1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተፈጻሚ ሊሆን የማይችለው የእሥራ ምዕቱ ግብ፣

ሐሙስ፣ ጥቅምት 12 2002

በዓለም ዙሪያ፣ ሴት ፣ ወንድ ፣ ህጻን፣ ሽማግሌ ሳይል፣ በደፈናው በረሃብ የሚጠቁትንና የድሆችን አኀዝ፣ እ ጎ አ ፣ እስከ 2015 ዓ ም፣ ቁጥር ግማሽ-በግማሽ ለመቀነስ፣

https://p.dw.com/p/KD8U
ከእሥራ- ምዕቱ ግቦች አንዱ፣ በአደጊ አጋሮች፣ ድህነትን ግማሽ-በግማሽ መቀነስ ነው።ምስል picture alliance/dpa

እንዲሁም፣ እኩልነትን ለማሥፈን፣ ተዛማቹን HIV ንና AIDS ን ም ለመታገል፣ 189 አባል መንግሥታት የተወከሉበት የተባበሩት መንግሥታት አጠቃላይ ጉባዔ፣ እ ጎ አ በ 2000 ዓ ም፣ ጥሪ ማስተላለፉ የሚታወስ ነው። የእሥራ- ምዕቱ ትልም ፣ ግቡን እንደማይመታ ሲነገር ዓመታት ያለፉ ቢሆንም፣ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ቀውስ ካጋጠመ ወዲህ ደግሞ በይበልጥ በአፍሪቃ ተስፋው በአጅጉ ነው የደበዘዘው።

የዶቸ ቨለ የአፍሪቃው ክፍል ባልደረቦች፣ ናንሲ ሃውሽልድና ዳንኤል ፔልትዝ ያቀረቡትን ዘገባ ፣ ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል።

በድኅነት የሚማቅቁ አፍሪቃውያን፣ ስለገንዘብ የአክሲዮን ገበያ ትርፍና ኪሣራ የሚያውቁት ነገር የለም። የፋይናንስ ቀውስ ተጽእኖ ግን፣ የአነርሱንም ዕለታዊ ኑሮ ክፉኛ መጎነጡን አይተውታል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚገምተው ከሆነ፣ ሊያከትም 2 ወራት ገደማ በቀሩት 2009 ጎርጎሪዮሳዊው ዓመት በድህነት የሚማቅቁት አኀዝ 90 ሚሊዮን ገደማ ደርሷል። በኤኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ የውጭ ባለወረቶች፣ ገንዘብ ሥራ ላይ ለማዋል አልቻሉም፣ ንግዱና የልማት እርዳታውም ቀዝቅዟል። እርግጥ ነው የእሥራ-ምዕቱ አቅድ ግቡን እንደማይመታ ከተባበሩት መንግሥታት ጽ/ቤት በኩል ሲነገር አይሰማም። አንድ ባለሙያ ግን ተስፋ አስቆራጭ በመሰለ ድምፅ፣ ተማጽኖአቸውን ያሰማሉ። እርሳቸውም፣ በናይሮቢ የተባበሩት መንግሥታት የእሥራ ምዕቱ ዘመቻ የፖለቲካ አማካሪ Thomas Deve ናቸው።

«በአሁኑ ጊዜ፣ የእሥራ ምዕቱ የልማት ግብ ተፋጻሚ ሊሆን አይችልም ብሎ መናገር አደገኛ ነው። በዓለማችን፣ እቅዱን ከግብ እንዲደርስ የሚያስችል በቂ የተፈጥሮ ሀብት አለ፣ እያልን ዘወትር ስንከራከር ቆይተናል። የተፈጥሮ ሀብት ሳይሆን የሚጎድለው የፖለቲካ በጎ ፈቃድ ነው። ስለሆነም፣ በዚህ ረገድ ጉዳዩ ግልፅ ሊሆንልን ይገባል። የወደፊት ዕጣ -ፈንታችን፣ ራእያችን ክፉኛ ተጎንጧል።»

የተባበሩት መንግሥታት እንዳስታወቀው፣ የዓማአቱን ግብ ለማሣካት በያመቱ ቢያንስ ከ 121 እስከ 189 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል። በዛ ያለ ገንዘብ ደግሞ በኢንዱስትሪ የበለጸጉት መንግሥታት ፣ ባለፈው ጊዜ፣ የከሠሩ ባንኮችና ኩባንያዎች እንዲያንሠራሩ ለማድረግ በመደጎሚያነት አውለውታል። መንግሥታቱ ዕዳ ስላለባቸው በቁጠባ ላይ ማትኮር ግዴታቸው ሆኗል። የልማት እርዳታ በሚመጡት ዓመታት እጅግ መቀነሱ አይቀርም። ቶማስ ዲቭ ፣ በበኩላቸው ፣ ለጋሽ መንግሥታት ፣ የልማት እርዳታን እንዳይቀንሱ ነው የሚማጸኑት።

«የማዳኑ ተግባር ለኩባንያዎችና ለባለጸጎች ተብሎ ነው የሚከናወነው። ተራው ኑዋሪ ምንጊዜም እንደተጎሳቆለ ነው። ሀዝቡን ከትርፍ ማሳደድ ማስቀደም ይገባናል። ድሆችንና የተገፉትን ለመርዳት፣ በቂ የተፈጥሮ ሀብትና ገንዘብ አለ። »

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚያምነው የልማት እርዳታ መቀነስ፣ የታዩ የእድገት እመርታዎችን ፣ በተለይ በትምህርት ረገድ የታየውን ግሥጋሤ ትርጉም የለሽ ነው የሚያደርገው። ለምሳሌ ያህል በጋና ፣ታንዛንያ፣ ዩጋንዳና ሞዛምቢክ፣ ባለፉት ዓመታት በትምህርት ሰፊ እመርታ ነው የታየው። ሩዋንዳንና ማላዊን በመሳሰሉ አገሮች የረሀብተኛውና በድህነት የሚማቅቀው ህዝብ ቁጥር እጅግ ነው የቀነሰው። በጤና ጥበቃም ረገድ ትልቅ መሻሻል ታይቷል። ቢያንስ 2 ሚሊዮን በHIV-AIDS ህሙማን ያልተቋረጠ የመድኀኒት እርዳታ ሲያገኙ ቆይተዋል። ይህ ሁሉ፣ ቶማስ ዲቭ እንደሚሉት የተሻለ አመራር ያላቸው የተለያዩ የአፍሪቃ መንግሥታት አዎንታዊ እርምጃ ውጤት ነው።

በከፍተኛ የአመራር ደረጃ ፣ ፕሬዚዳንቶችና ጠ/ሚንስትሮች፣ በበጀት ረገድ ቅድሚያ በሚሰጠው ዐቢይ ጉዳይ ላይ ማትኮር ፣ የህዝብ እንደራሴዎችም ከህዝብ ጋር ተባብረው መሥራትና የመንግሥትን አሠራር መቆጣጠር ተገቢአቸው ነው።

የልማት እቅዶች፣ ግባቸውን እንዲመቱ ነጻ የመገናኛ ብዙኀን ጠቃሚ ድርሻ ያበረክታሉ። መንግሥታት ፣ ለእሥራ-ምዕቱ ግብ ታጥቀው እንዲሠሩ፣ ነጻ መገናኛ ብዙኅን በሚያቀርቧቸው ዜናዎች፣ ዘገባዎችና ሂሶች ማስገንዘብ ይችላሉ። ከዚህም ጋር፣ ህዝቡ በፖለቲከኞች ላይ ግፊት በማጠናከር፣ በአፍሪቃ የተከናወኑ ገንቢ ጉዳዮች ዋጋቢስ ሆነው እንዳይቀሩ እንዲጥር መቀስቀስ ይችላሉ። በኢንዱትሪ የበለጸጉ ምዕራባውያን አገሮች ዜጎችም፣ ቶማስ ዲቭ እንደሚሉት፣ የእሥራ ምዕቱ እቅዶች ግባቸውን እንዲመቱ፣ መንግሥቶቻቸውን መገፋፋት ይኖርባቸዋል።

«ለእኛ አሁን ጠቃሚው ጉዳይ፣ የፋይናንስ ቀውስ ቢያጋጥምም፣ ይህን ችግር ለማስወገድ እንችላለን። እስካሁን ብዙዎች የባለኢንዱስትሪ አገሮች መንግሥታት ፣ የተጠቀሰው ግብ እንዲሣካ የገቡትን ቃል ለመጠበቅ በመጣር ላይ ናቸው። በመንግሥቶቻቸው ላይ ፣ ጣልቃ በመግባትና ግፊትም በማድረግ ተግባራት እንዲከናውኑ የሚያደርጉ የሰሜናውያኑ አገሮች ተወላጆች ናቸው። ቀረጥ ከፋዮች እንደመሆናቸው መጠን የተገባው ቃል እንዲፈጸም መከታተል ይችላሉ።» ናንሲ ሃውሺልድና ዳንኤል ፔልትዝ፣

ተክሌ የኋላ፣

ሸዋዬ ለገሠ፣