1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተጨማሪ ምግቦች

ማክሰኞ፣ ግንቦት 30 2008

«ሰዉ የሚመገበዉን ይመስላል» ይባላል። ለጤናማ ሰዉነት ግንባታ የተለያዩ ቫይታሚኖችና ማዕድኖች ያስፈልጋሉ። እያንዳንዱ ሰዉ በየዕለቱ ከሚመገበዉ ምግብ እነዚህን ያገኛል ተብሎ ይታሰባል። ከዕድሜም ሆነ ከአመጋገብ አቅም ጋር በተገናኘ በሰዉነት ዉስጥ የተፈላጊ ንጥረነገሮች መጓደልን ደግሞ ተጨማሪ የምግብ ቅምሞች ያካክሱታል በሚል ለገበያ ይቀርባል።

https://p.dw.com/p/1J25d
05.10.2010 DW-TV Fit und gesund Nahrungsergänzungsmittel

ቅምም ተጨማሪ ምግቦች

ቅምም ተጨማሪ ምግብ ተብለዉ በተለያዩ ፋብሪካዎች ከተለያዩ ምንጮች ተጠጋጅተዉ ለሽያጭ በኪኒንም ሆነ በዱቄት መልክ የሚቀርቡት ጥቅማቸዉ እንደመድኃኒት ሳይሆን እንደምግብ ብቻ መሆኑን በቅድሚያ ማወቅ እንደሚገባ ነዉ ጥናቶችም ሆኑ ያነጋገርናቸዉ ምሁራን የሚያሳስቡት። በተጨማሪ ምግብነት ከሚቀመሙት ቫይታሚኖች፣ ማዕድኖች፣ ፋይበር(ጭድ) ፣ ፋቲ አሲድ ወይም አሚኖ አሲድ እና የመሳሰሉትን ንጥረነገሮች መጥቀስ ይቻላል። አሜሪካን ዉስጥ ብቻ ከ50 ሺህ የሚበልጡ የተጠቀሱት ዓይነት ቅምም ተጨማሪ ምግቦች ገበያ ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከ53 እስከ 55 በመቶ የሚገመተዉ በአዋቂ የዕድሜ ክልል የሚገኝ አሜሪካዊም በየዕለቱ ይህን ተጨማሪ የምግብ ቅምም ይወስዳል። እዚያ እጅግ የሚዘወተረዉ ደግሞ መልቲ ቫይታሚን ነዉ። የሀገሪቱ የጤና ጥበቃ ተቋም ታዲያ ፤ እነዚህ የምግብ ቅምሞች ከየትኛዉም በሽታ አያድኑም፤ መድኃኒቶችም አይደሉም፤ ሲል ግልጽ ማስጠንቀቂያ ለሕዝቡ ሰጥቷል።

Symbolbild funktionelle Lebensmittel
ምስል imago/M.Zettler

የአዉሮጳ ኅብረትም በአባል ሃገራት ዉስጥ ለገበያ የሚቀርቡትን የተጨማሪ ምግብ ቅምሞች በየጊዜዉ ጥራታቸዉን ይከታተላል፤ ይመዝናልም። ንጥረነገሮቹ በሰዉነት ዉስጥ በሃኪም ምርመራ የሚታየዉን የቫይታሚንም ሆነ ማዕድን ጉድለት ሊያስተካክሉ፤ ወይም ተፈላጊዉን መጠን ጠብቀዉ ሊያቆዩ እንደሚችሉ አስረግጦ ቢገልጽም፤ አንድም መድኃኒት እንዳልሆኑ፤ አልፎ ተርፎም ከመጠን ያለፈ ከተወሰዱ አሉታዊ ጫና ሊኖራቸዉ እንደሚችል ያስጠነቅቃል። የአዉሮጳ ኅብረት ቀደም ብሎ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2001ዓ,ም ላይ እነዚህን ምርቶች ለገበያ ስለማቅረብም ሆነ ጥቅምና አጠቃቀማቸዉን የሚመለከት መረጃ በምግብ ሳይንስ ጉዳዮች ተመልካች ኮሚቴዉ አማካኝነት ተዘርዝሮ መመሪያ አዉጥቷል። ከ2005 እስከ 2009ዓ,ም በተመሳሳይ የዘመን ቀመር ማለት ነዉ ወደ533 የተጨማሪ ቅምም ምግቦች አዘጋጆች ምርታቸዉን ለመሸጥ ለኅብረቱ ማመልከቻ አቅርበዉ ነበር። የኅብረቱ የምግብ ሳይንስ ጉዳዮች ተመልካች ኮሚቴዉ ጥናት ምዘናዉን ሲጀምር ከአመልካቾቹ ግማሽ የሚሆኑት በቂ መረጃ እና ማብራሪያ ስላላቀረቡለት ተዋቸዉ። 186ቱ አመልካቾች ደግሞ ምክንያታቸዉ ባይገለጽም ጥያቄያቸዉን ትተዉ ከገበያዉ ፉክክር ወጡ። እንግዲህ አሁን በየአባል ሃገራቱ ለሽያጭ የቀረቡት የተጨማሪ ምግብ ቅምሞች ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ከሚካሄድ ጥናትና ምርምር በኋላ የተፈቀደላቸዉ መሆናቸዉ ነዉ።

Symbolbild Glas Milch
ምስል Colourbox/E. Atamanenko

እዚህ ጀርመን ሀገር እንዲህ ዓይነቶቹ ተጨማሪ ምግቦች በሚዋጥ እንክብል ወይም በዉኃ ሟሙቶ ሊጠጡ እንደሚችሉ ሆነዉ ወይም በዱቄት መልክ፤ አንዳንዶቹም በፈሳሽ መልክ በየመደብሩ ይገኛሉ።ብዙዎችም ይጠቀሙባቸዉ። ይህን አስመልክተን ያነጋገርናቸዉ የምግብ ሳይንስ ባለሙያዉም ሆኑ የህክምና ባለሙያዋ የሚመክሩት እንዲህ ዓይነቶቹን የተጨማሪ ምግብ ቅምሞች ከመዉሰድ በፊት ማንኛዉም ሰዉ አስቀድሞ በሰዉነቱ ዉስጥ ያለዉን የአስፈላጊ ንጥረነገር መጠን ማወቅ እንዳለበት ነዉ። ከድምጽ ዘገባዉ ይከታተሉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ