1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቱርክና ኢራቅ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 6 2000

የቱርክ መንግስት ድንበር ዘልቆ በሰሜናዊ ኢራቅ የሚገኙ የኩርድ አማፅያንን እንዲመታ የምክር ቤቱን ፈቃድ ለማግኘት እየጣረ ነዉ።

https://p.dw.com/p/E87e
ኤርዶጋን በምክር ቤት
ኤርዶጋን በምክር ቤትምስል AP

በዛሬዉ ዕለትም በመዲናይቱ አንካራ ምክር ቤቱ በዚህ ነጥብ ላይ የተከራከረ ሲሆን ምናልባትም የብዙሃን ድጋፍ ያለዉን የድንበር አልፎ ጥቃት ስንዘራ ሳያሳልፈዉ አይቀርም። የአዉሮፓ ህብረት፤ ዩናይትድ ስቴትስና የኢራቅ መንግስት ግን እርምጃዉ ጎረቤት አገርንን መዉረር ነዉ በሚል ከመነሻዉ አልተቀበሉትም።
የቱርክ ዓላማ መሳሪያ የታጠቁትን በምህፃረ ቃል PKK በመባል የሚታወቁትን ሶስት ሺህ የኩርድ ሰራተኞች ፓርቲ ይዞታ ድንበር አልፋ መምታት ነዉ። ሃሳቡ ዛሬ የተነሳ ሳይሆን ቀደም ሲል በምርጫ እንቅስቃሴ ወቅት የጦር ኃይሉና የተቃዋሚዉ ፓርቲ በጋራ ድንበር አልፎ ጥቃት ለመሰንዘር ጥሪ አቅርበዉ እንደነበር ይታወሳል። የጠቅላይ ሚኒስትር ራሲብ ጣይብ ኤርዶጋን መንግስት ግን ይህን ያስተባብላል።

ከተመድ ዋና ፀሃፊ ባን ጊ ሙንም ሆነ ከዋሽንግተን ከወታደራዊ ርምጃ በፊት በርጋታ ማሰብ እንደሚገባት ለቱርክ ሃሳብ ተሰንዝሯል። በሰሜን ኢራቅ የሚገኙት ኩርዶች ለPKK አማፅያን ከለላ ይሰጣሉ፤ አቋማቸዉም ለዘብተኛ ነዉ በሚል ግን ኡርክ መንግስት ቡድኑ የሚፈፅመዉን ጥቃት ለመታገስ አቅም እንዳለቀበት ነዉ የገለፀዉ። PKK ከሳምንት በፊት ጥቃት ሰንዝሮ ከገደላቸዉ 30 የቱርክ ወታደሮች ሌላ በያዝነዉ ዓመት አጋማሽም እንዲሁ 50 የሚሆኑ ወታደሮችን ገድሏል። ይህን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርዶጋን ከአገር ዉስጥ ግፊት አይሎባቸዋል።


ምንም እንኳን ዩናይትድ ስቴትስም ሆኑ ኢራቅ PKKን በአሸባሪነት ቢፈርጁም በኢራቅ ብቸኛ ሰላማዊ ግዛት ቱርክ ጦር ኃይሏን ማዝመቷን አልደገፉላትም። የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች በሚገኙበት የኢራቅ ምድር የሚታየዉ አለመረጋጋት ወደዚህም ተዛምቶ የዋሽንግተንን ሚና ይባስ ያጣጥላል የሚል ስጋትም አለ። ቱርክ በሽብር ላይ በተከፈተዉ ጦርነት በአካባቢዋ ግንባር ቀደም የሚባለዉን ሚና እንደምትጫወት ከዋሽንግተን አስተዳደርም ያላት ግንኙነት ጠንካራ የሚባል ቢሆንም ይህን መሰሉ ዉሳኔዋ የሚያመጣዉ ሊኖር ይቻል በሚል ስጋት አለ። የአገሪቱ ምክር ቤት ዛሬ ያሳልፋል ተብሎ የሚጠበቀዉ ዉሳኔ ምን እንደሚሆን የአገሪቱ መንግስት ቃል አቀባይ ኬሚል ኪቼክ ሲናገሩ፤


«ድምፅ የሚሰጥበት ዋና ዓላማ በቀጥታ በአሸባሪ ድርጅቱ PKK ላይ ነዉ። ከዚያ ዉጪ ያለዉ ነገር ሁሉ ግባችን አይደለም። ኢራቅ ዉስጥ የሚኖሩት ሁሉ ወንድምና እህቶቻችን ናቸዉ ማለት ይቻላል። ያ ህዝብ ወዳጃችን ነዉ። ወታደራዊ ርምጃዉን ለመዉሰድ ፈቃድ ቢያገኝም እንኳን ሰራዊቱ ተግባራዊ እንደማያደርገዉ ነዉ ተስፋ የማደርገዉ። የኢራቅን ሰሜናዊ ግዛትም ሆነ በራሳች ምድር ፀጥታና ሰላም ሰፍኖ ማየት ስለሚፈልግ።»


እንደቃል አቀባዩ ከሆነ የቱርክ ምክር ቤቱ አዎንታዊ ምላሽ ማለት የጦር ኃይል ማዝመት ማለት አይደለም። ይልቁንም እንደአስፈላጊነቱ ድንበር አልፎ ለመሄድ አስገዳጅ ሁኔታ ቢፈጠር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ይኖራቸዋል እንጂ።

በአንፃሩ ቱርክ ወደኢራቅ ድንበር አልፋ በመግባት እሳቱን ብትጭር ነበልባሉ መልሶ ራሷን ሊለበልብ ይችላል ባይ ናቸዉ የአገሪቱ በርካታ ተቺዎች። በአሁኑ ሰዓት ቱርክ ከዓመታት በፊት በአርመናዉያን ዜጎች ላይ የፈፀመችዉን ግድያ የዘር ማጥፋት ነዉ ብሎ የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት የዉጪ ጉዳይ ዘርፍ ካሳመነ ወዲህ የቱርክ ርምጃ የከረረ የፖለቲካ ኳስ ጨዋታ ያለችዉን የሚያንፀባርቅ መስሏል። ቱርክ በሰሜን አትላንቲክ የጋራ ጦር NATO ስልታዊ ለሚባለዉ ትብብር ዓይነተኛ ጠቀሜታ ያላት አገር ናት።