1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቱርክና የኩርዶች ጥቃት

ሰኞ፣ ጥቅምት 11 2000

«ጎረቤት አገር የአሸባሪዎች መሸሸጊያ ከሆነች እኛም ዓለም ዓቀፉን ህግ የመጠቀም መብት አለን ።» የቱርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሬሴፕ ተይፕ ኤርዶጋን

https://p.dw.com/p/E87a
ልጃቸው በፒኬኬ የተገደለባቸው ቤተሰቦች ከሟች ፎቶግራፍ ጋር
ልጃቸው በፒኬኬ የተገደለባቸው ቤተሰቦች ከሟች ፎቶግራፍ ጋርምስል AP

አስራ ሁለት የቱርክ ወታደሮች ትናንት በኢራቅ ወሰን አቅራቢያ በኩርድ አማፅያን መገደላቸው የቱርክን ህዝብ አስቆጥቷል ። መንግስት ድንበር ተሻግሮ አማፅያኑ ወደ ሚገኙበት ወደ ኢራቅ በመዝለቅ ግድያውን በፈፀሙት የኩርድ አማፅያን ላይ የአፀፋ ዕርምጃ እንዲወስድ ህዝቡ ግፊት እያደረገ ነው ። ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ ቱርክ ይህን ከማድረግ እንድትቆጠብ መምከርዋን ቀጥላለች ። በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ያሉት የቱርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሬሴፕ ተይፕ ኤርዶጋን በበኩላቸው መንግስታቸው በዓለም ዓቀፍ ህግጋት መሰረት ለሚወስዳቸው ዕርምጃዎች ከማንም ፈቃድ ማግኘት አያሻውም ይላሉ ። አስራ ሁለቱ የቱርክ ወታደሮች የተገደሉት በእንግሊዘኛው ምህፃር ፒኬኬ በመባል በሚጠራው የኩርድ ሰራተኞች ፓርቲ አማፅያን ነው ። በቱርክ ወታደሮች ላይ ይህን መሰሉ ጥቃት የደረሰው ከሰሜን ኢራቅ በሚንቀሳቀሱት በፒኬኬ አማፅያን ላይ መንግስት ወታደራዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ የቱርክ ፓርላማ በተስማማ በአራተኛው ቀን መሆኑ ነው ። በትናንቱ ግድያ ቱርኮች ክፉኛ ተበሳጭተዋል ። የቱርክ ኃይል ድንበር ተሻግሮ እንዲያጠቃ መንግስት ትዕዛዝ እንዲያስተላልፍ ጩኽታቸውን እያሰሙ ነው ። ዛሬ በቱርክ ትልቂቱ ከተማ ኢስታንቡል ውስጥ አደባባይ የወጡ ወደ ሶስት ሺህ የሚጠጉ ተቃዋሚዎች ፒኬኬን ሲያወግዙ መንግስት አፋጣኝ ወታደራዊ ዕርምጃ ባለመውሰዱ ወቅሰዋል ። ከዚያም አልፈው የኤርዶጋን መንግስት ሀላፊነቱን በቅጡ ባለመወጣቱ ስልጣን እንዲለቅም ጠይቀዋል ። የተቃውሞ ሰልፉ በኢስታንቡል ብቻ አልነበረም ። በዋና ከተማይቱ በአንካራ እንዲሁም በወደብ ከተማዋ በሜርሲንም ተመሳሳይ ሰልፎች ተካሂደዋል ። ከህዝቡ በኩል ይህን መሰሉ ግፊት የሚደረግባቸው የቱርኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርዶጋን ከዩናይትድ ስቴትስ በኩል ደግሞ ሌላ ጫና ገጥሟቸዋል ። ቱርክ በአማፅያኑ ላይ ዕርምጃ ከመውሰድ እንድትታገስ ዩናይትድ ስቴትስ ጠይቃለች ። የዩናይትድ ስቴትሱ መከላከያ ሚኒስትር ሮበርት ጌትስ እንዳሉት ቱርክ በፒኬኬ ላይ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄዷ ራስዋንም ሆነ ማንንም አይጠቅምም ።
ድምፅ ................................
“ድንበር ተሻጋሪ ሰፊ ዘመቻ መካሄዱ ከቱርክ ከኛም እንዲሁም ከኢራቅም ጥቅም ጋር የሚቃረን ነው የሚሆነው “
ጠቅላይ ሚኒስትር ስለ ሁኔታው ከዩናይትድ ስቴትስዋ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮንዶሊሳ ራይስ ጋር ትናንት በስልክ ባካሄዱት ውይይት ሰሜን ኢራቅ በሚገኙት የፒኬኬ አማፅያን ላይ ዋሽንግተን የበኩልዋን ዕርምጃ እንድትወስድ ጠይቀው ነበር ። ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያገኙት መልስ ግን ታገሱ የሚል ነው ። ኤርዶጋን ለጋዜጠኖች እንደተናገሩት የጥቂት ቀናት ጊዜ ስጡን ነው የተባሉት ። ብሪታኒያ ደግሞ በቱርክ ወታደሮች ላይ የተፈፀመውን ጥቃት አውግዛ ቱርክ ከኢራቅ ጋር መፍትሄ ሊያመጣ የሚችል ውይይት እንድታካሂድ ሀሳብ አቅርባለች ። ሆኖም ኤርዶጋን በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት ለዚህ ሁሉ ትዕግስቱ ያላቸው አይመስልም ። ጎረቤት አገር የአሸባሪዎች መሸሸጊያ ከሆነች እኛም ዓለም ዓቀፉን ህግ የመጠቀም መብት አለን ። ለዚህም ከማንም ፈቃድ ማግኘት አይጠበቅብንም ነው ያሉት በጋዜጣዊ መግለጫቸው ። እንደርሳቸው ፒኬኬን አሸባሪ ከማይል መንግስት ጋር መደራደርም አይሹም ።
ድምፅ
“ፒኬኬን እንደ አሸባሪ ድርጅት ከማያይ መንግስት ጋር ቱርክ አትነጋገርም ። “
የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ ቱርክ በፀረ ሽብሩ ዘመቻ ያላትን አቋም እንደሚደግፍና ከጎንዋም እንደሚቆም አስታውቋል ። ይሁንና አንካራ ፒኬኬን ለማጥቃት ወታደሮችዋን ወደ ኢራቅ እንዳትልክ ከማስጠንቀቅ ወደ ኃላ አላለም ። የቱርክ ወታደራዊ ባለስልጣናት እንደተናገሩት ትናንት አማፅያኑ ካደረሱት ጥቃት በኃላ በተወሰደው ዕርምጃ ከአማፅያኑ ወገንም ወደ ሰላሳ ሁለት የሚሆኑ ተገድለዋል ።