላይ ባለፈዉ ኅዳር ወር ማለቂያ ላይ የተደረሰዉን ስምምነት ወደተግባር ለመለወጥ የሚቻልበትን መንገድ የሚቀይስ ግዙፍ ጉባኤ ከትናንት አንስታ እያስተናገደች ነዉ።

https://p.dw.com/p/1IpGr
Nordpol Flagge im Eis : Pole to Paris
ምስል Pole to Paris

ተግባር የናፈቀዉ የአየር ንብረት ለዉጥ

የጉባኤዉ አዘጋጅ የሆነዉ የተመ የአየር ንብረት ለዉጥ ተከታታይ መድረክ እስከዛሬ ዉጤት ለማሳየት የተጓተተዉ ሂደት ከዚህ በኋላ ፍጥነት እንደሚኖረዉ ተናግሯል።

ትናንት ጉባኤዉ ሲጀመር ንግግር ካደረጉት ኃላፊዎች አንዷ የተመ የአየር ንብረት ለዉጥ መድረክ ዋና ጸሐፊ ክሪስቲያና ፊጎረስ ፓሪስ ላይ የተደረሰዉ ስምምነት እዉን እንዲሆን የሁሉም ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

«ዛሬ ለሁላችን የተለየ ዘመን መሆኑን የሚያመለክት ዕለት ነዉ። ፓሪስ ላይ የደረሳችሁት ስምምነት ታሪካዊ ስኬት ሆኖ ተመዝግቧል። በእርግጥም ነዉ። አሁን ሁላችሁም ያ እዉን እንዲሆን የጋራ ራዕያችሁ መሆኑን ለማሳየት መሥራት ይኖርባችኋል።»

ባለፈዉ ኅዳር ወር ፓሪስ ላይ የተደረሰዉ ስምምነት በተለይም የዓለም የሙቀት መጠን ከ2 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በታች እንዲሆን የብክለት መጠንን መቀነስ ያስፈልጋል የሚለዉ መግባቢያ ነዉ። እያንዳንዱ ሀገርም በየግሉ የሚቀንሰዉን የራሱን የብክለት መጠን ማቅረብ ይጠበቅበታል። ክርስቲያና ፊጎረስ ከዚህ ቀደም የአየር ንብረት ለዉጡን ለመግታት ለሚደረገዉ ጥረት የበኩላቸዉን ለመተባበር ፈቃደኝነታቸዉን በፊርማቸዉ ያረጋገጡ ከ119 ሃገራት የማይበልጡ እንደነበሩ አስታዉሰዋል። እሳቸዉ እንደሚሉት ግን ከፓሪሱ ጉባኤ መግባባት በኋላ 195 ሃገራት አዎንታዊ አቋም መያዛቸዉን በፊርማቸዉ ሲገልፁ፤ ባለፈዉ ወር ኒዉዮርክ ላይም በተመሳሳይ ጥረታቸዉን ለማጠናከር ቃል የገቡት ፈራሚ ሃገራት ቁጥር 175 ደርሷል። ሃገራቱ የአየር ንብረት ለዉጥን የሚያስከትሉ እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተዉ ለመሥራት የመወሰናቸዉ መንስኤ እና ምናልባትም የተመድ የአየር ንብረት ለዉጥ ተመልካች ጉባኤ ከሚፈልገዉ የጋራ ስምምነት ዉሳኔ ለመድረስ ለዓመታት የተጓተተዉ ሂደት ይፋጠናል ብለዉ የሚያምኑበትን ምክንያት ዋና ጸሐፊ ክርስቲያና ፊጎረስ በጋዜጣ ጉባኤዉ ወቅት ሳይጠቁሙም አላለፉም።

Bangladesh Flusserosion Klimawandel
ምስል picture-alliance/Zumapress.com

«አሁን ለምን ሂደቱ ይፋጠናል ብዬ ያሰብኩበትን ምክንያት ለማወቅ ከፈለጋችሁ፤ የአየር ንብረት ለዉጥ ስጋት አሁን ሙሉ በሙሉ ሁሉም ገብቶታል። በዚያም ላይ በዚህ ዓመትም ሆነ በዛሬዋ ዕለት ጭምር የሙቀት መጠኑ ከፍ እያለ መሄዱን ከሳይንስ ምርምርና በመላዉ ዓለም ያስከተለዉን ተፅዕኖ እያየን ነዉ።»

የቦኑ የተመድ የአየር ንብረት ለዉጥ ተመልካች ጉባኤ አዘጋጆቹም ሆነ ጉዳዩን በቅርበት የሚያዉቁት ባለሙያዎች እንደሚሉት ፓሪስ ላይ 195ቱ ሃገራት በወረቅት ላይ ያሠፈሩት ስምምነት ወደተግባር የሚመነዘርበትን መንገድ የማመቻቸት ሥራ እንደሚሠራ ይጠበቃል። እስከዛሬ የአየር ንብረት ለዉጥና መዘዙ ከሩቅ ይታያቸዉ የነበሩት የፖለቲካ ፈቃደኝነት የራቃቸዉ መንግሥታትም ደጃቸዉን የሚያንኳኳ የተፈጥሮ ቁጣ ማስተናገድ መጀመራቸዉ የየዕለት ዜና ከሆነ ሰነበተ። እንደድሃዎቹ እና በቴክኒዎሎጂም ሆነ ኢንዱስትሪዉ እድገት ኋላ እንደቀሩት የአፍሪቃም ሆነ የእስያ ሃገራት ጉዳታቸዉ በቶሎ ባይታይም፤ እንደአሜሪካም ሆነ ቻይና ያሉት ግንባር ቀደም የዓለማችን ከባቢ አየር በካዮች ለከፋ ድርቅና የዉኃ እጥረት የጠናባቸዉ ግዛቶች አሏቸዉ። ያም ሆነ ይህ ታሪካዊዉ የፓሪሱ ስምምነት የገዘፈ ስሙን ይዞ የሚዘልቀዉ ከእንግዲህ ሃገራቱ በሚያስመዘግቡት ተጨባጭ የብክለት ቅነሳ መጠን በመሆኑ ካለፉት ዓመታት ይልቅ ሥራዉ አሁን የተጀመረ ይመስላል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ